ሐሜት ወዳጅነትን ለማጠናከር እና ተጽእኖ ለመፍጠር ያግዛል - አጥኚዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስማችሁን ሊያጠፋ ይችላል። ባህሪያችሁን የመሸርሸር አቅም አለው። ያዝናናል። በብዙዎች ዘንድ ግን "ኃጢያት" ነው።
ሐሜት ከገጠር እስከ ከተማ በአብዛኛው ማኅበረሰብ ባህል ውስጥ የሚስተዋል ባህሪ እንደሆነ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
በዋሽንግተን ስቴት ዩኒቨርስቲ የዝግመተ ለውጥ ተመራማሪ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ኒኮል ሄገን ሄስ "ከሁኔታዎች አንፃር ሁሉም ሰው በየትኛውም ባህል ሊያማ ይችላል" ይላሉ።
ስለ ሐሜት ስናስብ ተንኮል በማሰብ ስለ ሰው ማውራትን ልናስብ እንችላለን። ነገር ግን ዶ/ር ሄስ ከዚህ የሰፋ ዕይታን ያነሳሉ። ሐሜት ማንኛውም "ከስም [ዝና] ጋር የተያያዘ መረጃ" መለዋወጥ ነው ይላሉ።
ይህም ማለት ወዳጆች፣ ቤተሰቦች፣ ባልደረቦች ወይም ደግሞ ተቀናቃኞች ስለ እኛ የሚያወሩት ነው። ነገር ግን ይህ በዜና ዘገባዎች አሊያም በስፖርት ውድድር ውጤቶች የሚባለውንም ያካትታል ይላሉ።
"በእኔ ትርጓሜ እየታማ ያለ ሦስተኛ ወገን በቦታው አለመኖር ላያስፈልግ ይችላል፤ ፊት ለፊት አብረው እያለም ሊታማ ይችላል" በማለት ያብራራሉ።
"ስለ እነርሱ እያወራችሁ ከሆነ ስለ አለባበሳቸው ማሰብ ወይም ስለ ሠሩት ነገር ማሰብ ይህ ለእኔ ሐሜት ነው" ይላሉ።
ነገር ግን የሰው ልጆች በእንደዚህ ዓይነት ባህሪ የተጠመዱት ለምንድን ነው? በሚለው ጥያቄ የዚህ ዘመን ተመራማሪዎችም እየተጨነቁበት ያለ ጉዳይ ነው።
አንዳንድ ቁልፍ ፅንሰ ሀሳቦች እናንሳ።
ወዳጅነት መመሥረቻ
በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ሐሜት አዎንታዊ ሚና አለው የሚለውን ሀሳብ ያስተዋወቁት የዝግመተ ለውጥ አንትሮፖሎጂ አጥኚ የሆኑት ፕሮፌሰር ሮቢን ዱንባር ናቸው።
በእርሳቸው ፅንሰ ሀሳብ መሠረት ራስን መጠበቅ የማኅበረሰብ ባህሪ ከመሆኑ በተጨማሪ የግል ንፅህና መጠበቂያ ነው። ከትስስር ጎን ለጎን ከግጭት በኋላ ለመታረቅ፤ ውጥረትን ለማርገብ እና የማኅበረሰብ ተዋረዳዊ ቦታን ለመመደብ ይውላል።
ይህም ሂደት ማኅበረሰባዊ መተሳሰሪያ ይባላል።
ነገር ግን የሰው ልጅ መያዣ ስሌለው ሐሜት እና ወሬ ግንኙነትን ለመመሥረት፣ የአንድን ሰው አቻዊ ቦታ ለመገንባት እና ማንን ማመን እንዳለብን እና እንደሌለብን ለማወቅ፣ ማኅበረሰባዊ መረጃ በመለዋወጥ የዘመናዊው ሰው ማኅበረሰባዊ መጠባበቂያ አድርገን ልናየው እንችላለን።
ለፕሮፌሰር ዱናበር ቋንቋ በራሱ ሰዎች እንዲያሙ ሲባል ተሻሽሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያኑ 2021 በአሜሪካ በሚገኘው ዳርትማውዝ ዩኒቨርስቲ በተደረገ ጥናት ተመራማሪዎች አብረው የሚያሙ ሰዎች አንዱ በሌላው አመለካከት ላይ ተፅዕኖ ማሳረፋቸው ብቻም ሳይሆን በሂደቱም ወዳጅነታቸው ይጠናከራል ብለዋል።
"ተሳታፊዎች እርስ በእርስ የጋርዮሽ ስሜት አዳብረዋል ብለን እንገምታለም። የማኅበረሰብ ትስስር የማግኘት ፍላጎታቸውን እያረኩ አንዳቸው የሌላቸውን ባህሪ እና ዕይታ ተፅዕኖ የሚያደርግ 'የጋራ ዓለም' ይፈጥራሉ" ሲሉ ተመራማሪዎች በጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።
በተጨማሪም ሐሜት በቡድን ውስጥ ትብብርን እንደሚያሳድግ ተገንዝበዋል። የጥናቱ ተሳታፊዎች በቡድን ጨዋታዎች እርስ በርስ ለማውራት ሲሉ ተጨማሪ ገንዘብ ለማውጣት ፈቃደኛ ናቸው።
"ሐሜት አንድ ዓይነት ስሪት አይደለም። እና በሕዝባዊ እሳቤዎች መሠረተ ቢስ፣ የማይረባ ወሬ ተብሎ ከሚንፀባረቀው ጠባብ ፍቺ በበለጠ የተወሳሰበ ነው" ሲሉ ተመራማሪዎቹ ደምድመዋል።
