ቻይና ከቡድን 20 ሃገራት ተለይታ የሩሲያን ወረራ ከማውገዝ ተቆጠበች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቻይና ከቡድን 20 ሃገራት ተለይታ የሩሲያን ወረራ ከማውገዝ ተቆጠበች
የዓለማችን ግዙፍ ምጣኔ ሃብት ያላቸው ሃገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች ሕንድ ውስጥ ውይይት ሲያደርጉ ከርመዋል።
ሚኒስትሮቹ ውይይታቸውን ሲያጠናቅቁ አንድ ወጥ የሆነ አቋም ይፋ ሊያደርጉ ቢሰናዱም ቻይና አሻፈረኝ ብላለች።
መግለጫው ሩሲያ ጎረቤቷ ዩክሬንን ወራለች የሚል ነው።
የሩሲያን ወረራ አጥብቆ የሚቃወመውን ይህን መግለጫ ቤይዢንግ አልፈርምም ብላለች።
ሞስኮ፤ “ፀረ-ሩሲያ” ምዕራባዊያን ሃገራት ናቸው ቡድን 20 የተሰኘውን ክንፍ ያቋቋሙት ትላለች።
ቻይና በዚህ ሳምንት አንድ ዓመት የደፈነውን ጦርነት ለማስቆም ይሆናል ያለችውን ዕቅድ ይፋ ብታደርግም አንዳንዶች ዕቅዱን ለሩሲያ ያደላ ብለውታል።
የቡድን 20 ሃገራት በሕንዷ ቤንጋሎር ከተማ ስብሰባቸውን ሲያከናውኑ በዩክሬን ጉዳይና ሩሲያ ላይ መጣል ስላለበት ማዕቀብ በተለመከተ ሳይስማሙ ቀርተዋል።
የስብሰባው አጀንዳ እንደሚጠቁመው ከሩሲያና ቻይና በቀር ጦርነቱን በተመለከተ ሁሉም ሃገራት ከስምምነት ደርሰዋል።
ቻይና፤ የዩክሬንን ጦርነት በተመለከተ እምብዛም አስተያየት ስትሰጥ አትታይም። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዲፕሎማሲ ሥራዋን አጠናክራለች።
የቻይናው ጉምቱ ዲፕሎማት አውሮፓን የጎበኙ ሲሆን በሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላዲሚር ፑቲን ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ቻይን ከሰሞኑ ባሳተመችው ጦርነቱን ለማስቆም ይረዳል ባለቸው ዕቅድ የሰላም ውይይት እንዲካሄድና ሁለቱም የሌላውን ድንበር እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርባለች።
ነገር ግን 12 ነጥብ ያለው የሰላም ዕቅድ ሩሲያ ወታደሮቿን ከዩክሬን ታስወጣ አሊያም ሩሲያ ወረራ ማድረጓ ትክክል አይደለም የሚል ሐሳብ አልያዘም።
ሩሲያ፤ የቻይናን ዕቅድ በበጎ ብትመለከተውም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን “ፕሬዝደንት ፑቲን ካደነቁት ምኑን ጥሩ ዕቅድ ሆነ?” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
የቡድን 20 ሃገራት ውይይታቸውን ሲያጠናቅቁ የሕንድ ነባር ባለሥልጣን የሆኑት አጃይ ሴዝ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው የቻይናውና የሩሲያ ተወካዮች “እኛ ሥራችን ምጣኔ ሃብትና ፋይናንስን የተመለከተ ነው” በሚል የአቋም መግለጫውን አንፈርምም እንዳሉ ተናግረዋል።
“ነገር ግን 18ቱ አባል ሃገራት ይህ ጦርነት ለዓለም ምጣኔ ሃብት ትሩፋት አለው በማለት መግለጫውን ደግፈዋል” ብለዋል።
17 አንቀፆች የያዘው መግለጫ ከዩክሬን ጦርነት ባለፈ በቅርቡ የተከሰተውን የቱርክ ርዕደ-መሬት፣ የዓለም አቀፍ ግብር ፖሊሲና በምግብ ራስን መቻልን ዳሷል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የቡድን 20 ሃገራት “ሥራ የተቃኘው በምዕራባዊያን አጀንዳ መሆኑና ፀረ-ሩሲያ አቋም መያዙ” አሳዛኝ ነው ብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አሜሪካን፣ የአውሮፓ ሕብረትንና የቡድን 7 ሃገራትን ወቅሶ እኒህ ሃገራት “በግልፅ ተፅዕኖ እያደረባቸው ነው” ሲል ገልጧል።
የጀርመን ፋይናንስ ሚኒስትር ክሪስቲያን ሊንደር “ይህ ጦርነት የተጀመረውን በሩሲያና ፑቲን አማካይነት ነው። ይህ በዚህ ስብበሳ ላይ በግልጥ ሊወራ ይገባል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጦርነት ካወጀች በኋላ የተደረጉ የቡድን 20 ሃገራት ስብሰባዎች ወጥ አቋም ያለው መግለጫ ማውጣት ተስኗቸዋል።
ባፈለው ሐሙስ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ሩሲያን ዩክሬንን ወራለች የሚል አቋም አንፀባርቋል።
ይህ አቋም 141 ሃገራት ሲደግፉት፤ 32 ሃገራት ድምፅ ተዓቅቦ አድርገዋል። ሩሲያን ጨምሮ 7 ሃገራት ደግሞ ተቃውመውታል።












