ሕይወትን የሚያመሰቃቅል ጭንቀት ምንድን ነው? ምን ብናደርግ መፍትሔ እናገኛለን?

ጭንቅላቷን ይዛ አንድ ነገር ላይ ያተኮረች የተጨነቀች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጭንቀት በማንኛውም ሰው ላይ የሚከሰት የስሜት ዓይነት ነው። አስፈሪ ወይም ፈታኝ ነገር ሲገጥም መጨነቅ ተፈጥሯዊም ነው።

ጭንቀት አደገኛ የሚሆነው መጠኑን ሲያልፍ ነው። መቆጣጠር የማይቻል ጭንቀት (anxiety) ሕይወትን ፈታኝ ያደርጋል።

ጭንቀት የሰዎችን አጠቃላይ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴን በማወክ የሚፈልጉትን ስኬት እንዳያገኙ በማድረግ ሕይወታቸው ላይ ተጽእኖ ያሳድራል።

በተጨማሪም ጭንቀት አካላዊ እና አእምሯዊ ጤና ላይ ችግሮችን ያስከትላል።

ጭንቀት ምንድን ነው? ለምንና እንዴት ይከሰታል? በምን መንገድስ መከላከል ይቻላል? የሚሉትን ነጥቦች በዚህ ዘገባ እንመለከታለን።

ጭንቀት ምንድን ነው?

ከፍርሃት ወይም ከስጋት የሚመነጭ ስሜት ጭንቀት ይባላል። ይህም አደጋ ሊከሰት ነው ብሎ መስጋት ወይም በአካባቢ ያለን ነገር ሁሉ በጥርጣሬ መመልከትን ያካትታል።

በቬትናም እና በአሜሪካ የሠሩት የሥነ ልቦና ባለሙያ ፎውንግ ሊ እንደሚሉት፣ ጭንቀት መጠኑን ሲያልፍ አካላዊ ሕመም ምልክቱ ይሆናል። የአእምሮ እረፍት ስለሚነሳ መፍትሔም ያሻዋል።

ለወደፊት ሊመጣ የሚችል አደጋን ለመከላከል የሚያስችል መጠነኛ ጭንቀት ጤናማ ቢሆንም ምክንያታዊ ያልሆነ እና እውነታ ላይ ያልተመሠረተ ጭንቀት ከሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ይመደባል።

ተመሳሳይ ስሜት ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር መወያየት አንዱ መፍትሔ ነው።

የጭንቀትና ፍርሃት ልዩነት ምንድን ነው?

የሥራ ጫና ወይም የቤተሰብ ጉዳይ የሚፈጥረው ጤናማ ጭንቀት እንዳለ ሆኖ፣ ከመጠን ባለፈ ፍርሃት ምክንያት ውስጣዊ ሰላም የሚያሳጣ ጭንቀትም ሰዎች ይገጥማቸዋል።

ዘለግ ላለ ጊዜ ሲቆይ ሕይወትን ያመሰቃቅላል።

"በተወሰነ ጊዜ ውስጥ መጠኑን ያለፈ ጭንቀት ሲገጥም በአእምሮ ውስጥ መልዕክት የሚዘዋወርበትን ሥርዓት ያዛባል። ስሜትን የሚቆጣጠረውን የአእምሮ ክፍል ያውካል። ለጤና እክልም ያጋልጣል" ይላሉ ባለሙያው።

የዕለት ከዕለት ሕይወት ጭንቀትን ሊያባብስ ይችላል። ሌሎች ጭንቀትን የሚያባብሱ የሕይወት አጋጣሚዎችም ይጠቀሳሉ።

ባለሙያው እንደሚሉት፣ ጭንቀትን መቆጣጠር አስፈላጊ ነው።

የተመስጦ (ሜዲቴት) ስፖርት የሚሠሩ በዕድሜ የገፉ ሴቶች እና ወንዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጭንቀት ሰውነትን እንዴት ይጎዳል?

ቀጣይነት ያለው ጭንቀት ጤናን ያቃውሳል። ከልብ ሕመም፣ ከደም ግፊት፣ ከስትሮክ እና ሌሎችም ሕመሞች ጋርም ቀጥተኛ ትስስር አለው።

አልሰር፣ ተቅማጥ እና ሌሎችም ሕመሞች ከጭንቀት ጋር ይገናኛሉ። ጭንቀት የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅምም ያዳክማል።

በጭንቀት ምክንያት ለተለያዩ ሕመሞች መጋለጥ ለተጨማሪ ጭንቀት ይዳርጋል።

በጭንቀት ወቅት ራስ ምታት እና ሌሎችም ምልክቶች ይታያሉ።

ጭንቀት ለሌሎች የአእምሮ ሕመሞች እንደሚያጋልጥም ባለሙያዎች ይናገራሉ።

መጠኑን ያለፈ ጭንቀት የሰው ለሰው ግንኙነትን፣ ሥራን እንዲሁም አጠቃላይ ሕይወትን የሚፈትን ሲሆን፣ ራስን እስከማጥፋት የሚደርስባቸው ሁኔታዎችም አሉ።

ጭንቀትን እንዴት መከላከል ይቻላል?

