የአፋሩ እሳተ ገሞራ መቼ እንደሚፈነዳ ማወቅ ይቻል ነበር?

የሃይሊ ጉቢ እሳተ ገሞራ የለቀቀው አመድ በቀይ ባሕር ሲጓዝ የሚያሳይ የሳተላይት ምሥል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሃይሊ ጉቢ እሳተ ገሞራ የለቀቀው አመድ በቀይ ባሕር ሲጓዝ የሚያሳይ የሳተላይት ምሥል

ሃይሊ ጉቢ እሳተ ገሞራ የፈነዳው ከ12ሺህ ዓመታት በኋላ ነው። እስካለፈው እሑድ ድረስ አንዳችም እንቅስቃሴ ሳያሳይ ቆይቷል።

የእሳተ ገሞራው አመድ በነፋስ አማካይነት አንድ ሺህ ጫማ ተጉዞ ጥቃቅን ቅንጣቶች ሰማይ ላይ ታይተዋል።

ሃይሊ ጉቢ ከኤርታአሌ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ኤርታአሌ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ንቁ እሳተ ገሞራዎች (active volcano) ቀዳሚው ነው።

የሃይሊ ጉቢ ፍንዳታ በከፍተኛ መጠን ያለው 'ማግማ' በመውጣቱ በአቅራቢያው ያለው መሬት ጎድጊዷል።

ማግማ (magma) ከምድር በታች የሚገኝ በከፊል አልያም ሙሉ በሙሉ የቀለጠ ዓለት ነው።

ሃይሊ ጉቢ እና ኤርትአሌ በምሥራቅ አፍሪካ ሸለቆ ይገኛሉ። በዚህ ሸለቆ የአፍሪካ እና የአረቢያን ቴክቶኒክ ፕሌቶች (ከምድር በታች ያሉ ንብርብር ዓለቶች) ይገናኛሉ።

ቴክቶኒክ ፕሌቶች (tectonic plates) የምድር የላይኛው ክፍል የሚሸፍኑ ጠንካራ ዓለቶች ናቸው።

በዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ብሪስቶል የምድር ሳይንስ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጁልየት ቢግስ ቀጣናውን ለዓመታት አጥንተዋል።

የኤርትአሌ እና የሃይሊ ጎቢ ፍንዳታዎች ትስስር እንዳላቸው ይናገራሉ።

"ኤርትአሌ እየሟሸሸ ስለመጣ ሁሉም ነገር የሚወጣው በሃይሊ ጉቢ በኩል ነው" ይላሉ።

ማግማ ውስጥ ፈሳሽ ዓለት፣ ሚኒራሎች እና የሟሟ ጋዝ ይገኛል። ከምድር በታች የሚታመቀው ጋዝ መሬት ውስጥ ይስፋፋል።

ለዚህም ምክንያቱ በአካባቢው የሚኖር ለውጥ እና ከምድር በታች ያለው ጫና ነው።

ከመሬት ሥር ያለው ጫና (pressure) ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ማግማው ምድርን ፈንቅሎ ይወጣል።

ከእሳተ ገሞራ ሥር አዲስ ማግማ ሲፈጠር እንደ ሃይሊ ጉቢ ያሉ ፍንዳታዎች ይከሰታሉ።

በበርሚንግሀም ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ሳይንስ ተመራማሪ ማይክ ካሲዲ እንደሚሉት፤ ሌላው የክስተቱ መነሻ ሊሆን የሚችለው አካባቢያዊ ለውጥ የበረዶ መቅለጥ (glacier melting) ወይም የመሬት መንሸራተት ነው።

ካርታ

ንቁ እሳተ ገሞራ እና ፍዝ እሳተ ገሞራን ምን ይለያቸዋል?

አክቲቭ ቮልካኖ (active volcanoes) በግርድፉ ንቁ እሳተ ገሞራ ብለን መተርጎም እንችላለን። ተቃራኒው ዶርማንት ቮልካኖ (dormant volcanoes) ፍዝ እሳተ ገሞራ ሊባል ይችላል።

