የዓለም አንጋፋው የማራቶን ሯጭ በ114 ዓመታቸው በመኪና አደጋ ህይወታቸው አለፈ

ፋውጃ ሲንግ ባለፈው ሰኔ ቢቢሲ ፑንጃቢ ጋር ቆይታ ባደረጎበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Pardeep Sharma/BBC

የዓለማችን በዕድሜ ትልቁ የማራቶን ሯጭ እንደሆኑ የሚነገርላቸው እንግሊዛዊ ህንዳዊ ፋውጃ ሲንግ በህንድ በ114 ዓመታቸው በመኪና አደጋ ህይወታቸው አለፈ።

ፖሊስ ሲንግ በተወለዱበት ፑንጃብ መንደር ውስጥ መንገድ እያቋረጡ ሳለ ማንነቱ ያልታወቀ ተሽከርካሪ እንደገጫቸው አስታውቋል።

ከአደጋው በኋላ የአካባቢው ሰዎች ህይወታቸው ወዳለፈበት ሆስፒታል ወስደዋቸዋል።

አለም አቀፋዊ ተምሳሌት የሆኑት ሲንግ እድሜያቸው ከ100 ተሻግሮም ጭምር በተለያዩ የእድሜ ምድቦች በመሮጥ ክብረ ወሰንን አስመዝግበዋል። በ89 ዓመታቸው መሮጥ የጀመሩት ሲንግ እ.አ.አ ከ2000 እና 2013 ዘጠኝ የሙሉ ማራቶን ሩጫው ላይ ተሳትፈዋል።

የእሳቸው የሩጫ ክለብ እና የበጎ አድራጎት ድርጅት 'ሲክስ ኢን ዘ ሲቲ' ከ1992 ጀምሮ በኖሩበት እና በምስራቃዊ ለንደን በሚገኘው በኢልፎርድ የሚያደርጋቸው ዝግጅቶች የሲንግን ህይወት እና ስኬቶች የሚዘከሩበት ይሆናል ብሏል።

አዛውንቱ ፋውጁ ሲንግ አደጋው የተከሰተው በተወለዱበት እና በጃላንድሃር አቅራቢያ በሚገነው ቢያስ ፒንድ መንደር እየተራመዱ ሳለ ነው።

የዲስትሪክቱ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን ሃርቪንደር ሲንግ "አሰሳ እየተካሄደ ነው፣ እናም ተከሳሹ በቅርቡ ይያዛል" ብለዋል።

የሞታቸው ዜና እንደተሰማ፣ ሲንግ የአድናቆት መልዕክቶች እየጎረፉ ይገኛሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ "ቆራጥነት እና ልዩ አትሌት"ብለዋቸዋል።

በሲክስ ኢን ዘ ሲቲ የፋውጃ ሲንግ አሰልጣኝ ሃርማንደር ሲንግ በሩጫው ክለብ ላይ በለጠፉት መግለጫ መሞታቸውን አረጋግጠዋል።

መግለጫው "የእኛን የሰብአዊነት አምድ እና እና የአዎንታዊነት ሃይል ፋውጃ ሲንግ በህንድ ውስጥ መሞቱን ስንገልጽ በታላቅ ሀዘን ነው። የእርሱ የሩጫ ክለብ እና በጎ አድራጎት ሲክስ ኢን ዘ ሲቲ እሑድ መጋቢት 29 ቀን 2026 እስከሚውለው የፋውጃ ሲንግ የልደት ድረስ ያሉ ዝግጅቶቹን በሙሉ የስታቸውን እና ህይወታቸውን ለማክበር ይውላሉ" ብሏል።

ቢቢሲ በሰኔ ወር ቢያስ ፒንድ ውስጥ ከሲንግ ጋር ሲገናኝ፣ ቀልጣፋ እና ንቁ ነበሩ፣ በየቀኑ ብዙ ማይሎች ይራመድ ነበር።

"እግሬን ጠንካራ ለማድረግ አሁንም መንደሩ ውስጥ እዟዟራለሁ ሰው የራሱን አካል መንከባከብ አለበት" ብለው ነበር።

እ.ኤ.አ. በ2012 የለንደን ኦሊምፒክ ችቦ ተሸካሚው ሲንግ በሩጫ ህይወታቸው በርካታ ክንዋኔዎችን ያስመዘገቡ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2011 በቶሮንቶ ሙሉ ማራቶንን ያጠናቀቁ የመጀመሪያው መቶ አመት ሯጭ መሆናቸው ተዘግቧል።

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 1911 መወለዳቸውን የሚያሳይ የልደት ሰርተፍኬት ማቅረብ ባለማቻላቸው የዓለማችን በዕድሜ ትልቁ ሯጭ መሆናቸው በጊነስ ወርልድ ሪከርድስ እውቅና አላገኘም።

