በእርጅና ጊዜ ሥጋ እና የእንስሳት ተዋጽዖዎችን አለመመገብ ጠቃሚ ይሆን?

ሥጋ

የምንመገበው ምግብ ውስጥ ሥጋ እና የእንስሳትን ተዋጽዖዎች በምን ያህል መጠን ማካተት ይገባናል የሚለው አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።

በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፆም ምግብ የሚባለው ከሥጋ እና ከእንስሳት ተዋጽዖዎች ውጪ የሆነው (ቬጋን) አመጋገብ አንዳንዶች ሁሉም ሊከተሉት የሚገባ የኑሮ ዘዬ ነው ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ ይህንን አመጋገብ በጥንቃቄ ይመለከቱታል።

ሥጋ እና የእንስሳት ተዋጽዖዎችን አለመመገብ ጠቃሚ የሚሆነው በሁሉም ዕድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ሰዎች ነው? ወይስ በእርጅና ወቅት? የሚለውም አከራካሪ ነው።

በቅርቡ በዩናይትድ ኪንግደም የሚታተመወ ቢኤምሲ ሜዲሲን የተሰኘው መጽሔት በፆም ምግቦች መወሰን ሊኖረው የሚችለውን የጤና በተለይም እርጅናን በማዘግየት ረገድ ያለውን ጠቀሜታ አስመልክቶ አወዛጋቢ ምርምር አውጥቷል።

ባለሙያዎች ጥናቱ አነስተኛ በሆኑ ናሙናዎች ላይ የተመሠረተ እና ውስን በሆነ ጊዜ የተካሄደ ከመሆኑ አንጻር በግኝቶቹ ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ቢመክሩም፤ ነገር ግን ክርክሩን እንደ አዲስ እንዲቀሰቀስ ማድረጉ አልቀረም።

አትክልት እና ፍራፍሬዎች

የፎቶው ባለመብት, David Davies/PA Wire

ለአረጋውያን “በፆም ምግቦች” መወሰን ስጋት አለው?

በለንደን የኪንግስ ኮሌጅ ባልደረባ የሆኑት የሥነ ምግብ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ቶም ሳንደርስ የጥናቱን ግኝቶች በመጠራጠር ሥጋ እና የእንስሳት ተዋጽዖዎችን አለመመገብ በዕድሜ ለገፉ ሰዎች መጥፎ ሊሆን እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

“ሥጋ እና የእንስሳት ተዋጽዖዎችን ከአመጋገባቸው ያስወገዱ አረጋውያን በጡንቻ መዛል፣ በአጥንት መሳሳት እና በነርቭ ሕመሞች በበለጠ እንደሚሰቃዩ መመልከት ተችሏል” ይላሉ።

አክለውም “ሥጋ እና የእንስሳት ተዋጽዖዎችን የማይመገቡ አረጋውያን ከሚጠበቅባቸው ክብደት በታች ናቸው። በተጨማሪም ለአጥንት መሰበር ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው።

በሥጋ እና በእንስሳት ተዋጽዖዎች ውስጥ የሚገኙት ካልሲየም እና ፕሮቲን ዝቅተኛ በመሆኑም ለዚህ አስተዋጽኦ ያደርጋል” በማለት ተመራማሪው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በሰውነት ውስጥ የአይረን እና የዚንክ ማዕድናት የመዋሀድ መጠን ዝቅተኛ መሆን ሥጋ እና የእንስሳት ተዋጽዖ በማይመገቡ ሰዎች ላይ ችግር ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ሆኖም ጥራጥሬዎች፣ የእህል ተዋጽዖዎችን፣ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን በመመገብ ማስተካከል እንደሚቻልም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ፕሮፌሰር ሳንደርስ ሥጋ እና የእንስሳት ተዋጽዖዎችን ያለመመገብ የጤና ጠቀሜታን ከሌሎች የአመጋገብ ልማዶች ጋር በሚያነጻጽሩበት ወቅት የተለዩ የጤና ጠቀሜታዎች የሉትም ይላሉ።

“ሥጋ እና የእንስሳት አስተዋጽዖን የማይመገቡ ሰዎች አጠቃላይ ጤና ሁሉንም ከሚመገቡ የተለየ አይደለም በሚለው እጸናለሁ” ይላሉ።

በአመጋገብ ላይ አማካሪ የሆነው ኢንሱሊያን የተሰኘ ድርጅት ያላቸው እና የሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ንያምቡራ እምቡሩም በተመሳሳይ መልኩ ከሥጋ እና ከእንስሳት ተዋጽዖዎች ውጪ የሆነው አመጋገብ ላይ የራሳቸው ጥርጣሬ አላቸው።

ዶክተሯ ማመጣጠን ቁልፍ ነገር ነው ይላሉ።

“የእጸዋት፣ የሥጋ እና የእንስሳት ተዋጽዖ ምግቦች የያዟቸው ንጥረ ነገሮች የተለያዩ ናቸው። ለዚያም ነው እንደ ንጥረ ነገሮች ምንጭነት ከመወዳደር ይልቅ እርስ በርስ መደጋገፍ የሚገባቸው” ይላሉ።

የአረጋዊ እጅ

የፎቶው ባለመብት, PA

ከሥጋ እና ከእንስሳት ተዋጽዖ ነጻ የሆነ አመጋገብ ጥቅም

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዩናይትድ ኪንግደም የሆድ ዕቃ ጤና ባለሙያ (ጋስትሮኢንተሮሎጂስት) የሆኑት ዶክተር አላን ዴዝሞንድ በበኩላቸው ከሥጋ እና ከእንስሳት ተዋጽዖ ነጻ የሆነ አመጋገብ ጠቀሜታን በተመለከተ ንግግሮችን ያደርጋሉ እንዲሁም የተለያዩ ጽሁፎችን አሳትመዋል።

