የኬንያ የተቃዋሚ መሪ ራይላ ‘የመግደል ሙከራ’ ተደረገብኝ አሉ

የራይላ መኪና

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የተቃዋሚ መሪ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ መኪናቸው በሰባት ጥይት እንደተመታና እርሳቸውንም ለመግደል ሙከራ መደረጉን ተናገሩ።

ራይላ ትናንት ሐሙስ ዕለት በጠሩት ጸረ መንግሥት ተቃውሞ ላይ ነው ህይወታቸው ላይ ያነጣጠረ ሙከራ ደርሶብኛል ያሉት።

በዋና መዲናዋ ናይሮቢ ኢስትላንድ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ፖሊስ እሳቸውና ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ኢላማ አድርጎ እንደነበርም በሚዲያ መግለጫቸው ተናግረዋል።

የሳቸውን ጨምሮ የሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር መኪኖችም በፖሊስ ጥቃት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

በተጨማሪም በዚህ በተቃዋሚ ፓርቲ ጥምረት በተጠራው የጸረ መንግሥት የአደባባይ ተቃውሞ ፖሊስ ጋዜጠኞችን ኢላማ ያደረገ ነው ሲሉ በተጨማሪ ተናግረዋል።

ናይሮቢ የሚገኘውና ዋነኛ የዜና ምንጭ የሆነው የሮያል ሚዲያ አገልግሎት ቢሮዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም እቅድ መያዙንም ነው በዚህ ወቅት የተናገሩት።

በዚህ ተቃውሞ ሰልፎች ላይ ባለስልጣናት የሚያደርሱትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ችላ በማለት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ተችተዋል።

መንግሥት በአገሪቱ ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት እንዲሻሻል እንዲሁም የምርጫ ማሻሻያን ጨምሮ ሌሎች ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱ በመጪው ሰኞ መጋቢት 25፣ 2015 ዓ.ም ታላቅ የተባለውን የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያካሂዱ ተናግረዋል።

ሃሙስ ዕለት በነበረው አገር አቀፍ ተቃውሞ ስድስት ጋዜጠኞች የቆሰሉ ሲሆን ይህም ባለፈው ሳምንት የተቃውሞ ሰልፉ ከተጀመረ ወዲህ የቆሰሉ የሚዲያ ባለሙያዎችን ቁጥር 22 አድርሶታል።

“በኬንያ በቅርብ ወቅት በጋዜጠኞች ላይ እየተሰነዘረ ያለው ጥቃት አሜሪካን ያሳስባታል። የፕሬስ ነጻነት እና ደህንነትን መጠበቅ የዲሞክራሲ መሰረት ነው” ሲሉ በኬንያ የአሜሪካ አምባሳደር ሜግ ዊትማን አርብ ማለዳ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ራይላ ኦዲንጋና እሳቸው የሚመሩት አዚሚዮ ላ ኡሞጃ የተባለው የፓርቲዎች ጥምረት መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለመግታት አልቻለም እንዲሁም ፕሬዚዳንት ሩቶ ያሸነፉበት ምርጫ የተጭበረበረ ነው በሚልም ነው ከወር በፊት ተቃውሞ የጠሩት።

ምንም እንኳን የምርጫ ውጤቱ በኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተረጋገጠ ቢሆንም ራይላ ኦዲንጋ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል በየሳምንቱ ሰኞ እና ሐሙስ የሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎችን ጠርተዋል።