ጭንቀትን ለመከላከል የተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ ይውላሉ። የተወሰኑትን እንመልከት።

  • አሁን ላይ መሆን - Mindfulness በመባል የሚታወቀው መንገድ የአእምሮን ትኩረት ወደ ኋላም ወደ ፊትም ሳይወስዱ አሁን ላይ ማተኮርን ያበረታታል። አተነፋፈስን ማስተካከል እና ሰውነትን ማዝናናት ለዚህ ይረዳል። የሰውነትን የጭንቀት መጠን ለመቀነስም ያግዛል።
  • መተንፈስ - ትክክለኛ የሆነ አተነፋፈስ የአእምሮ እና የተቀረውን ሰውነት ጤና ያስተካክላል። በአግባቡ እና በጥልቅ ለመተንፈስ መቸገር አንድ የጭንቀት ምልክት ነው።
  • የጭንቀት ጊዜ መመደብ - በሁሉም ሰዓት ጭንቀት ውስጥ ከመሆን ይልቅ የሚያስጨንቁ ነገሮችን ለማሰላሰል ጊዜ መመደብ የሚመርጡ ሰዎች አሉ። የሚያስጨንቃቸውን ነገር በመጻፍ ለጭንቀት የሚያጋልጣቸውን ነገር ለማስወግድም ይሞክራሉ።
  • ማውራት - ከጓደኛ፣ ከቤተሰብ ወይም ከሥነ ልቦና ባለሙያ ጋር ማውራት አንድ ጭንቀትን ማስወገጃ መንገድ ነው። ተመሳሳይ ችግር ከገጠማቸው ሰዎች ጋር መደጋገፊያ ማኅበር መመሥረት እና የሚያዝናኑ ነገሮችን መከወንም ያግዛሉ።
የተጨነቀች የምትመስል ሴት እያማከራቻት ካለች ሴት ፊት ለፊት ተቀምጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሥነ ልቦና ድጋፍ

የተለያዩ ዓይነት የሥነ ልቦና ድጋፍ መስጫ መንገዶች አሉ። Cognitive Behavioural Therapy ወይም CBT በመባል የሚታወቀው መንገድ ጭንቀትን የሚያስከትል አስተሳሰብን በመቆጣጠር ጭንቀትን ለማስወገድ የሚሞከርበት ነው።

አሉታዊ ስሜት ሲፈጠር ለምን ተፈጠረ? ብሎ በመፈተሽ ምን ያህል ትክክለኛ ስሜት እንደሆነ በመመዘን ለማስወገድ መሞከርን ያካትታል።

ስሜትን ከውጭ ወደ ውስጥ ለመቃኘት በመሞከር ምን ያህል ትክክል ነው ብሎ ራስን መመልከትም ሌላው መንገድ ነው።

የሥነ ልቦና ድጋፍ ውስጥ ከሚካተቱ መንገዶች መካከል Behavioural activation የሚባለው ይገኝበታል።

ስሜትን የተመጣጠነ ለማድረግ እና ጭንቀትን ለማስወገድ አሉታዊ ስሜትን ቅድሚያ መስጠትን ያካትታል።

ጭንቀትን በመጋፈጥ ስሜትን ለመቆጣጠርም በዚህ የሥነ ልቦና ሕክምና ይከናወናል።

አእምሮን ከጭንቀት ለማውጣት እና ሰውነትን ለማዝናናት የተለያዩ መንገዶች አሉ።

አስጨናቂ ስሜትን መጻፍ፣ የሚያስጨንቁ ሐሳቦችን ለይቶ ለማወቅ ይረዳል።

ሌላው የሥነ ልቦና ሕክምና Cognitive restructuring ይባላል። ይህም አሉታዊ ስሜትን ነቅሶ በማውጣት እነዚህን ስሜቶች በአሉታዊ መንገድ ከመመልከት ይልቅ ወደ አወንታዊ አመለካከት መውሰድ ማለት ነው።

በክብ ቅርጽ ተቀምጠው እጅ ለእጅ የተያያዙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጭንቀት መድኃኒቶች

