ሰሜን ኮርያ የገነባችው የጦር መርከብ በመክሸፉ ከፍተኛ ባለስልጣኗን አስረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰሜን ኮርያ፤ የሀገሪቱን መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ባስቆጣው የአዲስ የጦር መርከብ ክሽፈት ምክንያት አራት ባለስልጣናትን አሰረች።
በሀገሪቱ መንግስት የሚተዳደረው ኬሲኤንኤ የዜና ወኪል፤ የሰራተኞች ፓርቲ የጦር መሳሪያ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር ሪ ሃዮንግ ሰን፤ ባለፈው ሳምንት ለተከሰተው "ከፍተኛ አደጋ በአብዛኛው ተጠያቂ ናቸው" ሲል ሰኞ ዕለት ዘግቧል።
አምስት ሺህ ቶን የሚሸከመው የጦር መርከብ በመገልበጡ የተነሳ ውሃ ላይ የሚያርፈው ዋነኛው የመርከቡ ክፍል ተጎድቷል። ኪም ጆንግ ኡን ይህንን ክስተት የሀገሪቱን "ክብር እና ኩራት በእጅጉ የጎዳ"፤ "የወንጀል ድርጊት" ሲሉ ገልጸውታል።
መርከቡ በባለሙያዎች ቡድን ጥገና እየተደረገለት እንደሆነ የዜና ወኪሉ ዘግቧል።
የፓርቲው ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮሚሽን አባል የሆኑት ሪ ሃዮንግ ሰን፤ በዚህ ክስተት ምክንያት እስካሁን ከታሰሩ ሰዎች መካከል ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው ናቸው።
ኮሚሽኑ የሰሜን ኮርያ ህዝብ ሠራዊትን የሚያዝ እንዲሁም የሀገሪቱን ወታደራዊ ፖሊሲዎች የማዘጋጀት እና የመተግበር ኃላፊነት ያለው ነው።
ፒዮንግያንግ፤ የጦር መርከቡ በተሰራበት እና በከሸፈበት ሰሜናዊ ቾንግጂን የመርከብ ግንባታ የሚገኙ ሶስት ባለስልጣናትን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አስራለች። ባለስልጣናቱ ዋና ኢንጂነር፣ የንግባታ ኃላፊ እና የአስተዳደሩ ስራ አስኪያጅ ናቸው።
ኪም፤ የረቡዕ ዕለቱ ክስተት "በፍጹም ግድየለሽነት፣ ኃላፊነት በጎደለው እና ሳይንሳዊ ባልሆነ ልምምድ" የተፈጠረ መሆኑን ከዚህ ቀደም ተናግረዋል።
የታሰሩት ባለስልጣናት ምን ቅጣት ሊጣልባቸው ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አልታወቀም። ነገር ግን የሀገሪቱ አምባገነን መንግሥት ጥፋተኛ ሆነው ያገኛቸውን ባለስልጣናት በግዳጅ የጉልበት ስራ እና በሞት ጭምር እንደሚቀጣ ይታወቃል።
በሰሜን ኮርያ በሀገር ውስጥ የተፈጠረ አደጋን ለህዝብ ይፋ የማድረግ ነገር ያልተለመደ ቢሆንም ከዚህ ቀደም የተወሰኑ የከሸፉ ሳተላይት የማምጠቅ ሙከራዎች ተገልጸው ያውቃሉ።
አንዳንድ ተንታኞች፤ የኪም ጆንግ ኡን ፈጣን እና ጠንካራ ምላሽ ፒዮንግያንግ ወታደራዊ አቅሟን ማጠናከሯን እንደምትቀጥል የሚያመለክት እንደሆነ ያምናሉ።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሰሜን ኮርያ ባለሙያ የሆኑት ኤድዋርድ ሆውል፤ "ይህ ሰሜን ኮርያ የባህር ኃይል ቴክኖሎጂዋን ለመጠገን እና ለማጠናከር የምታደርገውን ሙከራ እንደማታቆም ለደቡብ ኮርያ እና አሜሪካ ግልጽ መልዕክት ያስተላልፋል" ሲሉ ለኤቢሲ ተናግረዋል።
ደቡብ ኮርያ በሚታተመው እና በሰሜን ኮርያ ላይ በሚያተኩረው ዴይሊ ኤንኬ የዜና አውታር ላይ የወጣ አንድ አስተያየት፤ የኪም ጆንግ ኡን "የግዴታ ግልጽነት" የባህር ኃይልን ማዘመንን ወሳኝ እና ቅድሚያ የሚሰጠው እርምጃ አድርጎ እንደሚመለከት ያሳያል ብሏል። "ይፋዊ ክሽፈቶች ሰፊውን የወታደራዊ እድገት ትርክት አያደናቅፉም" ሲልም አክሏል።
የባለፈው ሳምንቱ አደጋ የተፈጠረው ሰሜን ኮርያ በሌላ የሀገሪቱ ክፍል ተመሳሳይ የጦር መርከብ ይፋ ካደረገች ከሳምንታት በኋላ ነው።
ኪም የጦር መርከቡ፤ የሰሜን ኮርያን የባህር ኃይል ለማዘመን "ፈርቀዳጅ" ሲሉ የጠሩት ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ወደ ስራ እንደሚገባ አስታውቀዋል።












