የፈረንሳይ ፖሊስ ወደ ዩኬ እያመራች የነበረችን የስደተኞች ጀልባ በስለት ሲቀድ ቢቢሲ ተመለከተ

በስደተኞች የተጨናነቀችው በአየር መናኛ ጀልባ
የምስሉ መግለጫ, አንዲት ታዳጊ በስደተኞች በተጨናነቀችው በአየር ተሞላች ጀልባ ላይ ሆና ስታለቅስ ነበር።

የፈረንሳይ ፖሊስ በደቡብ ቦሎኝ የባሕር ዳርቻ ዘልቆ በመግባት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እያመራች የነበረችን በአየር የተሞላች የስደተኞች ጀልባ ስለት በመጠቀም ሲቀድ ቢቢሲ ተመለከተ።

በአደገኛ ሁኔታ ልትገለበጥ በነበረችው ጀልባ ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕጻናት ተሳፍረው ነበር።

በባሕር ዳርቻው ጀልባዋ ስደተኞችን እየጫነች በነበረችበት ወቅት በተፈጠረ ትርምስ መንቀሳቀስ አቅቷት የነበረ ሲሆን ቀድመው ተሳፍረው የነበሩት ለደኅንታቸው ሲሉ ጀልባዋን የሙጥኝ ብለው ነበር።

በዚህ ጊዜም ፖሊስ ባልተለመደ መልኩ ጣልቃ ገብቷል።

የፈረንሳይ ፖሊስ ብዙውን ጊዜ ሕይወትን ለመታደግ ካልሆነ በስተቀር ወደ ባሕር ዘልቆ መግባትን የሚከለክለውን ጥብቅ ሕግ ይከተላል።

በኢኳልት የባሕር ዳርቻ ሆኖ ክስተቱን የተመለከተው የቢቢሲ ዘጋቢ ስለክስተቱ ሲገልጽ፣ በሥፍራው የነበረ የፖሊስ መኮንን ትጥቁን ካወለቀ በኋላ ትንሽ ስለት በማውጣት ወደ ባሕሩ "እንግባ!" አለ፤ ከዚያም ባልደረቦቹ ከባድ ትጥቃቸውን በአቅራቢያቸው ባለ የፖሊስ መኪና ላይ ካስቀመጡ በኋላ ወደ ባሕሩ ተጣድፈው ገቡ ብሏል።

ይህ እምብዛም የማያጋጥም ክስተት የፈረንሳይ ፖሊስ ስደተኞች በመናኛ ጀልባዎች ወደ ዩኬ እንዳይገቡ ለማስቆም የሚጠቀመውን ስልት ለመቀየሩ ማስረጃ ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው ።

ሆኖም ፖሊስ የስደተኞችን ሕገ ወጥ ጉዞ ለማስቆም ምንም ዓይነት ሌላ ዘዴ እየተጠቀመ እንዳልሆነ ለቢቢሲ ገልጿል።

ስደተኞችን ለማስቆም ወደ ባሕር ዘልቆ መግባት የሚከለክለው ሕግ አሁንም ሥራ ላይ እንዳለ እና ፖሊሶች በባሕር ዳርቻዎች ላይ በሚወስዱት እርምጃ ለደኅንነት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸው አስረድቷል።

ጣልቃ መግባት የሚፈቀድላቸውም ክስተቱ ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ካመኑ ብቻ ነው።

ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፈረንሳይ ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት አሁን ተግባራዊ ለማድረግ እየታሰበ ያለው የአሰራር ለውጥ፣ፖሊስ በባሕር ዳርቻዎች ላይ ከሚወስዳቸው ኃይል የተቀላቀለባቸው ጣልቃ ገብነት ይልቅ፣አነስተኛ ጀልባዎቹ ስደተኞችን ከመጫናቸው በፊት ለመያዝ የባሕር ላይ የጥበቃ ጀልባዎችን መጠቀም ላይ የሚያተኩር ነው።

ክስተቱን ተከትሎ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ፣ የፈረንሳይ ፖሊስ የስደተኞችን ጀልባ ሲያወድም የሚያሳየው ምስል "ወሳኝ" እንደሆነ ገልጸው፣ እርምጃውን እንደሚደግፉት ገልጸዋል።

" ከባድ እርምጃ ሲወሰድ ማየት እንፈልጋለን። ይህ የሥራችን ዋና ትኩረት ነው። ያያችሁትም በቅርበት የመሥራታችን ውጤት ነው" ብለዋል።

ከባሕር ዳርቻው በጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ የነበረችው ጀልባ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደነበረች ግልጽ ነው። ጠፍቶ እንደገና ከተነሳው የጀልባዋ የውጭ ሞተር ላይ ሳይቀር ሰዎች ተሳፍረው ነበር።