ሃይሊ ጉቢ ከመፈንዳቱ አስቀድሞ ፍዝ እሳተ ገሞራ ነበር። ፍዝ እሳተ ገሞራ እንደ ንቁ እሳተ ገሞራ የሚታይበት ጊዜም አለ።

ከ11,650 ዓመታት በፊት ምድር ለመጨረሻ ጊዜ በበረዶ ከተሸፈነች (Ice Age) ወዲህ የተነሱ እሳተ ገሞራዎች ንቁ ይባላሉ።

ፍዝ እሳተ ገሞራ ባለፉት ዓመታት ባይፈነዳም በማንኛውም ጊዜ የመፈንዳት አቅም አለው።

ሌላኛው የእሳተ ገሞራ ዓይነት እረፍት አልባ (restless) ሲሆን፤ ከመሬት ሥር የማግማ ክምችት ወይም እንቅስቃሴ ያሳያል።

ከምድር በታች ያለ እንቅስቃሴ አልያም እሳተ ገሞራ እረፍት አልባ እሳተ ገሞራ ፈንቅሎ እንዲወጣ ይገፋፋሉ።

በአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬል የሚሠሩት ማይክል ፖላንድ እንደሚሉት፤ ከላይ የተዘረዘሩት የእሳተ ገሞራ እንቅስቃሴዎች ከተቀመጠላቸው ሳይንሳዊ መርኅ አፈንግጠው ሊወጡ የሚችሉበት ጊዜ አለ።

"የሎስቶን እሳተ ገሞራ በ70 ሺህ ዓመታት ባይፈነዳም ንቁ እሳተ ገሞራ ነው እንላለን። አንዳንዶቹ እሳተ ገሞራዎች አንቀላፍተው ለረዥም ጊዜ ይቆዩና ድንገት ይፈነዳሉ" ሲሉ ያስረዳሉ።

ሌላው የእሳተ ገሞራ ዓይነት በድጋሚ የማይፈነዱ (extinct volcanoes) ናቸው። እነዚህ ማግማ ስለሌላው ፈንድቶ መውጣት አይችሉም።

የሩሲያው ቦልሻያ ኡዲና በድጋሚ የማይፈነዱ እሳተ ገሞራዎች ዝርዝር ውስጥ ቢቆይም በአውሮፓውያኑ 2017 ውስን እንቅስቃሴ ስለተስተዋለ ለዘብተኛ እሳተ ገሞራ ተብሏል።

የኢኳዶር ለዘብተኛ እሳተ ገሞራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢኳዶር ለዘብተኛ እሳተ ገሞራ

እሳተ ገሞራ ሊፈነዳ ሲል የሚያሳያቸው ምልክቶች

እሳተ ገሞራ መቼ እንደሚፈነዳ ለማወቅ መረጃ መሰብሰብ ያስፈልጋል። ሙያዊ ትንበያ ለማስቀመጥ ማስረጃዎች ሊገኙም ይገባል።

ርዕደ መሬት፣ የእሳተ ገሞራ ጋዝ እንቅስቃሴ አልያም ሌላ የመሬት በታች ንቅናቄ (Seismic activity) እሳተ ገሞራ ሊፈነዳ መቃረቡን ይጠቁማሉ።

የመረጃ ክምችት ሲጨምር እሳተ ገሞራ መቼ እንደሚፈነዳ በተሻለ ሁኔታ መገመት ይቻላል።

በአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬል የሚሠሩት ማይክል ፖላንድ "የእሳተ ገሞራ ፍንዳታን በመተንበይ ረገድ እየተሻሻልን መጥተናል። ለዚህ ምክንያቱ የተሻለ የመረጃ ክምችት መኖሩ እና የፍንዳታ ምልክቶች መታየት ነው" ይላሉ።

ሆኖም ግን እሳተ ገሞራ ሊፈነዳ መቃረቡን የሚያሳዩ ምልክቶች ታይተው "መሬት በስሱ ብቻ የሚከፈትበት" ወቅትም እንዳለ ያስረዳሉ።

ይሄ ውስን ክፍተት ማግማውን ከምድር ሥር ያስወጣል።

በዩኒቨርስቲ ኦፍ ብሪስቶል የምድር ሳይንስ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጁልየት ቢግስ እንደሚሉት፤ እሳተ ገሞራን ለመተንበይ የሳተላይት ምሥል ጉልህ ሚና ይጫወታል።

እንደ ሃይሊ ጉቢ ባሉ በቀላሉ ሊደረስባቸው በማይችሉ አካባቢዎች የሳተላይት ምሥልን በመጠቀም ግምት ማስቀመጥ እንደሚቻል ይገልጻሉ።

