'ሁላችንም ገንዘብ እንከፍላለን...ሴቶች ግን ለወሲብም ፈቃደኛ መሆን አለባቸው'

ናይጄሪያዊቷ ኤስተር
የምስሉ መግለጫ, ኤስተር ሌጎስን ለቅቃ የወጣችው እአአ በ2016 ነው

ኤስተር በናይጄሪያ መዲና ሌጎስ ጎዳናዎች ላይ ተኝታ ሳለ ነበር፤ አንዲት ሴት ከአገር እንደምታስወጣት እንዲሁም በአውሮፓ ሥራ እና የመኖሪያ ቤት እንደሚኖራት ቃል የገባችላት።

ኤስተር ይህንን ስትሰማ አዲስ ሕይወትን አልማ ነበር፤ በተለይ በዩናይትድ ኪንግደም። የተለያዩ በደሎች እና ጥቃቶች ካደረሰባት የማደጎ ቤት ከተባረረች በኋላ የምትቆይበት መጠለያ፣ ለመኖር የሚያስችል ቤሳ ቤስቲን አልነበራትም።

በአውሮፓውያኑ 2016 ሌጎስን ለቅቃ ስትሄድ እና የሊቢያ በረሃን ስታቋርጥ የሚጠብቃትን አስቸጋሪ ጉዞ፣ በወሲብ ንግድ ላይ እንደምትሰማራ እንዲሁም ከአገር አገር ጥገኝነት በመጠየቅ ለዓመታት እንደምትንከራተት ምንም ዕውቀት አልነበራትም።

አብዛኞቹ መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ወንዶች ናቸው።

የአውሮፓ መንግሥት ይህ ቁጥር 70 በመቶ እንደሚደርስ ይናገራል።

እንደ ኤስተር ያሉ ጥገኝነት ለመጠየቅ ወደ አውሮፓ የሚመጡ ሴቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

መቀመጫውን ጣሊያን ያደረገው የኢንተርናሽናል ሬስኪዩ ኮሚቴ ባልደረባ የሆነው ኢሪኒ ኮንቶጊያኒስ "በሜዲትራኒያን ባሕር እና በባልካን መንገድ ላይ ብቻቸውን የሚጓዙ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን እያየን ነው" ይላል።

በ2024 የወጣ ሪፖርት በባልካን መስመር ወደ ጣሊያን ለመግባት ብቻቸውን የሚጓዙ ሴቶች ቁጥር 250% ዓመታዊ ሲያሻቅብ የቤተሰቦች ቁጥር ደግሞ በ52 በመቶ ጨምሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወደ አውሮፓ የሚወስዱ የስደት መንገዶች በጣም ፈታኝ ናቸው። የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ባለፈው ዓመት ብቻ በአውሮፓ 3,419 ስደተኞች መሞታቸውን ወይም መጥፋታቸውን መመዝገቡን አስታውቋል። ይህ ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ የከፋ ነው ብሏል።

ኤስተር የተሻለ ሕይወት እንደምትኖር ቃል የገባችላት ሴት ከከዳቻት በኋላ ለፆታዊ ጥቃት እና ብዝበዛ ተጋልጣለች።

ይህ ደግሞ የሌሎች ስደተኛ ሴቶችም ዕጣ ፈንታ ነው።

"አንድ ክፍል ውስጥ ዘግታብኝ ወንድ አመጣችኝ። ከእኔ ጋር በጉልበት ወሲብ ፈጸመ። ገና ድንግል ነበርኩ" ትላለች ኤስተር።

"…ወጣት ልጃገረዶችን ለማማለል በናይጄሪያ በሚገኙ የተለያዩ መንደሮች ይሄዳሉ፤ ከዚያ ወደ ሊቢያ በማምጣት የወሲብ ባሪያ ያደርጓቸዋል።"

የአይኦኤም ባልደረባ የሆኑት ኡጎቺ ዳኒልስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የሴት ስደተኞች ልምድ የተለየ እና ብዙ ጊዜ ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው።"