ተራ ተርታ ሰዎች ሐሜታቸውን የሚያጋሩበት 'ኖርማል ጎሲፕ' የሚል ፖድካስት አቅራቢ የሆነችው ኬልሲ ሚክኪኒ ጮማ ወሬዎች የማይተዋወቁ ሰዎችን እንደሚያቀራርብ ጠንቅቃ ታውቃለች።
የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተ ጊዜ እና ሰዎች ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ ሲገደዱ፣ ወሬ የማግኘት ፍላጎት የበለጠ ከፍ አለ።
"እንደተራብን ገባኝ" ትላለች።
"አብዛኛውን ሕይወታችንን እና ዓለምን የምናስተውልበት መንገድ የሚገነባው ለራሳችን በምንነግረው ትርክት ነው፤ እና ወሬ ደግሞ ትርክቱ ነው። እርስ በርሳችን ስለራሳችን እናወራለን፤ ይህ አደጋ ቢኖረውም ብዙ ጥሩ ነገሮችም አሉት" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሕልውና
የሰው ልጅ ራሱን እና በዙሪያው ያሉት ሰዎች ላይ ሊከሰት ከሚችል ጉዳት እንዴት በደንብ መጠበቅ እንደሚችል በሚሊዮኖች ዓመታት የተሻለ መንገድ ፈጥሯል።
ለአንዳንድ ሴቶች በተለይ እንደ አደገኛ የፍቅር ግንኙነት ያሉ ስጋቶችን ለመቅረፍ ሐሜት ችግርን የመወጣጫ ስልት ወሳኝ መሳሪያ ነው።
ዶ/ር ኒኮል ሄገን ሄስ "ሴቶች ከወንዶች ጋር ፀብ ውስጥ ሲገቡ በአካለ መጠናቸው አነስተኛ በመሆናቸው ተጎጂ ናቸው። ስለዚህ በተለይ ለሴት ዘመዶቻቸው እና ለቅርብ ሴት ጓደኞቻቸው መረጃውን ማጋራት ጠቃሚ ነው" ይላሉ።
በሕይወት መቆየት እና በማኅበረሰቡ ያለን ስፍራ በስም ወይም በዝና ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የተመሠረተ ነው።
"መጥፎ ስም መስጠት አስከፊ ሊሆን ይችላል" ይላሉ ዶ/ር ሄስ ሲያብራሩ። በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለዎትን ስፍራ ሊጎዳ ይችላል፤ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ሊገድብ አልፎ ተርፎም እንደ ምግብ ያሉ ሀብቶችን የማግኘት ዕድልን ሊጎዳ ይችላል። "ስለዚህ ሰዎች ስለ እናንተ አሉታዊ ወሬ ሲያወሩ፤ በእርግጥ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል" ይላሉ።
ዶ/ር ሄስ ሐሜት በማኅበራዊ ተዋረድ ውስጥ የራስን ስፍራ ለመጠበቅ ወይም ለማሻሻል ጥቅም ላይ የሚውል የማኅበራዊ ቁጥጥር መንገድ ወይም ዓይነት ነው ሲሉ ይከራከራሉ።
ሰዎች በማኅበራዊ ግንኙነታቸው ውስጥ እንዴት እንደሚታዩ መቆጣጠር ይሞክራሉ። ስለዚህ እርስ በርሳቸው ለመቆጣጠር በሐሜት ይሳተፋሉ ይላሉ። ዶ/ር ሄስ አክለውም ሰዎች የራሳቸውን ስም ለመጠበቅ እና አንዳንዴም ተቀናቃኞችን ለመጉዳት ሐሜትን እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ።
"ሰዎች በተፈጥሮ ተፎካካሪ ናቸው። እናም ግጭትን የምናስወግደው ነገር አይደለም" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መዝናኛ
በአብዛኛው ሰው ሐሜት ጉዳት አልባ ጨዋታ ተደርጎ ይወሰዳል።
የፖድካስት አቅራቢ የሆነችው ሚክኪኒ "እንደዚህ ዓይነት ሐሜት ላይ ነው እኔ የምሠራው" ትላለች።
የእርሷ መደነቅ፤ ታሪክ ለመንገር ያላት ፍቅር እንዲሁም ባደገችበት አክራሪ ሃይማኖተኛ ቤተሰብ ሐሜት ኃጢያት ተደርጎ መታየቱ ለሥራዋ ምንጭ ነው።
"ትልቁ የሐሜት ክፍል ወዲያው ከአፍ ወጥቶ ለሌላ ሰው የሚነገር ነው" ትላለች።
እና ዓለም ያለ ሐሜት? "ደባሪ ናት" በማለት ትስቃለች።
ለመዝናናት፣ ለህልውና ወይም ለማኅበራዊ ትስስርም ቢሆን ወሬ በሕይወታችን ውስጥ የማያቋርጥ ነው። "የሰው ዓለም አቀፋዊነት" መገለጫ በመሆኑ መወገድ የሌለበት ነው ይላሉ ዶ/ር ሄስ።
"ሐሜት በገሃዱ ዓለም መዘዝ አለው" ሲሉ ያብራራሉ። የዘፈቀደ፣ እውነት ያልሆነ፣ መደበኛ ያልሆነ ንግግር ባይኖር ኖሮ ሰዎች ለሌሎች የማኅበረሰባቸው አባላት ጥቅማ ጥቅሞችን ለመመደብ በሚወስኑበት ጊዜ ያለው ተፅዕኖ አይኖርም ነበር"።












