ሐማስ ከ2 ሺህ በላይ ሮኬቶችን ከተኮሰ በኋላ አስራኤል ጦርነት እንደተከፈተባት አስታወቀች

በሐማስ በተተኮሱ በርካታ ሮኬቶች በተመታችው ደቡባዊቷ አሽኬሎን ከተማ የደረሰ ጉዳት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በሐማስ በተተኮሱ በርካታ ሮኬቶች በተመታችው ደቡባዊቷ አሽኬሎን ከተማ የደረሰ ጉዳት

የፍልስጤማዊው ቡድን ሐማስ ከሁለት ሺህ በላይ ሮኬቶችን በእስራኤል ላይ ከተኮሰ በኋላ፣ ታጣቂዎቹ ወደ ደቡባዊ የእስራኤል ክፍል ዘልቀው መግባታቸውን ተከትሎ አስራኤል ጦርነት ውስጥ መግባቷን አስታወቀች።

ይህንን ከባድ ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣናት በሐማስ ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ አስቸኳይ ምክክር አድርገዋል፤ የጦር ሠራዊቱም ለአባላቱ “ለጦርነት ዝግጁ” እንዲሆኑ ትዕዛዝ በማስተላለፍ፣ ለአገሪቱ ተጠባባቂ ጦር አባላት ጥሪ አቅርቧል።

ፍልስጤማዊው ታጣቂ ቡድን ሐማስ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፍቶ ተዋጊዎቹ ወደ እስራኤል ግዛት ሰርገው ከገቡ በኋላ ጦርነት እንደተከፈተባት እስራኤል ገልጻለች።

ድንገተኛውን ጥቃት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ “ጦርነት ውስጥ ነን” በማለት አገራቸው ላይ በሐማስ ታጣቂዎች ጦርነት እንደተከፈተ ተናግረዋል።

ቅዳሜ ማለዳ ላይ የሐማስ ታጣቂዎች ከጋዛ ሰርጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የሮኬት ውርጅብኝ በእስራኤል ላይ በሚያዘንቡበት ጊዜ፣ ተዋጊዎቻቸው የድንበር አጥር በመሻገር ነው ወደ እስራኤል መግባታቸው የተነገረው።

ከዚህ በፊት አጋጥሞ በማያውቅ ሁኔታ የሮኬት ጥቃት ወደ ተፈጸመባት እስራኤል ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ፣ ነገር ግን በርካታ የሐማስ ተዋጊዎች ድንበር ተሻግረው መግባታቸው እስራኤልን አስቆጥቷል።

አንድ የሐማስ ከፍተኛ አዛዥ ቡድናቸው ወደ እስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ከጋዛ ማስወንጨፉን ገልጸው፣ ፍልስጤማዊው ቡድን እስራኤልን ለመግጠም መቁረጡን “በቃ ማለት በቃ ነው ብለን ወስነናል” በማለት ገልጸዋል።

የእስራኤል የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ተቋማት እንዳሉት በሐማስ የሮኬት ጥቃቶች ቢያንስ 40 እስራኤላውያን ሲገደሉ፣ የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ደግሞ ከ540 በላይ ሰዎች የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የፍልስጥኤም የጤና ባለሥልጣናት ደግሞ በእስራኤል አየር ድብደባ ቢያንስ 198 ፍልስጤማውያን ጋዛ ውስጥ መገደላቸውን አሳውቀዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ፣ ሐማስ በአገራቸው ላይ ለፈጸመው ጥቃት “አይቶት የማያውቀውን ዋጋ ይከፍላል” ሲሉ ዝተዋል።

የእስራኤል ጦር ኃይልም ለተፈጸመው ጥቃት ምላሽ በርካታ የጦር አውሮፕላኖቹ ጋዛ ውስጥ በሚገኙ የሐማስ ይዞታዎች ላይ የአየር ድብደባ እየፈጸሙ መሆናቸውን ገልጾ፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተጠባባቂ የሠራዊቱ አባላትን እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል።

እንዲህ ያለው የተቀናጀ እና ከባድ ጥቃት በአገሪቱ ላይ እስኪከፈት ድረስ የእስራኤል የስለላ እና የደኅንነት ተቋማት ምንም አይነት መረጃ ሳያገኙ መቅረታቸው ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን፣ በዚህም ዙሪያ ከፍተኛ ምርመራ መጀመሩ ተነግሯል።

ከሐማስ ሮኬቶች አንዱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ከሐማስ ሮኬቶች አንዱ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከጥቃቱ ቀደም ብሎ በርካታ ሮኬቶች ወደ እስራኤል ግዛት የተተኮሱ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በመላዋ አገሪቱ የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደውሎች ተሰምተዋል።

እስራኤልም በበኩሏ በጋዛ ሰርጥ በሚገኙ ኢላማዎች የአየር ድብሰባ ማካሄድ የጀመረችው የሐማስ ሮኬቶች ግዛቷ ውስጥ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ነው።

የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን የሆነው ሐማስ ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነት የወሰደ ሲሆን፣ በ20 ደቂቃ ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ ሮኬቶችን ወደ አስራኤል መተኮሱን ገልጿል።

የእስራኤል የመከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ “ቡድኑ ሰፊ የሮኬት ጥቃቶችን ወደ እስራኤል ግዛት ከተኮሰ በኋላ” በተለያዩ አቅጣጫዎች ደግሞ ታጣቂዎቹ ወደ እስራኤል ግዛት መግባታቸውን አስታውቋል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ቪዲዮዎች ከጋዛ ሰርጥ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የእስራኤል ከተማ በሆነችው ስዴሮት ውስጥ የታጠቁ ፍልስጤማውያን በክፍት መኪና ላይ ሆነው በጎዳና ላይ አሳይተዋል።

መግለጫው አክሎም የእስራኤል ጦር ኃይል ጠቅላይ ማዘዣ በተከፈተው ጥቃት ዙሪያ “የሁኔታዎች ግምገማ” እያካሄደ መሆኑን ጠቅሶ ሐማስ ለተፈጸመው ጥቃት “ኃላፊነት እና የአጸፋ እርምጃ እንደሚከተለው” ገልጿል።

በተጨማሪም በጋዛ ሰርጥ ዙሪያ ያሉ ነዋሪዎች ቤታቸው እንዲቆዩ የተጠየቁ ሲሆን፣ በደቡባዊ እና በማዕከላዊ የእስራኤል አካባቢዎች ያሉ ሲቪል ሰዎች ደግሞ ከጥቃት ለመሸሸጊያ ከሚያገለግሉ መጠለያዎች አቅራቢያ እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል።

ከሮይተርስ ዜና ወኪል የተገኙ ምስሎች አሽኬሎን በተሰኘው የእስራኤል ከተማ ውስጥ የእሳት አደጋ ሠራተኞች እየተቃጠለ ያሉ ተሽከርካሪዎችን ለማጥፋት ሲሞክሩ አሳይተዋል።

ከሮኬቶቹ ጥቃት በኋላ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የፀጥታ ባለሥልጣናትን ሊያነጋግሩ እንደሆነ ጽሕፈት ቤታቸው ገልጿል።