የወታደር ልብስ የለበሱ የአልሸባብ ታጣቂዎች የሶማሊያ እስር ቤትን አጠቁ

ቅዳሜ ዕለት በሶማሊያ ፕሬዚዳንት ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ጭስ ታይቷል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ቅዳሜ ዕለት በሶማሊያ ፕሬዚዳንት ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ጭስ ታይቷል

ሰባት የአል ሻባብ ታጣቂዎች በሶማሊያ ዋና ከተማ የሚገኝ እና ጥብቅ ጥበቃ የሚደረግለት እስር ቤት ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ መገደላቸውን የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።

ቅዳሜ ማታ የአልሸባብ ታጣቂዎች ታስረውበት በሚገኘው ጎድካ ጂሊኮው ተብሎ የሚጠራው ማረሚያ ቤት ከሚገኝበት አካባቢ ከፍተኛ የፍንዳታ እና የተኩስ ድምጽ ተሰምቶ ነበር።

አል ሻባብ ባወጣው መግለጫ በማረሚያ ቤቱ ታስረው የነበሩ "ሁሉንም ሙስሊም እስረኞች" ማስለቀቀቁን እና ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጿል።

በመንግሥት የሚተዳደረው ሶና የዜና ወኪል በበኩሉ እሁድ እለት እንደዘገበው ታጣቂዎቹ ወደ ማረሚያ ቤቱ ለመግባት የአገሪቱን ወታደር የደንብ ልብስ ለብሰው እንደነበር ገልጿል።

መንግሥት ምን ያህል የፀጥታ አባላት እንደተገደሉበት ያልገለፀ ቢሆንም "ለተሰዉ ጀግኖች" ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል።

አልሸባብም እንዲሁ ምን ያህል አባላቱ እንደ ሞቱ ይፋ አላደረገም።

የአልሸባብ ታጣቂዎች ጥቃቱን የፈጸሙት ቅዳሜ ከሰዓት 10፡40 ላይ ነበር።

ጉድካ ጂሊኮው በሞቃዲሾ በሶማሊያ ፕሬዚዳንት ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የሚገኝ ማረሚያ ቤት ነው።

ጥበቃ የሚደረግለት በሶማሊያ ብሔራዊ ፀጥታ እና ደህንነት ኤጀንሲ ሲሆን የአልሸባብ ተዋጊዎችን እና ሌሎች ከፍተኛ ስም ያላቸውን እስረኞችን ይዟል።

ጥቃቱ ለሶማሊያ ደህንነት ከፍተኛ ኪሳራ ነው የተባለ ሲሆን ታጣቂዎቹ በዋና ከተማዋ ከፍተኛ ጥበቃ ወደ ሚደረግበት አካባቢ እንዴት ሊገቡ ቻሉ የሚል ጥያቄ አስነስቷል።

አል ሻባብ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው ሲሆን ላለፉት 20 ዓመታት የሶማሊያ መንግሥት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶቸን ሲሰነዝር ቆይቷል።

ከቅዳሜው ጥቃት ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ በሞቃዲሾ ከዚህ ቀደም በደህንነት ምክንያት ተዘግቶ የነበረ ዋና መንገድ የደህንነት መሻሻል ታይቷል በሚል ተከፍቶ ነበር።