የሶሪያው ፕሬዚዳንት ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ 'አሸባሪ' ዝርዝር ውስጥ ከወጡ በኋላ ለይፋዊ ጉብኝት ዋሺንግተን ገቡ

የሶሪያ ፕሬዚዳንት አህመድ ሻራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሶሪያ ፕሬዚዳንት አህመድ ሻራ በአሜሪካ ተጥሎባቸው የነበረው ዓለም አቀፍ አሸባሪ የሚለው ፍረጃ በይፋ ከተነሳ በኋላ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዋሺንግተን ገብተዋል።

የቀድሞው እስላማዊ ታጣቂ የሚመሩት የአማጺያን ጥምረት በሽር አላሳድን ከሥልጣን ካስወገደ ከ11 ወራት በኋላ ሰኞ ዕለት በዋይት ሐውስ ዶናልድ ትራምፕን ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሬዚዳንቱ በአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሺንግተን ዲሲ ከመድረሳቸው ሰዓታት ቀደም ብሎ የሶሪያ የደኅንነት ባልደረቦች በርካታ የኢስላሚክ ስቴት ቡድን አባላትን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ተገልጿል።

ሻራ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር በሚኖራቸው ንግግር ወቅት የእስላማዊው ቡድን የቀሩ አባላትን ለመቆጣጣር የሚደረገው የጋራ ትብብር ዋነኛ አጀንዳ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የሶሪያ ባለሥልጣናት በቡድኑ አባልነት የተጠረጠሩ 71 ሰዎችን ከጦር መሣሪያ እና ተቀጣጣይ ነገሮች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ተናግረዋል።

ሻራ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ሶሪያን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ለመወከል የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።

አሳድ በሥልጣን ላይ በነበሩት እና ለ13 ዓመት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት በቀጠለበት ወቅት ሶሪያ ከዓለም አቀፍ መድረክ ተገልላ ቆይታለች።

ፕሬዚዳንት ሻራ በመስከረም ወር ወደ አሜሪካ ተጉዘው በተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ጉባዔ ላይ የተገኙ ሲሆን በወቅቱም ሶሪያ "በዓለም ላይ የሚገባትን ስፍራ ዳግም ትይዛለች" በማለት የዓለም መሪዎች የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ ጠይቀው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አሜሪካ ማዕቀቦችን ለማንሳት የወሰደችውን እርምጃ ደግፏል።

አሜሪካ በሶሪያ እና በአገሪቱ መሪዎች ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማንሳት ወራትን የፈጀ ሂደት ተከትላለች።

ዩናይትድ ስቴትስ አርብ ዕለት ሻራ እና የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አናስ ሐሰን ካታብ ጽንፈኛ ቡድኖችን በመደገፍ ወይም ገንዘብ በመስጠት ከተጠረጠሩ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲወጡ አድርጋለች።

ውሳኔውን የአሜሪካ ግምጃ ቢሮ "በሶሪያ አመራሮች ዘንድ ለታየው ለውጥ እውቅና ለመስጠት የተደረገ" ብሎታል።

ሻራ በአሜሪካ የአሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ የሰፈሩት ሙሀመድ አል ጃውላኒ በሚል ተለዋጭ ስማቸው ሲሆን ይህም ሃያት ታህሪሪ አል ሻምን (ኤችቲኤስ) ታጣቂ ቡድን በሚመሩበት ወቅት ይጠቀሙበት የነበረ ነው።

ቡድኑ እአአ እስከ 2016 ድረስ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት የነበረው ሲሆን ሻራም የዚህ ትብብር ቁልፍ ሰው በመሆን አገልግለዋል።

ሻራ ኤቲኤስን ከመምራታቸው በፊት ኢራቅ ውስጥ ለአልቃይዳ ተሰልፈው ሲዋጉ በአሜሪካ በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ያሉበትን ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታ ነበር።

አሜሪካ ከወራቶች በፊት በኤቲኤስ ላይ ጥላ የነበረውን ማዕቀብ አንስታለች።

ትራምፕ ሪያድን በጎበኙበት ወቅት ከሻራ ጋር ተገናኝተው የነበረ ሲሆን "ጠንካራ ግለሰብ፣ በጣም ጠንካራ የሆነ የኋላ ታሪክ ያለው" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ምንም እንኳ ቀደም ሲል ሻራ በአሸባሪነት ከተፈረጁ ታጣቂዎች ጋር ቢሰሩም፣ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ሁሉን አካታች መንግሥት እንደሚመሰርቱ በመናገራቸው የሶሪያ የተለያዩ ብሔሮችን እና አንጃዎችን ድጋፍ ማግኘታቸውን ተከትሎ የአሳድ መንግሥትን የሚቃወሙ አገራት ድጋፍ ችረዋቸዋል።

ከወራቶች በፊት በፀጥታ መዋቅር ውስጥ የሶሪያ አላዌቴ ህዳጣንንን በመግደል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን መንጥረው እንደሚያወጡ ተናግረው ነበር።

ባለፉት ጥቂት ወራት በሱኒ ቤድወኒ ጎሳ ተዋጊዎች እና ድሩዝ ታጣቂዎች መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት ተቀስቅሶ ከአስር ዓመታት በላይ በጦርነት የምትታወቀውን አገር የሚመራው የኤችቲኤስ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ መረጋጋትን ያመጣል ወይ የሚል ጥያቄ ፈጥሮ ነበር።