"በቡድን ሆነው የሚጓዙ ሴቶች እንኳ ብዙ ጊዜ ቋሚ ጥበቃ ስለሌላቸው በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች፣ አጋቾች ወይም በሌሎች ስደተኞች ለሚደርስባቸው እንግልት ይጋለጣሉ።"

ብዙ ሴቶች የሚደርስባቸውን አደጋ ያውቃሉ፤ ነገር ግን የሚመጣውን እንጋፈጣለን በሚል የስደት ጉዞን ይጀምራሉ።

ምናልባት የመደፈር አደጋ የሚደርስባቸው ከሆነ በሚል ኮንዶም ወይም የእርግዝና መከላከያዎችን የሚይዙ ገጥመዋቸዋል።

ስቴላ ፖላር በተባለ የፀረ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ድርጅት ውስጥ የምትሠራው ሄርሚን ግቤዶ "ሁሉም ስደተኞች ለሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች መክፈል አለባቸው" ስትል ያለውን ሁኔታ ከገለጸች በኋላ "ሴቶች ግን ወሲብን እንደ የክፍያው አካል እንዲያቀርቡ ይጠበቃል" ብላለች።

ግቤዶ በሰሜን ምሥራቅ ጣልያን የወደብ ከተማ በሆነችው ትራይስቴ ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን ትደግፋለች።

ከባልካን የሚሻገሩ ስደተኞች ከዚህች ከተማ ተነስተው ወደ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ ።

ለስደተኞች ምግብ የሚያከፋፍል ወንድ

የፎቶው ባለመብት, Barbara Zanon/Getty Image

የምስሉ መግለጫ, በባልካን በኩል ወደ ትሬይስቴ የሚመጡት አብዛኞቹ ስደተኞች ወንዶች ናቸው

ኤስተር በሊቢያ ለአራት ወራት ስትበዘበዝ ከቆየች በኋላ አምልጣ የሜዲትራኒያን ባሕርን በጎማ ጀልባ ስታቋርጥ የጣሊያን የባሕር ዳርቻ ጠባቂዎች አግኝተዋት ወደ ላምፔዱሳ ደሴት ወስደዋታል።

የስደተኝነት ፈቃድ ከማግኘቷ በፊት ሦስት ጊዜ የጥገኝነት ጥያቄ አቅርባለች።

ብዙ ጊዜ ደኅንነታቸው አስተማማኝ ነው ተብለው ከሚታዩ አገራት የሚመጡ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ ይደረጋል።

የአውሮፓ መንግሥታት የስደተኞች ፍልሰት ቁጥርን ለመቀነስ እና ለማስቆም የተለያዩ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ግፊት ይደረግባቸዋል።

በዚህም የተነሳ ከስደተኞች ጋር የተያያዙ ሕጎቻቸውን ማጥበቅ በመጀመራቸው በአንድ ወቅት አስተማማኝ ሰላም የለባቸውም የተባሉ አገራት ላይ የያዙት አቋም ተለውጧል።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የጥገኝነት ጥያቄዎች ላይ ተጨማሪ ገደቦች እንዲቀመጡ የሚጠይቁ ድምፆች እየጨመሩ መጥተዋል።

የጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ፓርቲ አባል የሆኑት የሕዝብ እንደራሴ ኒኮላ ፕሮካቺኒ "የጅምላ ስደትን ማስቀጠል አይቻልም. . . ምንም መንገድ የለም" ብለዋል።

"በእርግጥ በአደጋ ውስጥ ላሉ ሴቶች ደኅንነቱ የተጠበቀ የሕይወት ዋስትና ልንሰጥ እንችላለን፤ ነገር ግን ለሁሉም አይደለም።"

ወግ አጥባቂ በሆነው የምርምር ተቋም ውስጥ ባልደረባ የሆኑት ራኪብ ኢህሳን "ጨካኞች መሆን አለብን" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

"ግጭት ከተከሰተባቸው እና አስገድዶ መድፈርን እንደ የጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ከሚገኝባቸው አገራት ለመጡ ሴቶች እና ልጃገረዶች ቅድሚያ መስጠት አለብን። በአሁኑ ጊዜ ግን ይህ በቋሚነት እየተተገበረ አይደለም" ሲሉ ይከራከራሉ።

