ህወሓት ለሦስት ወራት ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መታገዱን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

የህወሓት አርማ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ የተሰጠው የስድስት ወር ጊዜ በመጠናቀቁ ለሦስት ወራት ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መታገዱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጮ ቦርድ አስታወቀ።

ህወሓት በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበ ጊዜ አንስቶ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ፣ መተዳደሪያ ደንቡን ማጽደቅ እና አመራሮችን መምረጥ ቢኖርበትም "ይህንን ባለማክበሩ" እግዱ እንደተጣለበት ምርጫ ቦርድ የካቲት 5/2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ፓርቲው በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበት ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም. እስከ የካቲት 3/ 2017 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ በሕግ የተሰጠው የስድስት ወር ጊዜ በመጠናቀቁ ቦርዱ የካቲት 4/2017 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ገልጿል።

ህወሓት በኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዘገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1332/2016 መሠረት በልዩ ሁኔታ ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም. ተመዘግቦ ነበር።

ምዝገባውን ተከትሎ ፓርቲው ሊከተለው እና ሊፈጽመው ስለሚገባው ግዴታዎች ቦርዱ የጻፈው ደብዳቤ እንዲሁም የምዝገባ እና የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቅትን መቀበሉን አስታውሷል።

ህወሓት አዋጅ እና መመሪያዎችን ባለማክበር "ጉልህ ጥሰት ፈጽሟል" ያለው ምርጫ ቦርድ "ፓርቲው ይህ ውሳኔ ከደረሰው ቀን ጀምሮ ለሦስት ወራት በምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ አንዳይሣተፍ እንዲታገድ ቦርዱ ወስኗል" ብሏል።

ህወሓት "ለእግዱ ምክንያት የሆነውን ጥሰት በማረም" ሊያደርግ የሚገባውን ጠቅላላ ጉባኤ፣ የጉባኤ ቅድመ ዝግጅቱን ተግባራት ለቦርዱ በጽሑፍ ሲያሳውቅ እና ቦርዱ ይህንን ሲያረጋግጥ ተቋሙ ዕግዱን እንደሚያነሳ አስታውቋል።

ሆኖም ፓርቲው በተሰጠው የሦስት ወራት የዕግድ ጊዜ እርምት ካልወሰደ "የፓርቲው ምዝገባ እንዲሰረዝ ቦርዱ መወሰኑም" በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።

ቦርዱ በኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ እንዲሁም መመሪያ መሠረት ህወሓት ያለበትን ግዴታዎች እንዲወጣ በተለያዩ ጊዜያት በጻፋቸው ደብዳቤዎች ማሳሰቡን ገልጿል።

ለህወሓት በመጨረሻ ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ የማድረጊያ ጊዜ ገደቡ ሊጠናቀቅ ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ እንደቀረው የሚገልጽ የማሳሰቢያ ደብዳቤ ቦርዱ መጻፉን በማኅበራዊ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በዚህ ደብዳቤ ላይ "ለጠቅላላ ጉባዔ ዝግጅት የሚያስፈልገውን የቅድመ ጉባዔ ዝግጅት የተመለከቱ ሥራዎችን ቦርዱ መከታተል እንዲችል ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔውን ከማድረጉ 21 ቀናት በፊት ጉባዔው የሚደረግበትን ቀን ለቦርድ እንዲያሳውቅ የሚጠበቅ ነው" ይላል።

ፓርቲው ይህንን የሕግ ግዴታ በተሰጠው ቀነ ገደብ ካልፈጸመ ምርጫ ቦርድ ሕጉን መሠረት በማድረግ ተገቢ ነው የሚለውን ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑንም በዚህ መግለጫው አስፍሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፓርቲው የአዋጁን የመመሪያውን ድንጋጌዎች እና የቦርዱን ውሳኔዎች በማክበር የጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሄድ፣ መተዳደሪያ ደንቡን ሳያፀድቅ እና አመራሮቹን ሳይመርጥ ቀነ ገደቡ ተጠናቋል ብሏል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቱ አባላት የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን አንዳንድ ወረዳዎችን ያላሳተፈው እንዱሁም ከምርጫ ቦርድ ዕውቅ እና ውጪ የህወሓት 14ኛ ጉባኤ ባለፈው ዓመት ነሐሴ መካሄዱ ይታወሳል።

