የእንቅልፍ ሕይወትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ስድስት ሳይንሳዊ አማራጮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በመላው ዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በእንቅልፍ እጦት ይሰቃያል። በአሜሪካ ብቻ ከ50 እስከ 70 ሚሊዮን ሕዝብ በእንቅልፍ እጦት ይቸገራል።
በሳይሳዊ መንገድ ለአካላዊ እና ሥነ-አእምሯዊ ጉዳዮች ማስተካከያ በማድረግ የእንቅልፍ ማጣት ችግርን መቅረፍ የሚያስችሉ አማራጮች አሉ።
ሰዎች ከዚህ ቀደም የተጠቀሟቸውን ስልቶች እንዲሁም በሳይሳዊ ምርምር የተረጋገጡ ዘዴዎች በመጠቀም ጥሩ ተኝተው እንዲያድሩ የሚያስችሉ መንገዶች 6 አማራጮች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።
በሁለት ፈረቃ መተኛት
ለተከታታይ 8 ሰዓታት መተኘት ይኖርብናል ብለን እያሰብን ድንገት እኩለ ለሊት ላይ ንቅት ማለት ስሜት የሚረብሽ ሊሆን ይችላል።
ይህ እኩለ ለሊት ላይ መንቃት ጥንትም የነበረ ነው። በባለፉት በርካታ ዘመናት ሰዎች እኩለ ለሊት ላይ ነቅተው መልሶ እንቅልፍ እስኪወስዳቸው ድረስ በመካከሉ የቤት ውስጥ ስራዎችን እስከመስራት ይደርሱ ነበር።
ለጥቂት ሰዓታት ከመንቃት በኋላ ብዙዎች ወደ አልጋቸው ተመልሰው እስከ ጠዋት ድረስ ይተኛሉ።
በቨርጂኒያ ቴክ ዩኒቨርሲቲ እውቅ የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ሮጀር ኡኪርች ዛሬ ላይ በእንቅልፍ መቆራረጥ የሚቸገሩ ሰዎች በጥንቱ ጊዜ ከነበረው “የሁለት እንቅልፍ” ልማድ በመነሳት እንደ አስፈላጊነቱ በአተኛኘታቸው ላይ ለውጥ ማድረግ ይችላሉ ይላሉ።
አተኛኘትዎን ከወቅቱ ጋር ያዛምዱ
ተመራማሪዎች እንደሚሉት ወቅት በተቀያየረ ቁጥር የሰዎች እንቅልፍም ከጊዜው ጋር አብሮ ይቀያየራል።
በክረምቱ እና በቀዝቃዛው ወራት ብዙ እንቅልፍ መተኛት እንዳለብን ጥናቶች ያሳያሉ።
አንድ በጀርመን አገር የተሰራ ጥናት ሰዎች “አርኤኤም” የተባለ እና ጥልቅ የሆነ እንቅልፍ የሚተኙት በቀዝቃዛ ወራቶች ናቸው።
ሰዎች ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ገብተው ሕልም እያለሙ አይኖቻቸው የሚንቀሳቀሱበት የእንቅልፍ ደረጃ ‘ራፒድ አይ ሙቭመንት’ (አርኤኤም) ይባላል። ሰዎች ተኝተው ሕልም ሲያልሙ የልብ ምታቸው ይጨምራል። በጥልቅ ሲተኙ ደግሞ ሰውነታችን ጡንቻዎቻችንን እና ቲሹዎችን ይጠግናል።
ለደቂቃዎች ጋደም ለማለት ይሞክሩ
በበርካታ አገራት በቀን ለትንሽ ደቂቃዎች ጋደም ማለት የተለመደ ባሕል ነው።
ብዙ ጥናቶች ለደቂቃዎች ጋደም ማለት (ናፕ መውሰድ) ለጤና ጠቃሚ መሆናቸውን ያሳያሉ።
እአአ 2023 ላይ የተሰራ አንድ ጥናት በቀን ጋደም የማለት ልማድ ማዳበር አእምሮን ረዘም ላለ ሰዓት ንቁ ሆኖ እንዲቆይ ከማስቻሉም በላይ የአእምሮ ማርጀትን ከሦስት እስከ ስድስት ዓመት እንዲዘገይ ማድረግ እንደሚችል አሳይቷል።
