በትግራይ ክልል ሦስት አካባቢዎች ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን ፖሊስ ገለጸ

የድሮን ጥቃት የተፈጸመበት ተሽከርካሪ

የፎቶው ባለመብት, Enticho Town Communication

የምስሉ መግለጫ, የእንትጮ ከተማ አስተዳደር በሌሎች አካባቢዎች በድጋሚ የድሮን ጥቃት "ሊፈጸም ስለሚችል ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ" እንዲያደርግ አሳስቧል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን ውስጥ በሚገኙ ሁለት ከተሞች እና አንድ ወረዳ ውስጥ አርብ ሌሊት እና ዛሬ ንጋት ላይ የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸውን ቢቢሲ ያገኛቸው መረጃዎች አመለከቱ። እንትጮ በተባለችው ከተማ በተፈጸመው የድሮን ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ አንድ ሰው ደግሞ መቁሰሉን የከተማዋ ፖሊስ ለቢቢሲ ትግርኛ ገልጿል።

የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ዳግም ግጭት ውስጥ መግባታቸው እየተገለጸ ባለበት በዚህ ወቅት የድሮን ጥቃት የተፈጸመው ትናንት አርብ ጥር 22/2018 ነው።

ጥቃቱ የተፈጸመው እንትጮ እና ገንደበታ ከተሞች እንዲሁም አሕፈሮም ወረዳ ውስጥ እንደሆነ ፖሊስ እና ምንጮች ተናግረዋል።

በእንትጮ እና ገንደበታ ከተሞች የተፈጸሙት የድሮን ጥቃቶች ተሽከርካሪዎችን ዒላማ እንዳደረጉ ተገልጿል።

የእንትጮ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ተስፋይ አማረ እንደሚናገሩት በከተማዋ ሁለት ተሽከርካሪዎች ላይ የድሮን ጥቃት ተፈጽሟል። ጥቃቱ ከሌሊቱ ዘጠኝ እስከ 10 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተፈጸመ ተገልጿል።

የድሮን ቦምቡ ያረፈው "በመኪናዎቹ ጋቢና" ላይ መሆኑን የሚናገሩት የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ፤ በዚህ ጥቃት አንድ አሽከርካሪ ሕይወቱ እንዳለፈ አስታውቀዋል። የተሽከርካሪው ረዳት የሆነ አንድ ግለሰብ ደግሞ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሆስፒታል መወሰዱን አስረድተዋል።

የፖሊስ አዛዡ እንደሚናገሩት ጥቃት የተፈጸመባቸው አይሱዙ እና ኤፍ.ኤስ.አር (FSR) የጭነት ተሽከርካሪዎች "የምግብ እና የንግድ ሸቀጦችን" የጫኑ ነበሩ።

የእንትጮ ከተማ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ጥቃቱን በተመለከተ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ "ከተሽከርካሪዎቹ አንዱ ሙዝ" ጭኖ እንደነበር ገልጿል። ሌላኛው መኪና የጫነው ደግሞ "ዘይት እና የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን" እንደሆነ ጽፏል።

የከተማዋ ኮሚዩኒኬሽን ፌስቡክ ላይ ባወጣው መረጃ ላይ የሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎችን ፎቶግራፍ አያይዟል።

ከጭነት መኪናዎቹ አንዱ በአሽከርካሪ መቀመጫ ጋቢናው ላይ ጉዳት ደርሶበት ይታያል። በሸራ ከተሸፈነው የተሽከርካሪው ጭነት ውስጥ የተወሰነው የተገለጠ ሲሆን የተገለጠው ክፍል ላይ ጥሬ ሙዝ ይታያል።

የድሮን ጥቃት የተፈጸመበት ተሽከርካሪ

የፎቶው ባለመብት, Enticho Town Communication

የምስሉ መግለጫ, በእንትጮ ከተማ የድሮን ጥቃት የተፈጸመበት ሌላኛው የጭነት ተሽከርካሪ ይህ እንደሆነ የከተማዋ ኮሚዩኒኬሽን ገልጿል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተሰራጨ አንድ ቪዲዮ ሰዎች ጥቃት ከደረሰበት ከዚህ መኪና አንድ ሰው በጨርቅ ሸፍነው ሲያወጡ እና መሬት ላይ ሲያስቀምጡ ይታያል። ሥፍራው ላይ የፖሊስ ደንብ ልብስ የለበሱ እንዲሁም መንገድ ዳር ተሰብስበው የሚመለከቱ ነዋሪዎች ይታያሉ። ይሁን እንጂ ቢቢሲ የዚህን ቪዲዮ ትክክለኛነት በገለልተኝነት አላረጋገጠም።

የእንትጮ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን የለጠፈው ሌላ ፎቶ ከመሃል ጀምሮ የጭነት ሸራው የተቀደደ ሌላ ተሽርካሪን የሚያሳይ ነው። በተቀደደው የሸራው ክፍል ላይ ካርቶኖች፣ ቢጫ የዘይት ጄሪካን እና በፕላስቲክ የታሸጉ መጠጥ መሰል ነገሮች አሉ። መሬት ላይ ደግሞ በፕላስቲክ የታሸገ ፈሳሽ ዘይት ተቀምጦ እና ወድቆ ይታያል።

በገንደበታ ከተማ የተፈጸመው ጥቃትም በተመሳሳይ ተሽከርካሪን ዒላማ ያደረገ እንደሆነ የፖሊስ አዛዡ እና ምንጮች ገልጸዋል። ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው ምንጮች እንደገለጹት ንጋት 11 ሰዓት ተኩል ገደማ ጥቃት የተፈጸመበት ተሽከርካሪ "በርበሬ እና ሌሎች የንግድ እቃዎችን" ጭኖ ነበር።

በገንደበታ ከተማ እና በአሕፈሮም ወረዳ በተፈጸሙት ጥቃቶች በሰው ላይ ጉዳት ስለመድረሱ አልታወቀም።

የእንትጮ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ "የድሮን ጥቃት በሌሎች አካባቢዎችም ሊደገም ስለሚችል፣ ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ" እንዲያደርግ አሳስቧል።

የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ ግጭት ውስጥ ገብተዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት መቀስቀሱን ትናንት አርብ ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።

በሁለት ዓመቱ ደም አፋሳሽ የትግራይ ጦርነት ወቅት በስፋት ጥቅም ላይ የዋለው የድሮን ጥቃት ድጋሚ በተቀሰቀሰው ግጭት ጥቃት ሲያደርስ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በዚህ ሳምንት የትግራይ ኃይሎች እና የፌደራል ኃይሎች ግጭት ውስጥ በገቡበት ጸለምት አካበቢ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።