ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጋና የሚመራው ለባሪያ ንግድ ካሳ የማግኘት ንቅናቄ
የአትላንቲክ ውቅያኖስን ያቋረጠውን የባርያ ንግድ በተመለከተ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውይይቶች እየተለወጡ መጥተዋል።
ከባሪያ ንግድ የተጠቀሙ አገራት እና ተቋማት ይፋዊ ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ የዕዳ ቅነሳ እንዲያደርጉ እና የገንዘብ ካሳ እንዲሰጡ የሚደረገው ጫና ተጠናክሯል።
የተባበሩት መንግሥታት የካቲት ላይ ባስተላለፈው ውሳኔ የባሪያ ንግድ "በሰብአዊነት ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች የከፋው ነው" ብሏል።
አሜሪካ የውሳኔ ሐሳቡን ስትቃወም የአውሮፓ አገራት ድምጸ ተዓቅቦ አድርገዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም እና ፖርቹጋል ካሳ የመክፈል ሐሳብን በጽኑ ተቃውመዋል።
እንግሊዝ ካሳ ትክፈል ቢባል በትሪሊዮን ፓውንዶች የሚቆጠር ገንዘብ ማውጣት ይኖርባታል።
የካሳ ክፍያው እንዲፈጸም የሚደረገውን ንቅናቄ በግንባር ቀደምነት የምትመራው ጋና ናት።
መወያያ አጀንዳውን በተባበሩት መንግሥታት ያቀረበችው ጋና፤ ባለፈው ሰኔ ላይ በመዲናዋ አክራ የካሳ ክፍያ ጉባዔ አዘጋጅታለች።
በእርግጥ ከ80 አገራት የተውጣጡ ተወካዮች በተገኙበት የተደረገው ይህ ጉባዔ ዘግይቷል።
የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሙኤል ኦኩዜቶ አብላክዋ "ጋና ፓን-አፍሪካዊ መሪ ናት። ከሰሃራ በታች ነጻነት በማግኘት ቀዳሚ አገር ነን። ኢምፔሪያሊስቶን ታግሎ ማሸነፍ እንደሚቻል አሳይተናል" ብለዋል።
አፍሪካ ኅብረት ለጋና የሰጣት ልዩ ተልዕኮ "የካሳ ፍትሕ ተልዕኮ" መሪ አድርጓታል። ጋና ይሄንን ኃላፊነት ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት ማድረጓን ቀጥላለች።
ከቤታቸው፣ ከመንደራቸው በግዳጅ የተወሰዱ እና ታይቶ የማይታወቅ ኢ-ሰብአዊነት የተፈጸማቸው አፍሪካውያን ብዛት 12 ሚሊዮን ይደርሳል። ከእነዚህ መካከል ከ10 አስከ 15 በመቶ የሚሆኑት የተወሰዱት ከጋና ነበር።
ሚኒስትሩ "ጋና ወንጀል ተፈጽሞባታል። እነዚህ ግፎች የደረሱባት አገር በመሆኗ ወንጀለኞቹ ተጠያቂ እስከሚደረጉ ዝም ማለት አንችልም" ብለዋል።
ካሳ በመስጠት ፍትሕ የሚሰፍንበት ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የካሳ ክፍያው የትምህርት ዕድል ለማመቻቸት እና ወጣት አፍሪካውያን ነጋዴዎችን በገንዘብ ለመደገፍ እንደሚውል ተገልጿል።
በተጨማሪም ባርነት ያስከተለው ዘላቂ የጤና ቀውስ ላይ ለሚደረጉ ጥናቶች ገንዘቡ የሚመደብ ይሆናል።
ከፍተኛ የምግብ እጥረት እና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ ትውልድ የተሻገረ የጤና እክል ማስከተሉ ይገለጻል።
የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደተናገሩት ካሳው ወደ አፍሪካውያን መሪዎች ኪስ የሚገባ ገንዘብ አይደለም።
በቅርቡ በጋና በኩል የቀረበው ሐሳብ ካሳን በዕዳ ቅነሳ እና ዕዳ በመሰረዝ መልኩ ማቅረብን ይመለከታል።
ከባሪያ ንግድ የተጠቀሙ ተቋማት ተጠያቂ እንዲሆኑ እና ካሳ እንዲከፍሉም ተጠይቋል። ከእነዚህ አንዷ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ናት።
በ18ኛው ክፍል ዘመን የቤተ ክርስቲያኑ ሃይማኖት ማስፋፊያ ክንፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባሪያዎችን በእርሻ መሬት ላይ ያሠራ ነበር።
ከዚህ በሚገኘው ገቢ በአሜሪካ እና ሌሎችም አገራት ያለውን እንቅስቃሴ ደግፏል።
የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት በግላቸውም ባሪያዎች ነበሯቸው። ቤተ ክርስቲያኗ ከባሪያ ንግድ ከፍተኛ ትርፍ ማግኘቷን በቅርቡ ይፋ ተደርጓል።
ሐምሌ ላይ የካንትበሪ ሊቀ ጳጳስ ሳራ ሙሊ ወደ ጋና ተጉዘዋል። ኃላፊነት ከተሰጣቸው በኋላ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ጉብኝታቸው ነው።
በባሕር ዳርቻ ለባሪያ ንግድ ይውሉ ከነበሩ ቤተ መንግሥቶች አንዱ የሆነውን እና በእንግሊዝ ይተዳደር የነበረውን ኬፕ ኮስት ካስልን ጎብኝተዋል።
በእነዚህ ሥፍራዎች ባሪያዎች እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ ወደ ምዕራቡ አገራት አሰቃቂ ጉዞ ያደርጋሉ።
ሊቀ ጳጳሷ ባሪያዎች ተይዘው የሚቆዩበትን ሥፍራ ሲጎበኙ በስሜት ተሞልተው ሲጸልዩ ታይተዋል።
"አትላንቲክን ያቋረጠው የባርያ ንግድ ሰይጣናዊ መሆኑ ተሰምቶኛል። ሰዎች ባሳለፉት ሰቆቃ በጣም አዝኛለሁ" ብለዋል።
በ17ኛው ክፍለ ዘመን በተሠራው ቤተ መቅደስ ገብተው ከጸለዩ በኋላ "ቤተ ክርስቲያን በባሪያ ንግድ የነበራት ሚና ማሳያ ነው። እንዴት ያ ሁሉ ሰቆቃ ሲደርስ ቤተ ክርስቲያን ከላይ ሆና ተመለከተች?" ሲሉ ጠይቀዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ ለባሪያ ንግድ ይቅርታ ጠይቃ ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚውል 100 ሚሊዮን ፓውንድ መድባለች።
የተለያዩ አገራት ለባሪያ ንግድ ካሳ መሰጠቱን የሚተቹ እንዳሉት ሁሉ፣ በቤተ ክርስቲያኗ ገንዘብ መመደቡን የሚቃወሙ አልጠፉም።
የጋናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን ይህንን አካሄድ ይነቅፋሉ። "ለመከፋፈል እና ውዝግብ ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎች አሉ" ይላሉ።
ምዕራባውያን አገራት የባሪያ ንግድን ለማከናወን በአፍሪካ ውስጥ ተባባሪዎች እንደነበሯቸው ሳይጠቅሱም አላለፉም።
ሆኖም የባሪያ ንግድ ሕግ ሲወጣ፣ የኢንሹራንስ ፖሊሲ ሲረቀቅ እና አጠቃላይ የፋይናንስ አካሄዱ ሲነደፍ "አፍሪካውያን አለመገኘታቸውን" ሚኒስትሩ ይናገራሉ።
