በሩሲያ የአየር ጥቃት ቢያንስ 25 ሰዎች መሞታቸውን ዩክሬን አስታወቀች

ሩሲያ በዩክሬን ግዛቶች ላይ በፈጸመችው ተከታታይ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት በርካታ መኖርያ ቤቶች ወድመዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት ቢያንስ 25 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት ተናገሩ።

በዶኔትስክ ግዛት በተፈፀመ አንድ ጥቃት በትንሹ 11 ሰዎች ሲገደሉ፣ የስድስት ዓመት ሕጻንን ጨምሮ 40 ሰዎች መቁሰላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ቅዳሜ ዕለት ተናግረዋል።

በሌሎች የአገሪቱ ግዛቶች ደግሞ፣ ካርኪቭ እና ኦዴሳን ጨምሮ፣ ቤቶች እና መሠረተ ልማቶች በአየር ጥቃቱ ዒላማ ሆነዋል።

አሜሪካ ለኪየቭ የምትሰጠውን ወታደራዊ ዕርዳታ እና የስለላ መረጃ ልውውጥ ለጊዜው ባቆመችበት በዚህ ወቅት ሩሲያ ማጥቃቷን አጠናክራ ቀጥላለች።

ይህ የአሜሪካ እርምጃ የመጣው ባለፈው ሳምንት በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በዩክሬኑ ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ መካከል በኦቫል ኦፊስ የጋለ ምልልስ ከተካሄደ በኋላ ነው።

ከሩሲያ የቅርብ ጊዜ ጥቃቶች በኋላ የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ "አንድ ሰው አረመኔዎችን ሲያስደስት የሚሆነው ይህ ነው" ብለዋል ።

በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ "ተጨማሪ ቦምቦች፣ የበለጠ ጥቃት፣ ብዙ ሰለባዎች" ሲሉ ጽፈዋል።

በጣም አስከፊ የተባለው የአየር ጥቃት የተካሄደው አርብ እለት በዶኔትስክ ግዛት በምትገኘው የዶብሮፒሊያ ከተማ ውስጥ ነው።

በአየር ጥቃቱ ሁለት ባለስቲክ ሚሳኤሎች ስምንት የመኖሪያ ሕንፃዎችን እና የገበያ ማእከልን በመምታታቸው ቢያንስ 11 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በስፍራው ከደረሱ በኋላ ሩሲያ ሌላ የአየር ጥቃት የፈጸመች ሲሆን ዜሌንስኪ"ሆን ብሎ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ" ሲሉ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።

"እንዲህ ያሉት ጥቃቶች የሩስያ ግቦች ያልተለወጡ መሆናቸውን ያሳያሉ" ሲሉም አክለዋል።

አርብ እና ቅዳሜ ዕለት በግዛቱ በተፈፀሙ ሌሎች ጥቃቶች ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ 13 ደግሞ ቆስለዋል ሲሉ የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ቅዳሜ ዕለት ረፋድ ላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በካርኪቭ ግዛት ቦሆዱኪቭ የሚገኝ ኩባንያን መትተው ሦስት ሰዎች ሲገደሉ ሰባት ደግሞ ቆስለዋል ሲሉ የአካባቢው ባለስልጣን ኦሌህ ሲንዬሁቦቭ ተናግረዋል።

አርብ ዕለት ሌላ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት በኦዴሳ ሰላማዊ ዜጎችን እና የኢነርጂ መሠረተ ልማቶችን መምታቱን የአካባቢው አስተዳዳሪ ተናግረዋል።

"ይህ በሦስት ሳምንታት ውስጥ በክልሉ የኃይል ስርዓት ላይ የደረሰ ሰባተኛው ጥቃት ነው" ሲል ዲቲኢኬ ኢነርጂ ኩባንያ አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን ሩሲያ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ቀጥላለች።

የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር በአንድ ጀምበር 31 የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ማክሸፍ መቻሏን ተናግረዋል።

አርብ ዕለት ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ከሩሲያ ይልቅ "ከዩክሬን ጋር ለመነጋገር በጣም አስቸጋሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ" ብለዋል ።

አሜሪካ "ከሩሲያ ጋር በጣም ጥሩ እየሰራች ነው" እንዲሁም "ከኪየቭ ይልቅ ከሞስኮ ጋር መስራት ቀላል ሊሆን ይችላል" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ከሰዓታት በፊት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት እስኪደረስ ድረስ በሩሲያ ላይ መጠነ ሰፊ ማዕቀቦችን እና ታሪፎችን ለመጣል "በሚገባ እያጤኑ" መሆኑን ተናግረው ነበር።

አሜሪካ ወታደራዊ እና የስለላ መረጃ ልውውጥን ከማቆም በተጨማሪ፣ ዩክሬን አንዳንድ የሳተላይት ምስሎችን እንዳትገኝ አግዳለች ሲል የጠፈር ቴክኖሎጂ ኩባንያው ማክስር አርብ ዕለት ተናግሯል።

እርምጃው የተሰማው በዋይት ሐውስ ባልተለመደ መልኩ የተካረረ የቃላት ልውውጥ በሁለቱ ፕሬዝዳንቶች መካከል ከተካሄደ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።

በዚህ ጊዜ ትራምፕ ለአሜሪካ "አክብሮት የለውም" ሲሉ ዜሌንስኪን ወቅሰው ነበር።

በርካታ የአውሮፓ መንግሥታት የትራምፕ አስተዳደር ወደ ፑቲን ማድላቱ ያስጨነቃቸው ሲሆን፣ አህጉሪቱ ለደህንነቷ በአሜሪካ ድጋፍ ላይ መተማመን ላትችል ትችላለች ሲሉ እንዲሰጉ አድርጓቸዋል።

ሐሙስ ዕለት የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ለመከላከያ ተጨማሪ በጀት ለመመደብ እና ኅብረቱ ለዩክሬን የሚሰጠውን ድጋፍ ለማደስ በብራስልስ ተገናኝተው ነበር።

በሚቀጥለው ሳምንት የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ከዩክሬን ተደራዳሪዎች ጋር በሳውዲ አረቢያ ከሩሲያ ጋር የተኩስ አቁም ለማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ይመክራሉ።

ሩስያ እኤአ በ2022 የካቲት ወር የዩክሬን ግዛቶች የወረረች ሲሆን አሁን 20 በመቶ የሚሆነውን ግዛት ትቆጣጠራለች።