ጀልባዋ በባሕሩ ማዕበል ምክንያት እንቅስቃሴዋን መቆጣጠር ተስኗት ወዲያ ወዲህ ስትላጋ፤ በመገልበጥ አደጋ ውስጥ የነበሩ በርካታ ሕጻናት ከፍተኛ ጩኸት ሲያሰሙ ነበር።

ቢለዋ የያዘ የፈረንሳይ ፖሊስ ጀልባዋ አቅራቢያ
የምስሉ መግለጫ, የፈረንሳይ ፖሊስ በኢንግሊሽ ቻነል ላይ ስትጓዝ የነበረች በአየር የተሞላች የስደተኞች ጀልባን ለመቅደድ ቢላ ተጠቅሟል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቀደም ብሎ ብርቱካናማ ቀለም ያለው የደኅንነት ጃኬት የለበሱ በርካታ ሰዎች በሁለት ቡድን ሆነው በአቅራቢያ ካለ የባሕር ዳርቻ ወጥተው ተጣድፈው ወደ ባሕሩ ገቡ። ቁጥራቸው 80 ወይም 100 ሊሆን ይችላል።

ከዚያም ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ከተለያዩ የፈረንሳይ የባሕር ዳርቻዎች ስደተኞችን ለመሰብሰብ የሚጠቀሙበት የመጀመሪያው ጀልባ ከባሕር ዳርቻው በ100 ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ በፍጥነት አለፈ። ጀልባው ሞልቶ ስለነበር ለመጫን አልቆመም ነበር።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ምንም ተሳፋሪ ያልያዘች ሁለተኛዋ ጀልባ የፈረንሳይ የባሕር ዳርቻ ጠባቂዎች እየተመለከቷት ወደ ባሕር ዳርቻው መጣች።መሪ በሚመስል አንድ ግለሰብ እየተመሩ በቡድን በቡድን የሆኑና እጅ ለእጅ የተያያዙ ሰዎች ከፊት ቀድመው ሄደዋል።

በአየር የምትሞላው ትንሽ ጀልባ ፊቷን አዙራ ወደ ባሕር ዳርቻው ተጠጋች።ቀድመው የሄዱት ስደተኞች እስከ ወገብ ድረስ በሚያጠልቀው ባሕር እየገቡ ለመሳፈር ሲሞክሩ ትርምስ ተፈጠረ።

መጀመሪያ ላይ ይህንን የተመለከቱ የፈረንሳይ ፖሊሶች ጣልቃ ለመግባት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ዳርቻው ላይ ቆመው እየተመለከቱ ነበር።

አንድ የፖሊስ መኮንን የሰዎችን ነፍስ ለመታደግ ካልሆነ በስተቀር ወደ ውሃው መግባት ክልክል መሆኑን ሲገልጽ ነበር።

በሥፍራው ትርምስ ሲፈጠር በሥፍራው የነበሩ የፖሊስ መኮንኖች መስመር እንደታለፈና የተሳፈሩት ሰዎች ለአደጋ እንደተጋለጡ ስለተሰማቸው "ለደኅንነታቸው" ሲሉ ጀልባዋ እንዳትንቀሳቀስ ለማድረግ እድል አግኝተዋል።

በዚህ ወቅት አዘዋዋሪዎቹ የጀልባዋን ሞተር እንደገና ለማስነሳት በሚያደርጉት ሙከራ ሃሳባቸው ተሰርቆ ነበር።

ፖሊሱ በተደጋጋሚ ጀልባዋን በስለት ሲወጋ ተሳፍረው የነበሩ ሰዎች ለቅሶ፣ ቁጣ፣ ጩኸት እና የጭንቀት ድምጽ ሲያሰሙ ነበር።

መሃል ላይ ተቀምጣ የነበረች አንዲት ታዳጊም ሌሎች ወደ ጀልባ ሲንጠላጠሉ ተገፍታ ለደኅንነቷ አስጊ በሆነ የጀልባዋ የኋላ ሞተር ተጠግታ ነበር።

ከትንሽ ቆይታ በኋላም ጀልባዋ በፖሊሶች ተጎትታ ወደ ባሕር ዳርቻው ወጣች።

ስደተኞቹም በባሕር ዳርቻው ላይ የወዳደቁ ቁሳቁሶቻቸውን ሰብስበው በአቅራቢያ ወዳለች መንደር በእግራቸው ከሄዱ በኋላ በአውቶብስ ተሳፍረው ወደ ሰሜን አቅጣጫ ወደ ስደተኞች ካምፕ ተመለሱ።