" እያንዳንዱ ወንድ ድርሻውን ሊወጣ ይገባል" የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም የሚሞክሩት ደቡብ አፍሪካውያን ወንዶች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

"ሁል ጊዜ ሴቶችን የሚደበድቡ ወንዶችን እመለከታለሁ" ይላል የ30 ዓመቱ ጎሞሶ ማቴጋ። በተለይ ደግሞ ሁለቱም በሚሰክሩበት ጊዜ ይህ የከፋ እንደሆነ ይገልጻል።

በእርግጥ እርሱም በአንድ ወቅት ከፍቅረኛው ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ያስታውሳል። በዚህ ጊዜ ጎትቶ በጥፊ እንደመታትም አልሸሸገም።

ማቴጋ በአገሪቷ እየጨመረ የመጣውን እና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመቀነስ አልመው በተሰበሰቡ ወንዶች መካከል ያደረገውን በግልጽ ነበር የተናገረው።

ውይይቱ የተካሄደው በጆሃንስበርግ በሚገኘው 'ኦረጋኒክ ማርኬት' ተብሎ በሚጠራው መንገድ ላይ ነበር።

ማቴጋ ፍቅረኛውን የመታበትን ጊዜ ሲያስታውስ እንደሚያመው ይናገራል። "ተለያይተናል ፤ ልጄንም ማየት አልችልም፤ አሁን የሚሰማኝ ጥሩ ሰው በመሆን ፋንታ ለደቡብ አፍሪካ ችግር እኔም አስተዋፅኦ እንዳደረኩ ነው" ብሏል።

በአቅራቢያው ከሚገኝ መጠጥ ቤት የተወሰኑ ወንዶችም ወንበራቸውን ስበው ስብሰባውን ተቀላቀሉ።

በተወያዮቹ መካከል በአካባቢው ብራ ስቲቭ በመባል የሚታወቀው ኡቱሜሌንግ ስቴፈን ታማጋ ይገኛል። እጁን አውጥቶ "እኛ ወንዶች ነን!" ብሎ ጮኸ። ጭብጨባው ቀለጠ። አንዳንዶቹ ቢራቸውን እየተጎነጩ የሚለውን መስማት ቀጠሉ።

ስቲቭ ንግግሩን ቀጠለ። " በፆታ ላይ የተመሰረተ ጥቃትን እና ሴትን መግደልን ለመዋጋት በአንድ ላይ መቆም አለብን" አለ።

ብራ ስቲቭ 'ፋዘር ኤ ኔሽን' የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት የአካባቢው አስተባባሪ ነው። ድርጅቱ አዎንታዊ ወንድነትን በማጎልበት በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለማስቆም ከወንዶች እና ታዳጊ ወንዶች ጋር ይሰራል።

ቡድኑ ስብሰባውን ያካሄደውም እንደ አዲስ ያገረሸው በሴቶች ላይ የሚፈፀም ግድያ እና ጥቃት ቁጣ ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው።

በጆሃንስበርግ አቅራቢያ ኢኩርሁልኒ ከተማ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ የ12 ሴቶች አስክሬን መገኘት ጥያቄ አስነስቷል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ስሪል ራማፎሳ መንግሥታቸው በቂ እርምጃ እንዳልወሰደ አምነው ሴቶችን የበለጠ ደኅንነት እንዲሰማቸው ለማድረግ ያስችላል ያሏቸውን እርምጃዎች አስታውቀዋል።

አገሪቷ በዓለም ላይ ከፍተኛ ግድያ ከሚፈፀምባቸው አገራት አንዷ ስትሆን በዚህ ዓመት ብቻ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ 5 ሺህ 427 ሰዎች ተገድለዋል።

የደቡብ አፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንደገለጸው በእነዚህ ወራት 569 ሴቶች ተገድለዋል። በአማካይ በአንድ ቀን ስድስት ሴቶች ተገድለዋል ማለት ነው ። ከዚህም በተጨማሪ 1052 ሴቶች ከግድያ ሙከራ መትረፋቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ከአራት ዓመት በፊት 'ሂውማን ሳይንስ ሪሰርች ካውንስል' ባወጣው ሪፖርት ከ35 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደቡብ አፍሪካውያን ሴቶች አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች ተፈፅሞባቸዋል። አብዛኞቹ ይህ ጥቃት የደረሰባቸው በገዛ አጋሮቻቸው ነው።

ለብራ ስቲቭ የዚህ ችግር የመፍትሔ አካል የሚሆነው ወንዶች ጉዳዩን እንዲረዱት እና ለሚፈፅሙት ድርጊት ኃላፊነት እንዲወስዱ ማድረግ ነው።

" የጠፋ ትውልድ ነን" የሚለው ብራ ስቲቭ ፣ " እዚህ አካባቢ ያሉ ወንዶችን ክብር መመለስ አለብን" ብሏል።

ከመጠጥ ቤቱ ደጅ በተሰባሰቡ ወንዶች መካከል ዚዚፎ ሚትዊሲ ይገኛል። ሚትዊሲ የ'ፋዘር ኤ ኔሽን' ፕሮጀክት አስተባባሪ ነው።

በቅርቡ ያጋጠመውን ክስተት በተመለከተ አስተያየቱን ሲሰጥ "ብዙ መሰራት አለበት" ብሏል።

የመንገድ መብራቶችን ማሻሻል እና ያልተፈቱ ችግሮችን መገምገምን ጨምሮ ፕሬዚደንት ራማፎሳ ያስተዋወቁት የቅርብ ጊዜ እርምጃ " ኢምንት እና በጣም የዘገየ" እንደሆነም ተናግሯል።