አክለውም ሴቶቹ ወደ አውሮፓ ለመምጣት የሚያልፉባቸው አደገኛ መንገዶች የሚፈጥሩባቸውን የሐዘን ስሜት ገልጸው "አዋጪው መንገድ፣ ልጓም የተበጀተለት ርህራሄ ነው" ብለዋል።

አስተማማኝ ሰላም አላቸው ከሚባሉ አገራት የሚመጡ በርካታ ሴቶች ግን በሴትነታቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን በደል ዘርዝረው ያስረዳሉ። አገራቸው ውስጥ ያለው ሁኔታ ደኅንነታቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸውም ይናገራሉ።

ይህ ከኮሶቮ የመጣችው የ28 ዓመቷ ኒና ታሪክ ነው።

"ሰዎች ኮሶቮ ውስጥ ሁሉም ነገር መልካም ነው ብለው ያስባሉ፤ ግን ያ እውነት አይደለም" ትላለች። "ነገሮች ለሴቶች በጣም አስፈሪ ናቸው።"

ኒና እሷ እና እህቷ በወንድ ጓደኞቻቸው የወሲብ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው እና የወሲብ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ እንዳስገደዷቸው ትናገራለች።

በ2019 የአውሮፓ የደኅንነት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው በኮሶቮ 54 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ከ15 ዓመታቸው ጀምሮ በቅርብ ጓደኞቻቸው የሥነ ልቦና፣ የአካል ወይም ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል።

ፆታን መሠረት ካደረገ ጥቃት ጋር ተያይዞ የተለያየ እንግልት የሚደርስባቸው ሴቶች በአውሮፓ በኢስታንቡል ኮንቬንሽን ምክር ቤት መሠረት ጥገኝነት የማግኘት መብት አላቸው።

ይህ ደግሞ የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ዓመት ባሳለፈው ውሳኔ ድጋፍ አግኝቷል።

ኮንቬንሽኑ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ የሴቶች ግርዛትን ጨምሮ ሥነ ልቦናዊ፣ አካላዊ እና ፆታዊ መሆናቸውን ያጠቃልላል።

ነገር ግን በበጎ አድራጎት ቡድኖች ማብራሪያ መሠረት ደንቡ በወጥነት እየተተገበረ አይደለም።

የ'ኢንድ ኤፍጂኤም ዩሮፒያን ኔትወርክ' ዳይሬክተር የሆኑት ማሪያኔ ንጉዌና ካና "በዘርፉ ያሉ ብዙ የጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ የሚመለከቱ ኃላፊዎች እንዲህ ዓይነቱን አሳሳቢ ጉዳይ በሚመለከት [የሴት ልጅ ግርዛትን የመሰሉ] በቂ ሥልጠና ያላገኙ ወንዶች ናቸው።"

ብዙ ሴቶች ግርዛት ብቻ ስለተፈፀመባቸው ሌላ ምንም ዓይነት አደጋ አይደርስባቸውም በሚል የተሳሳተ ግምት የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጓል ሲሉ ያክላሉ።

ንጉዌና ካና "'አንድ ጊዜ ተገርዘሻል' ወደ አገርሽ ብትመለሽ ለአንቺ አደጋ የለውም'፤ ምከንያቱም ዳግመኛ ሊገርዙሽ አይችሉም" የሚሉ የሕግ ባለሙያዎች እንዳሉ ይናገራሉ።

ሦስት ሴቶች በአንድ ክፍል ውስጥ ተቀምጠው ሲስቁ

የፎቶው ባለመብት, International Rescue Committee

የምስሉ መግለጫ, በጣሊያን በስደተኞች እና በጥገኝነት ጠያቂዎች ዙሪያ የሚሰሩ የኢንተርናሽናል ሬስኪዩ ኮሚቴ ባለሙያዎች

በዩኬ 'ቻሪቲ ዊሜን ፎር ሪፊውጂ ዊሜን' የምትሠራው ካሬንዛ አርኖልድ፣ ወሲባዊ ጥቃት ልክ እንደ አካላዊ ጥቃት ተመሳሳይ ጠባሳ ትቶ ስለማያልፍ ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው ትላለች።

