ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአንድ የምሽት ክበብ ከ20 በላይ ታዳጊዎች ሞተው ተገኙ

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአንድ የምሽት ክበብ ተሰብስበው ከነበሩ ታዳጊዎች መካከል ከ20 በላይ የሚሆኑት ሕይወታቸው አልፎ ተገኘ።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት ባልታወቀ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈውን ታዳጊዎችን ሞት ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እያደረጉ መሆናቸው ተገልጿል።
አንዳንዶች ሟቾቹ ተመርዘው ነው ቢሉም አስካሁን ግን በይፋ አልተረጋገጠም።
ልጆቻቸው የጠፉባቸው ወላጆች የልጆቻቸውን የመጨረሻ ዕጣ ለማወቅ በመጠጥ ቤቱ አካባቢ ተሰባስበዋል።
ቀደም ሲል በወጣው ዜና ላይ ሟቾቹ ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ወጣቶች እንደሆኑ ተዘግቦ የነበረ ሲሆን፣ በኋላ ላይ የወጡ መረጃዎች ግን ሟቾቹ እድሜያቸው ከዚያ ያነሰ መሆኑ ተነግሯል።
ከሞቱት መካከል ትንሽ ዕድሜ ያለው 13 ዓመቱ ሲሆን፣ ትልቁ ደግሞ 17 ዓመቱ መሆኑን የፖሊስ ባለሥልጣን የሆኑት ብሄኪ ቼሌ ገልጸዋል፣ ነገር ግን የሟቾቹ ዝርዝር መረጃ ገና ይፋ አልሆነም።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ አልኮል መጠጥ ለመጠጣት ትንሹ ዕድሜ 18 ዓመት ሲሆን፣ ታዳጊዎቹ እንዲጠጡ መፈቀድ አልነበረበትም።
እንደተባለው ልጆቹ ወደ መጠጥ ቤቱ ያመሩት ፈተናቸውን መጨረሳቸውን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ተነግሯል።
የደቡብ አፍሪካ የአልኮል መጠጥ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እንዳለው የመጠጥ ቤቱ ባለቤት ፈቃድ ሲሰጠው የተስማማባቸውን ነጥቦች ጥሷል በሚል እንደሚከሱት ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታዳጊዎቹ ሞተው የተገኙት ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ሲሆን፣ መጠጥ ቤቱ ከዚህ ቀደም ብሎ አካባቢን በመረበሽ በነዋሪዎች አቤቱታ ሲቀርብበት ቆይቷል።
ታዳጊዎቹ በባሕር ዳርቻዋ ትንሽ ከተማ ኢስት ለንደን ውስጥ በሚገኘው የምሽት ክበብ ውስጥ ወለል እና ጠረጴዛዎች ላይ እንዳሉ ሞትው ነው የተገኙት።
በመጠጥ ቤቱ ሙዚቃ የሚያጫውተው ግለሰብ እንደተናገረው ልጆቹ እየጠጡ ሳለ እራሳቸውን እየሳቱ በየተራ ሲወድቁ በአልኮሉ ሰክረው ነው በማለት አሰርቦ ነበር።
ከ20 የሚበልጡት ታዳጊዎች አስክሬንም ምናልባት ተመርዘው እንደሆነ ለማወቅ እንዲሁም ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ወደ ተለያዩ የሕክምና ተቋማት ተወስደዋል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በታዳጊዎቹ ህልፈት የተሰማቸውን “ጥልቅ ሐዘን” ለሟቾቹ ቤተሰቦች ገልጸዋል።
"ይህ አሰቃቂ ሁኔታ የአገራችንን ወጣቶች አጠቃላይ ሁኔታን ለማሻሻል በሚረዱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በምናደርግበት የወጣቶች ወር ላይ መከሰቱ በእጅጉ ያሳዝነናል” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የታዳጊዎቹ ሞት ያጋጠመበት የኢስት ኬፕ ግዛት አስተዳዳሪ የሆኑት ኦስካር ማቡያኔ፣ ለህልፈታቸው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሳይገልጹ “ከልክ ያለፈ የአልኮል መጠጥ አጠቃቅምን” በደፈናው አውግዘዋል።
ባለሥልጣኑ ታዳጊዎቹ ሕይወታቸው አልፎ በተገኘበት የምሽት ክበብ ተገኝተው "በማኅበረሰቡ መካከል ሆኖ እንደዚህ መጠጥ ሲሸጥ ወጣቶች ሊሞክሩት አይችሉም ብሎ ማሰብ አይቻልም" ብለዋል።
አንድ የግዛቲቱ የሕዝብ ጤና ባለሥልጣን ለፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) እንደተናገሩት፣ ለታዳጊዎቹ ሞት በግርግር ውስጥ በተፈጠረ መረጋገጥ ምክንያት እንዳልሆነ “በሰውነታቸው ላይ ምንም አይነት ቁስለት” አለመኖሩን በመጥቀስ ተናግረዋል።
"መርማሪዎች ናሙናዎችን በመውሰድ ምርመራ ካደረጉ በኋላ አንዳች ዓይነት መመረዝ በሰውነታቸው ውስጥ መኖሩን ያጣራሉ” ሲሉ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።
በአንድ ምሽት ይህን ያህል ታዳጊዎቹ በአንድ ቦታ ተሰብስበው ለህልፈት መዳረጋቸው በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል።