ቢቢሲ በወቅቱ የሲንግ የብሪታኒያ ፓስፖርት የልደት ቀናቸው ሚያዝያ 1/ 1911 መሆኑን እንደሚያሳይ እና ንግስቲቱ 100ኛ የልደት በዓላቸውን አስመልክቶ እንኳን ደስ ያለዎት ደብዳቤ እንዳላቸው በወቅቱ ዘግቧል።

የእሳቸው አሰልጣኝ ሃርማንደር ሲንግ ሲንግ በተወለዱበት ጊዜ በህንድ የልደት የምስክር ወረቀቶች እንዳልነበሩ ተናግረዋል።

የጊነስ ወርልድ ሪከርድስ ባለሥልጣኖች "ሪከርዱን ቢሰጡት ደስ ይላቸው ነበር" ነገር ግን "በተወለዱበት ዓመት የተሰራ ይፋዊ የልደት ሰነዶችን ብቻ እንደሚቀበሉ" ተናግረዋል።

በፑንጃብ ያደጉት ብላቴናው ሲንግ እግሮቻቸው ደካማ ስለነበሩ እና እስከ አምስት ዓመታቸው ድረስ በትክክል መራመድ ስለማይችሉ በመንደራቸው ውስጥ ባሉ ሰዎች ይሳለቁባቸው ነበር።

"ነገር ግን በአንድ ወቅት በድክመቱ ምክንያት ስላቅ የደረሰበትያው ልጅ፤ ታሪክ ሰርቷል" ሲሉ በሰኔ ወር ለቢቢሲ ፑንጃቢ ተናግረው ነበር።

ሲንግ ለቢቢሲ ፑንጃቢ እንደተናገሩት "በወጣትነቴ 'ማራቶን' የሚለው ቃል መኖሩን እንኳ አላውቅም ነበር። "ትምህርት ቤት አልሄድኩም በማንኛውም አይነት ስፖርትም አልተሳተፍኩም። ገበሬ ነበርኩ እና አብዛኛውን ሕይወቴን ያሳለፍኩት በእርሻ ማሳ ውስጥ ነው።"

መጀመሪያ ወደ ሩጫ የገቡት ሀዘንን ለመቋቋም ነበር።

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ባለቤታቸው ጂያን ካውር ከሞተች በኋላ ከበኩር ልጃቸው ሱክጂንደር ጋር ለመኖር ወደ ለንደን አመሩ። ነገር ግን ወደ ህንድ ለጉብኝት ባቀኑበት ወቅት ታናሽ ወንድ ልጃቸው ኩልዲፕ በድንገተኛ አደጋ መሞቱ ከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ከትቷቸዋል።

ሲንግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩጫ ላይ የተሳተፉት 89 ዓመት ሊሞላቸው አንድ ወር ሲቀራቸው በለንደን ማራቶን እ.አ.አ በ2000 ነበር።

ሲንግ ከሩጫው በፊት የተርባን ጥምጣም ሳይሆን ፓትካ (ብዙ የሲክ ወንዶች እና ወንዶች የሚለብሱት የራስ መጎናጸፊያ) ብቻ እንደሚለብሱ በኹነቱ አዘጋጆች እንደነተነገራቸው ተናግረዋል።

"ጥምጥሜን ሳልይዝ ለመሮጥ ፈቃደኛ አልነበርኩም። በመጨረሻ አዘጋጆቹ አብሬው እንድሮጥ ፈቀዱልኝ፣ ለእኔ ትልቅ ስኬቴ ነው" ብለዋል።

ውድድሩን በስድስት ሰአት ከ54 ደቂቃ በማጠናቀቅ የአስደናቂው ጉዟቸው ጅማሮ ሆኗል።

በለንደን ማራቶን ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ በተሳተፉበት ወቅት ከቀድሞ ምርጡ ብቃቱን በ9 ደቂቃዎች አሻሽለዋል።

እ.ኤ.አ. በ2003 በቶሮንቶ ዋተርፍሮንት ማራቶን በአስደናቂ ሁኔታ በአንድ ሰአት ከአምስት ደቂቃ በማሻሻል ውድድሩን በአምስት ሰአት ከ40 ደቂቃ አጠናቅቀዋል።

ጤናማናታቸው እና ረዥም ዕድሜ መኖራቸው የቀላል የአኗኗር ዘይቤ እና ሥርዓት የተሞላ አመጋገብ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

"ትንሽ መብላት፣ ብዙ መሮጥ እና ደስተኛ ሆኜ መቆየቴ - ይህ ነው ረጅም ዕድሜ ከመኖሬ በስተጀርባ ያለው ሚስጥር። ይህ ለሁሉም ሰው የማስተላልፈው መልእክት ነው" ሲሉ በሰኔ ወር ተናግረዋል።

በመጨረሻዎቹ ዓመታት ሲንግ ጊዜያቸውን ያሳለፉት በህንድ እና በእንግሊዝ ነው።