ስሜትን የሚቆጣጠረውን የሆርሞን ዓይነት (serotonin) ለማስተካከል የሚሰጡ የመድኃኒት ዓይነቶች አሉ።

በብዛት የሚታወቀው ሉስትራል መድኃኒት ወይም SSRI የተባሉ መድኃኒቶች ውስጥ ይካተታል።

እንደ ፕሮዛክ ያሉ የሲሮቶኒን ሆርሞንን የሚያስተካከሉ መድኃኒቶችም ይጠቀሳሉ።

የሲሮቶኒን መጠን አነስተኛ ሲሆን፣ ጭንቀት እና ድባቴን ያስከትላል።

መድኃኒቶቹ አእምሯችን ይሄንን ሆርሞን አመንጭቶ በፍጥነት እንዳያከስመው በማድረግ ጭንቀትን ይቀንሳሉ ወይም የተዛባ ስሜትን ያስተካክላሉ።

የሥነ ልቦና ባለሙያው ፎውንግ ሊ እንደሚሉት፣ መድኃኒት ከሥነ ልቦና ድጋፍ ጋር ነው መወሰድ ያለበት።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እና አመጋገብን ማስተካከልም ይመከራል።

"መድኃኒት ያስፈልጋል የሚለውን መወሰን ያለባቸው የሕክምና ባለሙያዎች ናቸው። የጎንዮሽ ጉዳቱ ታውቆ ለየትኛው ሰው የትኛው መድኃኒት ይሠራል የሚለው ይወሰናል" ሲሉ ያስረዳሉ።

ስፖርት ሰርቶ በፊቱ ላይ ላብ የሚታይ ሰማያዊ ሹራብ የለበሰ ወንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስለ ጭንቀት የተዛቡ አመለካከቶች

ባለሙያው እንደሚሉት በተለይ በወጣቶች ዘንድ ጭንቀት ደካማ እንደመሆን ይቆጠራል።

ስለ ጭንቀት ያለው አመለካከት እየተለወጠ መምጣቱ ሰዎች ወደ ሕክምና እንዲሄዱ እያበረታታ ነው።

ካለፉት ዓመታት በተሻለ ወጣቶች ጭንቀት ሲገጥማቸው እርዳታ እየጠየቁ ነው።

ስለ ጭንቀት ከሚሰሙ የተዛቡ ምልከታዎች መካከል፣ ጭንቀት ነገሮችን ማጋነን ነው ብሎ መውሰድ ነው።

"ጭንቀት ከባድ ሕመም ነው። ጊዜያዊ ጭንቀት ተብሎ የሚታለፍ አይደለም። በአእምሮ ውቅር ላይ ለውጥ የሚያመጣ እክል ነው" ይላሉ የሥነ ልቦና ባለሙያው።

የሚጨነቁ ሰዎች ደካማ ናቸው የሚለው ሌላው የተዛባ ምልከታ ነው። ጭንቀት አካላዊ፣ አካባቢያዊ እንዲሁም ከዘረ መል ጋር የሚገናኙ ምክንያቶች አሉት።

ጭንቀት በራሱ ሰዓት የሚጠፋ ነገር ነው ብሎ ችላ ማለት እንደማይገባ የሥነ ልቦና ባለሙያው ፎውንግ ሊ ያስጠነቅቃሉ።

ስሜቱን ችላ ከማለት ይልቅ ለምን እንደተከሰተ መረዳት እና መፍትሔ መስጠት ይመከራል።

"ጭንቀት ያለ ሕክምና እየተባባሰ ይሄዳል። መድኃኒት ብቻ ነው መፍትሔው ማለት ሳይሆን፣ በተለያዩ መንገዶች ጭንቀትን ማከም ይቻላል" ሲሉ ያስረዳሉ።

አኗኗርን መለወጥ አንዱ የጭንቀት መፍትሔ ነው።

ከሚያማክረው ሰው ፊት ለፊት የተቀመጠ የተጨነቀ የሚመስል ወንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስለ ጭንቀት ማውራት ጭንቀትን ያባብሳል የሚለው ሌላኛው የተዛባ አመለካከት ነው።

ስለ ጭንቀት ማውራት ስሜቱን የሚያቃልል እና ወደ መፍትሔ የሚወስድም ነው።

ጭንቀት ብዙዎች የሚገጥማቸው አይደለም ብለው የሚያምኑ ቢኖሩም ጭንቀት ከአእምሮ ጤና እክሎች መካከል በርካቶች ላይ የሚከሰት ነው።

ጭንቀት ሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ የስሜት ለውጥ እንደሆነ ባለሙያው ያስረዳሉ።

ጤናማ መጠን ያለው ጭንቀት ውጤታማ እንድንሆን ሊገፋፋ ቢችልም መጠኑን ያለፈ ጭንቀት ሕይወትን ያመሳቅላል።

የተለያዩ መንገዶችን በመጠቅም ጭንቀትን ማስወገድ እንደሚገባም ባለሙያው ይመክራሉ።