ህወሓት በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን እንዲሁም የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠቱን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ተቋሙ ሳያውቅ እንዲሁም የቦርዱ ታዛቢዎች ባልተገኙበት ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤው ሊካሄድ እንደማይችል አስታውቆ ነበር።

ጠቅላላ ጉባኤው ከቦርዱ ፍቃድ ውጪ ከተካሄደ ለዚህ ጉባኤም ሆነ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ዕውቅና እንደማይሰጥም ከጉባኤው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ለህወሓት በጻፈው ደብዳቤ ላይ መግለጹ ይታወሳል።

በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን ያልተቀበለው ህወሓት፣ ያቀረበው ጥያቄ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስነት መሆኑን እና የተሰጠው መልስ ግን ሌላ መሆኑን ጠቅሷል።

ህወሓት፣ ግንቦት መጨረሻ ላይ የጸደቀው የፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት እንደማይመለስ በመገንዘቡ በጉዳዩ ላይ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎች የፌደራል መንግሥት ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገው የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ከስምምነት ተደርሷል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በአፍሪካ ኅብረት ፓነል ውይይት ላምይ እንዲሁ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ከስምምነት ተደርሷል ብሏል።

ይሁን እንጂ ቦርዱ የተደረሱ መግባባቶችን ወደጎን በመተው ጥያቄውን በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣ አዋጅ ላይ ተመሥርቶ የሰጠውን ምላሽ አልቀበልም ማለቱ ይታወሳል።

የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ሦስት ወራት ገደማ በኋላ የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት በምርጫ ቦርድ መሰረዙ ይታወሳል።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ፓርቲው በሊቀመንበሩ እና በምክትል ሊቀመንበሩ በሚመሩ ቡድኖች ተከፍሎ እየተወዛገበ ይገኛል።

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን በዶ/ር ደብረጽዮን በሚመራው ሌላኛው ቡድን ምክንያት ሥራውን በአግባቡ ለማከናወን እንቅፋት እንደገጠመው በመግለጽ ክስ ሲሰነዝር ቆይቷል።

ለወራት በገለልተኝነት የቆዩት የትግራይ ወታደራዊ አመራሮች አብዛኞቹ በደብረጽዮን ለሚመራው ወገን ድጋፍ መስጠታቸውን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ስጋት ተፈጥሯል።

በድርጅቱ ሊቀመንበር የሚመራው የህወሓት ቡድን ከዚህ ቀደም ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚደግፍ የገለጸው የትግራይ ሠራዊት አመራሮች በቅርቡ ያወጡት መግለጫ፣ ድጋፉን ለዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን መስጠቱን በተዘዋዋሪ አመልክቷል።

የሠራዊቱ አመራሮች ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም እየሞከረ ነው በማለት ወቅሶ "የተዳከመ" እና "ተልዕኮውን የዘነጋ" ያለውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማጠናከር አመራሮቹ ተነስተው በሌሎች መተካት እንዳለባቸው አሳስቧል።

በዚህም መሠረት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ለተካሄደውን የህወሓት 14ኛ ጉባኤ እውቅና በመስጠት በጉባኤው ውሳኔ መሠረት የጊዜያዊ አስተዳደር የአመራሮች ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በአዲስ እንዲዋቀር ወስነናል ያሉት የትግራይ ሠራዊት አዛዦች "መፈንቅለ መንግሥት አውጀዋል" ሲል የፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ጽህፈት ቤት መክሰሱ ይታወሳል።

የሠራዊት አዛዦቹ የሰጡት መግለጫ "የጦርነት አዋጅ እና ሥርዓት አልበኝነት" የሚያስከትል በመሆኑ የትግራይ የፀጥታ አባላት ሁኔታውን "ልብ ብለው በመገንዘብ አትኩሮት እንዲነፍጉት እና ከዚህ ውጪ የሚመጣው ማንኛው ዓይነት ትዕዛዝን ተግባራዊ እንዳያደርጉ እናሳስባለን" ሲል የጊዜያዊ አስተዳደሩ ጠይቋል።