"የምናስቀምጣቸው ግምቶች በሙሉ ትክክል ነበሩ ማለት አይደለም። የሳተላይት ምሥል መጠቀም ከመጀመራችን በፊት የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ እንቅስቃሴውን ሳንመለከት ቀርተናል" ሲሉም ያክላሉ።

ሃይሊ ጉቢ ለ12 ሺህ ዓመታት ለዘብተኛ ሆኖ መቆየቱን ይጠራጠራሉ። የእሳተ ገሞራ እንቅስቃሴው ሳይታይ ወይም ሳይመዘገብ አልፎ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ሰው አልባ አውሮፕላን በመጠቀም በሰው ሊለካ የማይችል ከፍተኛ ሙቀትን መመዝገብም ይቻላል።

ሬይነር ተራራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ፣ ዋሸንግተን የሚገኘው ሬይነር ተራራ አደገኛ ከሚባሉት እሳተ ገሞራዎች አንዱ ነው።

አደገኛው እሳተ ገሞራ የቱ ነው?

በዩኒቨርስቲ ኦፍ በርሚንግሀም የአካባቢ ሳይንስ ተመራማሪ ማይክ ካሲዲ እንደሚሉት፤ በዓለም እጅግ አደገኛው እሳተ ገሞራ የሚባለው ሰው በብዛት በሚኖርበት ወይም ሕንጻዎች አካባቢ የሚከሰተው ነው።

በአሜሪካ፣ ዋሸንግተን የሚገኘው ሬነር ተራራ እና በጣልያን፣ ኔፕል የሚገኘው ካምፒ ፍሌግሪን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ።

ከንቁ እና ለዘብተኛ እሳተ ገሞራዎች መካከል 45 በመቶ በሚሆኑት ላይ ክትትል ይደረጋል።

በዋነኛነት ክትትሉ የሚደረገው በመንግሥታት እና በግለሰቦች ሲሆን፤ ብዙም መረጃ የማይሰበስቡ አገራትም አሉ።

የጣልያኑ ኢታና እና የአሜሪካው የሎስቶን ከፍተኛ ክትትል ከሚደረግባቸው እሳተ ገሞራዎች መካከል ይጠቀሳሉ። ኢታና እሳተ ገሞራ ከአውሮፓ እሳተ ገሞራዎች መካከል እጅግ ንቁ የሚባለው ነው።

በኢንዶኔዥያ፣ በፊሊፒንስ እና በቫንዋቱ ከሚገኙ 160 እሳተ ገሞራዎች በበለጠ ስለ ኢታና ተራራ የተሠሩ ጥናቶች በቁጥር ይልቃሉ።

የሃይሊ ጉቢ ፍንዳታ አብዛኞቹን ባለሙያዎች ያስደነቀ ነው። ድንገት ከመከሰቱም በላይ እምብዛም ያልታወቀ እሳተ ገሞራ ነበር።

"በዓለም ወደ 1,500 እሳተ ገሞራዎች አሉ። ስለዚህኛ [ሃይሊ ጉቢ] ብዙም አላውቅም። ወደ አካባቢውም ሄጄ አላውቅም" ሲሉ ፕሮፌሰር ማይክ ካሲዲ ያስረዳሉ።

የሃይሊ ጉቢ ፍንዳታ አብዛኞቹን ባለሙያዎች ያስደነቀ ነው። ድንገት ከመከሰቱም በላይ እምብዛም ያልታወቀ እሳተ ገሞራ ነበር።

ኤርታአሌ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ንቁ እሳተ ገሞራዎች (active volcano) ቀዳሚው ነው።
የምስሉ መግለጫ, ኤርታአሌ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ንቁ እሳተ ገሞራዎች (active volcano) ቀዳሚው ነው።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው ንቁ እሳተ ገሞራ የሚገኝባቸው አገራት

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት አገራት በንቁ እሳተ ገሞራ ብዛት ከተቀረው የዓለም ክፍል ይበልጣሉ። መረጃው የተገኘው በስሚሶኒያን ተቋም ሥር ካለው 'ግሎባል ቮልካኒዝም ፕሮግራም' ነው።

  • አሜሪካ- 165
  • ጃፓን- 118
  • ሩሲያ- 107
  • ኢንዶኔዥያ- 101
  • ቺሊ- 90
  • ኢትዮጵያ- 50
  • ፓፓው ኒው ጊኒ- 39
  • ኢኳዶር- 36
  • ሜክሲኮ- 35
  • አይስላንድ- 35