ከ15 ዲቀቃ ያልበለጠ ናፕ መውሰድ ለተከታታይ ሦስት ሰዓታት አእምሯችን ንቁ እንዲሆን ሆኖ እንዲቆይ ማስቻሉን በአሜሪካ የተሰራ ጥናት አሳይቷል።
ሰዎች ለትንሽ ደቂቃ ጋደም ሲሉ መገንዘብ ያለባቸው ሁለት መሰራታዊ ነገሮች አሉ። ይህም እንቅልፉ ከ20 ደቂቃ መብለጥ የለበትም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከ20 ደቂቃዎች በኋላ ጭልጥ ወዳላው የእንቅልፍ ደረጃ ስለምንሸጋገር ነው።
ሁለተኛው መታወቅ ያለበት ደግሞ ከሰዓት ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች የምንወስዳት ናፕ ከምሽት እንቅልፋችን ጋር መጋጨት አይኖርበትም።
የማንቀላፋት አደጋን ይገንዘቡ
ሁሉም እንቅልፍ ጠቃሚ አይደለም። አንዳንድ ማንቀላፋቶች ለሽርፍራፊ ሴኮምዶች የሚቆዩ ናቸው። ታዲይ እኚህ ማንቀላፋቶች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ማሳያ እያሸከረከርን ማንቀላፋት ነው።
አንድ የጃፓን ኩባንያ በ52 የከባድ ተሸነርካሪዎች ላይ ካሜራ ከገጠመ በኋላ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ሹፌሮች ከመጋጨታቸው በፊት የማንቀላፋት ምልክት አሳይተው ነበር።
ማይክሮስሊፕስ ወይም ማንቀላፋቶች ምሽት ላይ በቂ እንቅልፍ በማያገኙት ላይ ይበረታል። ቀን ላይ እንቅልፍ እንቅልፍ የሚልዎ ከሆነ ምሽት ላይ በቂ እንቅልፍ እያገኙ እንዳልሆነ ማሳያ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተመቻችቶ ለመተኛት መሞከር
ብዙዎች ለብቻቸው ተደላድለው ሌሎች ደግሞ በሌሎች ጋር ታቅፈው መተኘትን ምርጫቸው ያደርጋሉ።
ለብዙዎች በራሳቸው አልጋ ለብቻቸው መተኛት ቀላል አይደለም። ቀደም ባለው የሕይወት ዘይቤ ሰዎች ከወንድም እህቶቻቸው አልያም ከትዳር አጋራቸው ጋር ብቻ ሳይሆን ከማያውቁ ግለሰብ ጎን ተኝቶ ማድር የግድ ይሆንባቸው ነበር።
ለአንዳንዶች ይህ ምቾት የሚነሳ ከመሆኑም በላይ ለእንቅልፍ እጦት ምክንያት ሊሆን ይችላል።
አንዳንዶች ደግሞ ታቅፈው መተኛት ምቾት ይፈጥርላቸዋል።
ምቹ ለሆኑት ዘመናዊ አልጋዎች ምስጋና እንስጥ
ዛሬ ላይ በተለይ በምዕራቡ የዓለም ከፍል የሚኖሩ ሰዎች ምቹ በሆኑ ፍራሾች ወይም ባለስፕሪንግ ሚሞሪ ፎም ላይ ጎናቸውን ማሳረፍ ችለዋል።
የቀደመው ትውልድ ግን ከእንቅልፉ የሚነሳው ከሚጎረብጠው የሳር ፍራሽ ላይ ነው። እነዚህ ከሳር የሚሰሩ ፍራሾች ምቾት አልባ ከመሆናቸውም በላይ የተባዮች መደበቂያ ናቸው።
እንቅልፍ አጥተን ከተቸገርን ምክንያቱ አልጋችን ሊሆን ይችላል።
ይህም ብቻ አይደለም። በሕይወታችን የተሻለ እንቅልፍ እንዲኖረን ከብዛት ይልቅ ለጥራት ትኩረት መስጠት ይገባናል።
ባለሙያዎች አንድ ሰው በቀን ከ7 እስከ 9 ሰዓታት መተኛት ይኖበታል ቢሉም ለምን ያክል ሰዓት መተኛት አለብን የሚለው እንደየ ግለሰቡ ፍላጎት ሊበዛ እና ሊያንስ ይችላል። ረዥም ሰዓት በአልጋ ላይ ከመቆየት ይልቅ ላነሱ ሰዓታት ጥሩ እንቅልፍ ማግኘት የተሻለ ነው።