"አፍሪካውያን ይሄንን ቀውስ ያቀነባበሩት ኃይሎች ያህል ተጠያቂ ናቸው የሚለውን አንቀበለውም" ብለዋል።
አንዳንድ የጋና ባህላዊ መሪዎች በባሪያ ንግድ ለነበረው ሚና ዕውቅና ሰጥተዋል። በጋራ ማገገም ወደሚቻልበት መንገድ መጓዝ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
ንጉሥ ታኪ ቴኮ ቱስሩ ሁለተኛ፣ ቀደምት ማኅበረሰብ በባሪያ ንግድ ለነበረው አስተዋዕኦ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።
"አትላንቲክን የተሻገው የባሪያ ንግር በሰብአዊነት ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች የከፋው ነው። ቅድመ አያቶቻችን በዚህ ውስጥ እጃቸው ነበረበት" ብለዋል።
ንጉሡ የሚመሩት 'ጋ' የተባለው ማኅበረሰብ እንደ አሻሻጭ ሆኖ ነበር።
ወርቅ እና የዝሆን ጥርስ ይሸጡ የነበረ ሲሆን፣ በግጭት ወቅት የተያዙ ሰዎችን በባርነት በመሸጥም ይታወቃሉ። በምላሹ ከእንግሊዝ እና ጀርመን ጨርቃ ጨርቅ፣ አልኮል እንዲሁም ሽጉጥ ይገዙ ነበር።
"ቅድመ አያቶቼ በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ባርነት ውስጥ ለነበራቸው ሚና በሁሉም ባህላዊ መሪዎች ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ" ብለዋል ንጉሡ።
የባሪያ ንግድ እስከዛሬም ድረስ የዘለቀ ጠባሳ እንዳሳደረ ተናግረው "ስህተታችንን አምነን ማረም አለብን።"
እሳቸውን ጨምሮ ከባሪያ ንግድ ተጠቃሚ የሆኑ አካላት ካሳ መክፈል እንዳለባቸው ንጉሡ ተናግረዋል።
ይህም "የሞራል ብርታት እና ተዓማኒነት የሚሰጥ ነው" ሲሉም ገልጸውታል።
የንጉሡ አቋም የአውሮፓውያንን ጥፋት የሚሸፍን አይደለም። ጋናም የካሳ ክፍያ እንዲፈጸም በሚጠይቀው ንቅናቄ ላይ አፍሪካውያን አሜሪካውያንን ጨምሮ አፍሪካውያን ዳያስፖራዎችን አሳትፋለች።
ተመሳሳይ ታሪክ የሚጋሩ ሕዝቦችን አንድ ላይ ለማምጣት እና እንዲያገግሙ ለማገዝ ካሳ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ጋና በተደጋጋሚ ገልጻለች።
በሀዋርድ ዩኒቨርስቲ የፒኤችዲ ተማሪው ጋናዊው ያው አሳር፤ መላው ጥቁር ሕዝቦች መሰባሰባቸው "ውብ፣ የሚያኮራ እና ከካፒታሊስት ፍላጎት የጸዳ" ነው ይላል።
የጋና መንግሥት የካሳን ጉዳይ ወደ ቱሪዝም መሳቢያ እንቅስቃሴ መለወጡንም ይናገራል።
ዳያስፖራዎች እንዲመለሱ የሚደረግ ንቅናቄ የውጭ ምንዛሬ ቢያስገኝም የአገር ውስጥ ገበያን በማስወደድ ጫና ሊያሳድርም ይችላል ሲል ይከራከራል።
ጉዳዩን ወደ ንግድ መለወጥ ጥልቅ የሆነውን ሥነ ልቦናዊ ሚና የሚገዳደር እንደሆነ ያስረዳል።
"ጉዳዩ የሰዎች ነው። ኑ ይሄንን ቦታ ጎብኙ ወደሚል እንቅስቃሴ መውረድ የለበትም" ይላል።
በተጨማሪም አፍሪካውያን የባሪያ ንግድ የተከናወነባቸውን ቦታዎች ሲጎበኙ በባርነት ንግድ ከተሳተፉ አውሮፓውያን አገራት እኩል ክፍያ መጠየቅ እንደሌለባቸው ይገልጻል።