ከዚህ በተጨማሪ እንደ ለማውራት የሚያሳፍር ነገር በመሆኑ እና ያለው ባህላዊ ስሱነት ሂደቱን የበለጠ ከባድ ያደርገዋል ብላለች።

አርኖልድ "ሴቶች በተደጋጋሚ ሂደቱ በፍጥነት እንዲያልቅላቸው ይፈልጋሉ። ዛሬ ላገኙት የኢሚግሬሽን መኮንን የደረሰባቸውን ፆታዊ ጥቃት ዘርዝረው ሊናገሩ አይችሉም።"

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አብዛኛው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የሚፈጸሙት በጉዟቸው ወቅት ነው ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ኡጎቺ ዳኒልስ "ሴቶች በአብዛኛው ከትዳር አጋሮቻቸው የሚደርስባቸውን ወሲባዊ ጥቃት አምልጠው ይመጣሉ፣ ከዚያም በጉዞው ወቅት ተመሳሳይ ነገር ያጋጥማቸዋል" ይላል።

ኒና እና እህቷ በኮሶቮ ጥቃት የሚያደርሱባቸውን አጋሮቻቸውን ሸሽተው ወደ ጣሊያን አዲስ ሕይወት ለመጀመር ሲሰደዱ ያጋጠማቸው ሁኔታ ይህ ነበር።

ከሌሎች ሴቶች ጋር ሲጓዙ ከድንበር ጠባቂዎች ለመሸሽ በሚል በምሥራቅ አውሮፓ በሚገኙ ደኖች መካከል ለመሄድ ተገድደዋል። እዚያም በወንድ ስደተኞች እና በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው ይናገራሉ።

ኒና በተራሮች አናት ላይ በጨለማ ውስጥ እየተጓዙ ሳሉ "ሰዎቹ ችቦ ይዘው ወደ እኛ መጥተው ፊታችን ላይ አበሩ፣ ከዚያ የሚፈልጉትን እየመረጡ ወደ ጫካ ወሰዷቸው። ሌሊት ላይ እህቴ እርዳታ ፍለጋ ስትጮህ እና ስታለቅስ እሰማ ነበር።"

ኒና እና እህቷ ወደ አገራቸው ከተመለሱ የቀድሞ የወንድ ጓደኞቻቸው እንደሚገድሏቸው ለጣሊያን ባለሥልጣናት ተናግረዋል። በስተመጨረሻም የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል።

ኤስተር የስደተኝነት መብት ለማግኘት የምታደርገው ትግል ግን ብዙ ጊዜ ወሰደ።

መጀመሪያ በጣሊያን የጥገኝነት ጥያቄዋን ያስገባችው በአውሮፓውያኑ 2016 ነበር። ነገር ግን በዚያ ረዥም ጊዜ ከቆየች በኋላ ወደ ፈረንሳይ ከዚያም ወደ ጀርመን ሄዳለች።

በአውሮፓ የጥገኝነት ጥያቄ ሕግ መሠረት አንድ ስደተኛ ጥያቄውን ማቅረብ የሚችለው መጀመሪያ በገባበት አገር በመሆኑ ማመልከቻዋ ውድቅ ተደርጎባታል።

በመጨረሻ በአውሮፓውያኑ 2019 በጣሊያን በስደተኛነት መኖር የሚያስችላትን ፈቃድ አግኝታለች።

ናይጄሪያን ለቅቃ ከወጣች ወደ አስር ዓመታት ገደማ የሆናት ኤስተር፣ አሁን የጣሊያን ቆይታዋ እዚያ ለመድረስ ያሳለፈችውን ስቃይ የሚክስ መሆን አለመሆኑን ትጠይቃለች።

"ወደዚህ የመጣሁበትን ምክንያት እንኳን አላውቅም።"