እሳቸው እንደሚሉት አረጋውያን ከሥጋ እና ከእንስሳት ተዋጽዖዎች ነጻ የሆነ አመጋገብን እንዲከተሉ ምክር የሚሰጡ ሲሆን፣ ጥቅሞቹም ችላ የሚባሉ አይደሉም ይላሉ።

“ከሥጋ እና ከእንስሳት ተዋጽዖዎች ነጻ የሆነ አመጋገብ በየትኛውም ዕድሜ ጠቃሚ ነው። በዕድሜ ስንገፋ ስጋት የሚሆኑብን እንደ ልብ ሕመም፣ የስኳር በሽታ እና በካንሰር የመያዝ ዕድልን ይቀንሰዋል። በየትኛውም ዕድሜ ከሥጋ እና ከእንስሳት ተዋጽዖዎች ነጻ ወደሆነ አመጋገብ ለመሸጋገር አልረፈደም” ይላሉ።

ሆኖም ዶክተር ዴዝሞንድ ከሥጋ እና ከእንስሳት ተዋጽዖዎች ነጻ የሆነ አመጋገብን የሚከተሉ አረጋውያን መሠረታዊ የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን ሊያስቡባቸው ይገባል ይላሉ።

“ጤናማ ሆነው ለመቆየት የሚፈልጉ ማናቸውም ሰዎች በፕሮቲን የበለጸጉ ጥራጥሬዎችን እና እህሎችን ሊመገቡ ይገባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የቫይታሚን ቢ-12 ተጨማሪ እንክብሎችን መውሰድ እንዲሁም የአጥንት ጤንነት ለመጠበቅ እና የጡንቻ መዛል እንዳያጋጥም ክብደት ከማንሳት ጋር የተያያዙ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይገባል” ይላሉ።

ቫይታሚን ቢ-12 ለሰውነታችን መሠረታዊ ከሚባሉት ንጥረ ነገሮች አንዱ ነው። ንጥረ ነገሩ በብቸኝነት የሚገኘው ከሥጋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም በርካታ ባለሙያዎች ሥጋን የማይበሉ ሰዎች እንደማያገኙ በተደጋጋሚ የሚጠቅሱት ጉዳይ ነው።

የቫይታሚን ቢ-12 እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት በሰውነታችን እና በአእምሯችን ላይ የተለያዩ ተጽእኖዎችን ያስከትላል። ከሚጠቀሱትም መካከል ድካም፣ የጡንቻ መዛል፣ ድብርት እና ግራ መጋባትን ያስከትላል።

እነዚህ ምልክቶች በዕድሜ አረጋውያን በሆኑት ላይ የበለጠ እንደሚጎሉ እና አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይናገራሉ። በአንድ ጥናት ላይ ደግሞ የቫይታሚን ቢ-12 እጥረት ለስትሮክ የመጋለጥ አደጋን ከመጨመሩ ጋር ተመራማሪዎች አያይዘውታል።

ሌላኛው የሚነሳው ጉዳይ በእንቁላል፣ በወተት እና በበሬ ሥጋ ላይ በብዛት የሚገኘው ቾሊን የተሰኘው ንጥረ ነገር ነው።

ቾሊን በነርቭ ህዋሳት መካከል መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ስለሚያግዝ እንዲሁም ከጤናማ የኩላሊት ተግባር ጋር ስለሚገናኝ የሥጋ እና የእንስሳት ተዋጽዖዎችን የማይመገቡ ሰዎች ንጥረ ነገሩን ቸል ሊሉት እንደማይገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ቾሊን በጽንስ የአእምሮ ዕድገት ላይ ጠቀሜታ ስላለው ለነፍሰ ጡር ሴቶች መሠረታዊ የሚባል ንጥረ ነገር መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ። እንደ ዕድል ሆኖ ይህ ንጥረ ነገሩ እንደ ብሮኮሊ፣ ኦቾሎኒ፣ እንጉዳይ ባሉ ምግቦች ላይም ይገኛል።

ከሥጋ እና ከእንስሳት ተዋጽዖ ነጻ የሆነ ምግብ መመገብ ተፈጥሯዊ ሃብቶችን በመጠበቅ ረገድ እንዲሁም ዘላቂነት እና ርህራሄ የተሞላበት ዓለም እንዲፈጠር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ዶክተር ዴዝሞንድ ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ሥጋ እና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን የማይመገቡት ከጤና ስጋቶች ወይም ካላቸው መርሆች ጋር በተገናኘ ላይሆን ይችላል።

በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ አረጋውያን ሕሙማን በሆስፒታሎች ውስጥ ከአመጋገባቸው ጋር በተያያዘ የአይረን እጥረት እና ሌሎች የጤና እክሎች እንዳሉባቸው ታይቷል።

እነዚህ አረጋውያን ሥጋ እና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን የማይመገቡት ከሞራል አንጻር ሳይሆን የትዳር ጓደኞቻቸው በሞት ከተለይዋቸው እና ብቻቸውን የሚኖሩ ከሆነ ምግብ ለማዘጋጀት ፍላጎት ከማጣት ሊሆን ይችላል ይላሉ።

በተጨማሪም የሥጋ እና የዓሳ ምርቶች ዋጋ መወደድ እና በገበያ መደብሮች ሄዶ የመግዛት አካላዊ ችግር የራሱ የሆነ አሉታዊ አስተዋጽዖ አድርጓል ይላሉ።