ዋይት ሐውስ የቲክቶክን የአልጎሪዝም ቁጥጥር ለአሜሪካ የሚሰጥ እቅድ ነደፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዋይት ሐውስ ቪዲዮ እየመረጠ ለተጠቃሚዎች የሚያቀርበውን የቲክቶክ አልጎሪዝም የአሜሪካ ኩባንያዎች እንደሚቆጣጠሩት አስታውቋል።
ከቻይና ጋር በሚደረገው ድርድር የመተግበሪያው የአሜሪካ እንቅስቃሴን በተመለከተ ከሰባቱ የቦርድ አባላት ስድስቱ አሜሪካውያን እንደሚሆኑም ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጿል።
የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ካሮላይን ሌቪት ስምምነቱ "በሚቀጥሉት ቀናት" እንደሚፈረም ያሳወቁ ቢሆንም፤ እስካሁን ግን ቤዢንግ አስተያየት አልሰጠችም።
አሜሪካ የተንቀሳቃሽ ምስል ማጋሪያ መተግበሪያውን ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት በሚል መቀመጫውን ቻይና ካደረገው የመተግበሪያው ባለቤት ባይትዳንስ ኩባንያ ለመቀበል ስትጥር ቆይታለች።
ቲክቶክ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ሥራውን እንዲሸጥ አሊያም እንደሚዘጋ መነገሩ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የመዘጋቱ ዜና ከተሰማ ካለፈው ዓመት ጥር ወር ወዲህ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተፈፃሚነቱን አራት ጊዜ ያዘገዩ ሲሆን በዚህ ሳምንትም የተቀመጠውን ቀነ ገደብ እስከ ታኅሳስ ድረስ አራዝመዋል።
የፕሬስ ስክሬታሪዋ በአሜሪካ የመተግበሪያው የመረጃ እና ግላዊነት አስተዳደር የዓለማችን ባለሀብት እና የትራምፕ አጋር በሆኑት ላሪ ኤልሰን ሊቀ መንበርነት የሚመራው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ኦራክል እንደሚተዳደር ተናግረዋል።
"መረጃው እና ግላዊነቱ በአሜሪካ ታላቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ኦራክል ይመራል። አልጎሪዝሙም በአሜሪካ ቁጥጥር ስር ይሆናል" ሲሉ ለፎክስ ኒውስ አስታውቀዋል።
"እነዚህ ሁሉ ዝርዝሮች ስምምነት ተደርሶባቸዋል። አሁን ይህ ስምምነት እንዲፈረም ነው የምንጠብቀው" ብለዋል።
ትራምፕ አርብ እለት እርሳቸው እና የቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ቲክቶክ በአሜሪካ በሚኖረው ሥራ ዙሪያ በስልክ ባደረጉት ንግግር ስምምነቱን ማፅደቃቸውን አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ ቤዢንግ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠችም።
ትራምፕ ትሩዝ በተባለው የማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ንግግሩን "ፍሬያማ" ያሉት ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት ዢ ስምምነቱን በማፅደቃቸው "አድናቆት" እንደተሰማቸው ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም ትራምፕ ቲክቶክ ለአሜሪካ ባለሀብቶች እንዲሸጥ ሲወተውቱ ቆይተዋል።
ቅዳሜ ዕለት የቻይና ንግድ ሚኒስቴር የስምምነቱን ሁኔታ በሚመለከት ግልፅ ያልሆነ መግለጫ አውጥቷል።
"በቲክቶክ ጉዳይ የቻይና አቋም ግልፅ ነው። የቻይና መንግሥት የኩባንያውን ፍላጎት ያከብራል። የቻይናን ሕግ እና ደንብ እና የጥቅም ሚዛንን ባከበረ መልኩ መፍትሔ ላይ ለመድረስ የሚያደርገውን የንግድ ስምምነት ይቀበላል" ብሏል።
የቻይና ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የሆነው ዥንዋ የድርድሩን ውጤት በተመለከተ ግልፅ ያልሆነ ዘገባ ያወጣ ሲሆን፤ ዘገባው የፕሬዝዳንትን ዢን ንግግር በመጥቀስ ቤጅንግ "የቲክቶክ ድርድርን ትቀበላለች" ብሏል።
የድርድሩ ትልቁ ክፍል ለ170 ሚሊዮን የአሜሪካ ተጠቃሚዎች ይዘቶችን መርጦ የሚያቀርበውን አልጎሪዝሙን ማን ባለቤት ይሆናል የሚለው ነው።
ባለፈው ሐሙስ ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ጋር መግለጫ የሰጡት ትራምፕ በአንድ ጋዜጠኛ ቲክቶክን የሚገዛው የአሜሪካ ኩባንያ አዲስ አልጎሪዝም ይገነባል ወይስ በነበረው አልጎሪዝም ይቀጥላል ተብለው ቢጠየቁም ጥያቄውን ወደ ጎን ብለዋል።
ምንም እንኳ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ቲክቶክ እንዲታገድ ጥሪ ቢያቀርቡም አሁን አቋማቸውን ቀይረዋል።
በ2024 የፕሬዝዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው የወጣት አሜሪካውያንን ድጋፍ ለማግኘት ቲክቶክን እንደተጠቀሙበት ይታመናል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2024 ባይትዳንስ የአሜሪካ ሥራውን ካልሸጠ መተግበሪያውን ያገደበትን ውሳኔ ባለፈው ጥር ያፀና ሲሆን መተግበሪያ እግዱ እስኪራዘም ድረስ ለጥቂት ሰዓት ተዘግቶ ነበር።
የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ቲክቶክ ከአሜሪካ ተጠቃሚዎች መረጃ አሰባሰቡ ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ነው የሚል ስጋቱን ገልጿል።