"በጆሃንስበርግ የተፈፀሙ የቅርብ ጊዜ ግድያዎችን ሳስብ በጣም ነው የምናደደው። ይህን ለማስቆም ምን እስከሚሆን ድረስ ነው መጠበቅ ያለብን? ሲልም ይጠይቃል።

የቡድኑ መሥራች የሆነው ክሬግ ዊልኪንሰን በበኩሉ ወንዶች እንዲያወሩ እና ስሜታቸውን እንዲያወጡ እንደሚሰበስቧቸው ያስረዳል።

"በዚህ ጊዜ ይታከማሉ፤ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ አዎንታዊ ወንድነት እንዲኖራቸው ማሰልጠን እና ማስተማር ነው" ሲሉም ይህ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ይቀንሳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።

ዊልኪንሰን " እናንተ እንደ ወንድ ለጥሩ ነገር ወሳኝ ኃይል ናችሁ" ሲል በተሰበሰቡት ወንዶች መካከል ቆሞ ይናገራል።

"ምን ዓይነት ወንድ መሆን እንደምትፈልጉ መምረጥ ትችላላችሁ። ሴቶች ደኅንነታቸው መጠበቅ አለበት" ሲልም ያክላል።

'ፋዘር ኤ ኔሽን' በመላው ደቡብ አፍሪካ የሚሰራ ሲሆን ጤናማ ወንድነትን የሚሰብክ ሲሆን እና በበርካታ ትምህርት ቤቶች እና ኮሌጆች ሥልጠና ይሰጣል።

በተከታታይ የተፈፀሙ እና እንቆቅልሽ የሆኑ ግድያዎች ደቡብ አፍሪካን አስደንግጠዋል። ይህም ሴቶች እየተጋፈጡት ያለውን አደጋ በተመለከተ ብሔራዊ ውይይቶች እንዲደረጉ ምክንያት ሆኗል።

ፖሊስ የተፈፀሙ ግድያዎች እየመረመረ እንደሆነ ቢገልጽም፣ ተከታታይ የሴቶች ግድያን የሚፈፅም እንዳለ አላረጋገጠም። በተወሰኑ ግድያዎች ላይ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ግን ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

የሴቶቹ ሞት አዲስ ስጋትን የፈጠረ ሲሆን 'በኦርጋኒክ ማርኬት' ያሉ አንዳንድ ሴቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ፍርሃት አድሮባቸዋል።

በወንዶቹ ውይይቱ የተሳበችው ሻክ ሊንኬ በአቅራቢያቸው ልብስ እያጠበች ታዳምጣለች።

ሊንኬ "ከቤታችን ስንወጣ ደኅንነት አይሰማንም" ብላለች።

" እየተራመድን ከጀርባችን መኪና ሲመጣ እንፈራለን፤ እንጨነቃለን፤ ይህ ሰው ቢያግተኝስ ወይም የሆነ ነገር ቢያደርገኝስ ብለን እንፈራለን" ትላለች።

ይህንን ስጋት በርካታ ሴቶችም ይጋሩታል። በአካባቢው በሚገኝ የውበት ሳሎን የምትሰራው ፕሮቪደንስ ማሴኮ " ደኅንነት የለም፤ ምን አልባት አንተ ገዳይ ልትሆን ትችላለህ፤ ማንን ማመን እንዳለብኝ እንዴት ላውቅ እችላለሁ?" ስትል ትጠይቃለች።

ይህንን ስትናገር ብራ ስቲቭ በሳቅ ታጅቦ " ስለዚህ ጉዳይ ማውራት አለብን፤ ወደ ውይይታችን ነይና እርስ በርስ እንዴት መተማመን እንዳለብን እንማማራለን" ሲል መልሶላታል።

ወንዶቹ ስብሰባቸውን እያጠቃለሉ ነው።

" ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለማስቆም እየሞከርን በመሆኑ እያንዳንዱ ወንድ የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ማወቅ አለበት" ብሏል ዚዚፖ በማጠቃለያ ሃሳቡ።

" ወንዶች በሴት ልጆቻቸው ወይም በራሳቸው እናት ላይ ይህ እንዲሆን የማይፈቅዱ ከሆነ ሚስቶቻቸው ወይም ፍቅረኛቸው በሆነች በሌሎች ሰዎች ሴት ልጆች ላይ ይህ እንዲሆን መፍቀድ የለባቸውም" ሲልም አፅንኦት ሰጥቷል።

ማቴጌ በሰማው ነገር ተደንቋል። የሰማውን ነገር በተግባር እንደሚያውልም ቃል ገብቷል።

" አርአያዎች የሉንም፤ አባቶቻችን እና አጎቶቻችን እስር ላይ ናቸው፤ አሁን ላይ እኛ ምሳሌ በመሆን ይህችን አገር የተሻለች ማድረግ አለብን" ብሏል።