አወዛጋቢው አሜሪካ መር የእርዳታ ተቋም በጋዛ ሥራውን አቆመ

ጋዛ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ እና እስራኤል የሚመሩት አወዛጋቢው የጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ተቋም ሥራ ማቆሙን ገለጸ።

ላለፉት ስድስት ወራት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ጂኤችኤፍ የተባለው የእርዳታ ተቋም በርካታ ጥያቄዎች ይነሱበት ነበር።

እስራኤል እና ሐማስ ተኩስ አቁም ለማድረግ ከተስማሙ በኋላ በጋዛ በሦስት እርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ሥራውን አቁሟል።

የተባበሩት መንግሥታት በዋነኛነት በጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ያቀርብ የነበረ ሲሆን፤ ጂኤችኤፍ ሥራ ሲጀምር ተመድ እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ተቃውሞ አሰምተዋል።

ተቋሙ ከሙያዊ ሥነ ምግባር ያፈነገጠ እንዲሁም ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ነው ሲሉም ተችተዋል።

በጂኤችኤፍ የእርዳታ ጣቢያዎች አቅራቢያ ሰብአዊ እርዳታ ሲጠባበቁ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። አብዛኞቹ የተገደሉት ከእስራኤል ወታደሮች በተተኮሰ የማስጠንቀቂያ ጥይት እንደሆነ ተመድ ይፋ አድርጓል።

ተቋሙ "አስቸኳይ እርዳታ የመስጠት ኃላፊነቱን በመወጣቱ" ሥራውን እንዳቆመ ገልጿል።

187 ሚሊዮን የምግብ አቅርቦቶችን የያዙ ሦስት ሚሊዮን ጥቅሎችን ለፍልስጤማውያን ማከፋፈሉን ይፋ አድርጓል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተቋሙ ዋና ኃላፊ ጆን አክር እንዳሉት፤ የተቋሙ አሠራር የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን የጋዛ የሰላም ዕቅድ በሚያስተገብረው ጥምረት የሚተካ ይሆናል።

አሜሪካ መራሹ የሲቪል እና ወታደራዊ ኃይሎች ጥምረት (CMCC) የጋዛን የሰላም ዕቅድ ለማስተግበር የተሠማራ ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ ቶሚ ፒጎት "የጂኤችኤፍ አሠራር ሐማስ እርዳታ ዘርፎ እንዳይጠቀም በማገድ ለተኩስ አቁም ስምምነቱ ከፍተኛ ሚና ነበረው" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

ሰብአዊ እርዳታ አለመስረቁን የገለጸው ሐማስ፤ ጂኤችኤፍ መዘጋቱን እንደሚደግፍ አስታውቋል። ተቋሙ በፍልስጤም ሕዝብ ላይ ላደረሰው ጉዳት ተጠያቂ እንዲሆንም ጠይቋል።

የሐማስ ቃል አቀባይ ሐዜም ቃሲም "ተቋሙ ከተጠያቂነት እንዳያመልጥ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲረባረቡ እንጠይቃለን። በሺዎች የሚቆጠሩ በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን እንዲሞቱ እንዲሁም የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው አድርጓል። የጋዛን ረሃብም ደብቋል" ሲሉ በቴሌግራም ገጻቸው ጽፈዋል።

ጂኤችኤፍ ሥራ የጀመረው እስራኤል ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ እንዳይገባ እገዳ በጣለች ማግሥት እአአ ግንቦት 2025 ነው።

ለ11 ሳምንታት ወደ ጋዛ መሠረታዊ እርዳታ ሳይገባ በመቅረቱ ከሦስት ወራት በኋላ ረሃብ ተከስቷል።

በደቡብ እና ማዕከላዊ ጋዛ የነበሩትን የጂኤችኤፍ እርዳታ ጣቢያዎች እንዲጠብቁ የአሜሪካ የግል ደኅንነት ጥበቃ ቅጥረኞች ተሰማርተዋል።

ተመድ የሚሠራው ነጻ እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንደሆነ ገልጾ፤ አሜሪካ መሩ ተቋም ግን በወታደራዊ ቀጣናዎች እርዳታ በማቅረብ ሰዎችን ለአደጋ እንዳጋለጠ አስታውቋል።

እአአ በ2025 ከግንቦት 26 እስከ ሐምሌ 31 ድረስ በጂኤችኤፍ ጣቢያዎች ቢያንስ 859 ፍልስጤማውያን ሰብአዊ እርዳታ ሲጠባበቁ መገደላቸውን ተመድ መዝግቧል።

ወደ ተመድ እና ሌሎችም እርዳታ ሰጪዎች ሲጓዙ የነበሩ 514 ፍልስጤማውያንም በእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል።

የእስራኤል መከላከያ እንደሚለው፤ ወታደሮቹ የሚተኩሱት "ማስጠንቀቂያ ለመስጠት" ነው።

ጂኤችኤፍ በጣቢያዎቹ አቅራቢያ ምንም ተኩስ እንዳልነበረ ገልጾ፤ ተመድ "ሐሰተኛ እና አሳሳች መረጃ" ያገኘው "በሐማስ ከሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር" መሆኑን ጠቅሷል።

የእርዳታ ተቋሙ የወደፊት እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ግልጽ አይደለም።

እርዳታ የማከፋፈል ኃላፊነቱ ከሐማስም ይሁን ከእስራኤል ጋር ትስስር ለሌላቸው ተመድ፣ ቀይ ጨረቃ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋሞች እንደሚሰጥ ገልጿል።

የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ "ቀድሞውንም አብረናቸው እየሠራን ስላልነበር አሁን ሥራ ማቆማቸው በእኛ ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም" ብለዋል።

ከተኩስ አቁሙ በኋላ ወደ ጋዛ የሚገባው ሰብአዊ እርዳታ መጠን ቢጨምርም፤ የ2.1 ሚሊዮን ፍልስጤማውያንን ፍላጎት ማሟላት እንደማይችል አክለዋል።