ቢቢሲ ትራምፕን በይፋ ይቀርታ ሲጠይቅ ካሳ ግን እንደማይከፍል አሳወቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters / AFP via Getty Images
ቢቢሲ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እአአ ጥር 6 ቀን 2021 ያደረጉትን ንግግር ፓኖራማ ለተሰኘው ዝግጅቱ ካቀረበበት መንገድ ጋር በተያያዘ ይቅርታ ቢጠይቅም የካሳ ጥያቄያቸውን ግን ውድቅ አደረገ።
ፓኖራማ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለዓመፅ ቀጥተኛ ጥሪ እንዳደረጉ የተሳሳተ ግንዛቤ" እንደሰጠ እና ዝግጅቱን በድጋሚ እንደማያሳይ ኮርፖሬሽኑ ተናግሯል።
የትራምፕ ጠበቆች ኮርፖሬሽኑ ዝግጅቱን ካልሰረዘ፣ ይቅርታ ካልጠየቀ እና ካሳ ካልከፈለ ቢቢሲን በአንድ ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንደሚከሱ ማሳወቃቸው ይታወሳል።
የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪ እና የዜና ኃላፊዋ ዴቦራ ተርነስ እሑድ ዕለት በፕሮግራሙ ምክንያት ከስራ እንዲለቁ ሆኗል።
ቢቢሲ ኒውስ አስተያየት ለማግኘት ለዋይት ሐውስ ጥያቄ አቀርቧል።
ይቅርታው የተጠየቀው በ2022 በኒውስናይት ላይ ተመሳሳይ ማስተካከያ የተደረገበት ቪዲዮ መተላለፉን ዴይሊ ቴሌግራፍ ካሳወቀ ከሰዓታት በኋላ ነው።
ቢቢሲ ሐሙስ ምሽት በታተመው የእርምት እና የማብራሪያ ክፍል የፓኖራማ ፕሮግራሙ የትራምፕ ንግግር የቀረበበትን መንገድ መገምገሙን አስታውቋል።
"በአርትኦት ወቅት በንግግሩ ውስጥ ከተለያዩ ነጥቦች የተወሰዱ ቪዲዮዎችን ብንጠቀምም፣ ወጥ የሆነ ንግግር እያሳየን እንደሆነ እና ይህም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለዓመፅ ቀጥተኛ ጥሪ እንዳደረጉ የተሳሳተ ግንዛቤ እንደሰጠ እንቀበላለን" ብሏል።
የቢቢሲ ጠበቆች እሑድ ዕለት ለተቀበሉት ደብዳቤ ምላሽ ለመስጠት ለፕሬዚዳንት ትራምፕ የጠበቆች ቡድን ደብዳቤ ጽፈዋል ሲል የቢቢሲ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
"የቢቢሲ ሊቀመንበር ሳሚር ሻህም በፕሮግራሙ ላይ በቀረበው የፕሬዚዳንቱ ንግግር አርትኦት ዙሪያ ይቅርታ እንደሚጠይቁ በመግለጽ ለዋይት ሐውስ የግል ደብዳቤ ልከዋል" ብለዋል።
በማከልም "ቢቢሲ ቪዲዮውን የተስተካከለበትን መንገድ በተመለከተ ከልብ ቢጸጸትም፤ ለስም ማጥፋት የተደረገ ነው የሚለው ክስ መሠረት ቢስ በማለት አጥብቀን እንቃወማለን።"
ትራምፕ በንግግራቸው "ወደ ካፒቶል እንሄዳለን። እና ደፋር ሴናተሮቻችንን፣ የኮንግረስ አባላቶቻችንን እናበረታታለን" ብለዋል።
ንግግራቸውን ቀጥለው ከ50 ደቂቃዎች በኋለ ደግሞ "እናም እንታገላለን። በጀግንነት እንታገላለን" ሲሉ አክለዋል።
በፓኖራማ ፕሮግራም ላይ የሚታየው ቪዲዮ ሁለቱን በማዋሃድ "ወደ ካፒቶል እንሄዳለን... እኔም ከእናንተ ጋር እሆናለሁ። እናም እንታገላለን። በጀግንነት እንታገላለን" በሚል አቅርቦታል።
ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ንግግራቸው "መበለቱን" እና የቀረበበት መንገድ ተመልካቾችን "ያጭበረበረ ነው" ብለዋል።
ቢቢሲ እሑድ ዕለት ነበር ከትራምፕ ጠበቆች ደብዳቤውን የተቀበለው። ዘጋቢ ፊልሙን "ቪዲዮውን ሙሉ በሙሉ ማንሳት፤ ይቅርታ መጠየቅ እና" ቢቢሲ "ለተከሰተው ጉዳት ፕሬዝዳንት ትራምፕን በአግባቡ መካስ" አለበት ይላል።
ኮርፖሬሽኑ አርብ ዕለት ምላሽ እንዲሰጥ የጊዜ ገደብም አስቀምጧል።
ቢቢሲ ለትራምፕ የሕግ ቡድን በጻፈው ደብዳቤ አምስት ዋና ዋና ጭብጦችን አስቀምጧል።
የመጀመሪያው ቢቢሲ የፓኖራማ ፕሮግራምን በአሜሪካ ቻናሎቹ ላይ የማሰራጨት መብት እንደሌለው እና እንዳላደረገው ተናግሯል።
ዘጋቢ ፊልሙ በቢቢሲ አይፕሌየር ላይ ሲሰራጭም በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ላሉ ተመልካቾች ብቻ ተገድቦ ነበር።
በሁለተኛ ደረጃ ዘጋቢ ፊልሙ ትራምፕ ላይ ጉዳት እንዳላደረሰ አስታውቆ ፕሬዝዳንቱ በድጋሚ መመረጣቸውን በምክንያትነት ጠቅሷል።
በሦስተኛ ደረጃ ቪዲዮው ለማሳሳት ሳይሆን ረጅም ንግግርን ለማሳጠር ብቻ የተቆረጠ እንጂ ማስተካከያው በክፋት የተደረገ እንዳልሆነ አስታውቋል።
አራተኛው ምክንያት ደግሞ ቪደዮው ለብቻው መታየት እንደሌለበት ጠቅሷል። ይልቁንም ከአንድ ሰዓት ፕሮግራም ውስጥ የ12 ሰከንዶች ቪዲዮ መሆኑን እና ፕሮግራሙ ትራምፕን የሚደግፉ ብዙ ድምጾችን መያዙንም አሳውቋል።
በመጨረሻም በሕዝብ እና በፖለቲካዊ ሐሳብ ላይ የሚሰጥ አስተያየት በአሜሪካ ሕጎች መሠረት በጥብቅ የተጠበቀ ነው ብሏል።
አንድ የቢቢሲ የውስጥ አዋቂ እንደገለጸው ከሆነ ኮርፖሬሽኑ ባቀረበው ጉዳይ እና በመከላከያው ላይ ጠንካራ እምነት አለው።
አዲስ የተሳሳተ አርትኦት ጥያቄ
ሐሙስ ዕለት ቢቢሲ የትራምፕን የጥር 6 ቀን 2021 ንግግር በተሳሳተ አርትኦት አሰራጭቷል ተብሎ ተከሷል። ይህም የፓኖራማ ፕሮግራም ከመተላለፉ ሁለት ዓመታት በፊት መሆኑ ተጠቅሷል።
በ2022 በተዘጋጀው የኒውስናይት ፕሮግራም ላይ አርትኦቱ ከፓኖራማ ትንሽ የተለየ ሆኖ ቀርቧል።
ትራምፕ "ወደ ካፒቶል እንሄዳለን። እናም ደፋር ሴናተሮቻችንን እና የኮንግረስ አባላቶቻችንን እናበረታታለን። እናም እንታገላለን። በጀግንነት እንታገላለን። በጀግንነት ካልተዋጋችሁ አገር አይኖራችሁም" እንዳሉ ሆኖ ቀርቧል።
ከዚያም አቅራቢዋ ኪርስቲ ዋርክ በካፒቶል የነበረውን ረብሻ በሚታይበት ወቅት "እናም ተዋጉ" ስትል ይሰማል።
ፕሮግራሙ ላይ ለቀረበው ለቪዲዮ ምላሽ የሰጡት የቀድሞው የዋይት ሐውስ ኃላፊ የነበሩት እና የካፒቶልን አመጽ "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ" ሲሉ ከገለጹ በኋላ የትራምፕን ተቺ የሆኑት ሚክ ሙልቫኒ ቪዲዮው የትራምፕን ንግግር "ቆራርጦ የቀጠለ" መሆኑን ተናግረዋል።
"'በጀግንነት እንታገላለን' የሚለው አባባል በንግግሩ ወደ ኋላ የሚገኝ ቢሆንም ቪዲዮው ግን እነዚህ ሁለት ነገሮች አንድ ላይ እንደተነገሩ አድርጎ አቅርቧል" ብለዋል።
ሐሙስ ዕለት በቴሌግራፍ ላይ ስለወጣው ዘገባ የቢቢሲ ቃል አቀባይ ሲመልሱ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።















