በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በደረሰ 'የማሽን ፍንዳታ' የሁለት ሰዎች ሕይወት አለፈ

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ

የፎቶው ባለመብት, Industrial Parks Development Corporation - Ethiopia

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ትናንት ማክሰኞ፣ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም. በተከሰተ "የቦይለር ፍንዳታ" አደጋ የሁለት ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተነገረ።

ፍንዳታው የተከሰው በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የወረቀት ማሸጊያ አምራች በሆነው ጃስ ሆልዲንግ በተባለ የአገር ውስጥ ኩባንያ ውስጥ ነው።

በዚህም አደጋ ምክንያት በመደበኛ ሥራቸው ላይ ተሰማርተው በነበሩ ሠራተኞች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲዎስ አሸናፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አደጋው ያጋጠመው ማክሰኞ ጠዋት 2፡30 አካባቢ ሠራተኞች የዕለቱን ሥራቸውን እንደጀመሩ ወዲያውኑ መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ ሰለባዎቹም የፈነዳው ማሽንን የሚያንቀሳቅሱ 'ኦፕሬተሮች' መሆናቸውን ገልፀዋል።

አደጋው ሲከሰት የፓርኩ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በአፋጣኝ ደርሰው የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ፍንዳታውን መቆጣጠራቸውን የተናገሩት ኃላፊው፤ የሁለቱ ሠራተኞች ሕይወት ወዲያውኑ ማለፉን ተናግረዋል።

በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች "ቦይለሩን የሚያንቀሳቅሱ [ኦፕሬተሮች] በመሆናቸው ፍንዳታው በቀጥታ ስላገኛቸው ወዲያውኑ ነው ለህልፈት የተዳረጉት" ብለዋል።

ሟቾቹ ማሽኑ "ፊት ለፊት" የነበሩ፤ "ማሽኑን በማንቀሳቀስ የስድስት ዓመት ልምድ ያላቸው፣ የተቋሙ ነባር ሠራተኞች" መሆናቸውን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ በአደጋው የቆሰሉት ሁለቱ ተጎጂዎች በሐዋሳ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

ሟቾቹ ረጅም ዓመታት የሠሩ እና ልምድ ያላቸው የ62 ዓመት እና የ45 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሠራተኞች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"አዲስ ቢሆኑ ኦሬንተሽን የለም [አልተሰጣቸውም] ይባል ነበር። ብዙ ዕውቀት እና ልምድ ኖሯቸው፤ ስለ ደኅንነት ሁኔታ [የሚያውቁ]፤ ማሽኑ ላይ የኖሩ ስለሆኑ የተፈጠረው አደጋ ግራ ገብቶናል" ብለዋል።

የአደጋውን መንስኤ ምንነት ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ ቢሆንም፤ "ከቴክኒክ ጋር የተያያዘ" ሊሆን እንደሚችል አቶ ማቲዎስ ተናግረዋል።

"ሲሠሩ መጠንቀቅ ያላባቸው የቴክኒክ ጉዳዮች ወይም ከማሽኑ ጋር የተያያዙ [ችግሮች]" የአደጋው መንስኤዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምታቸውን ገልጸዋል።

በሲዳማ ክልል ዋና ከተማ በሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት አደጋ ተከስቶ እንደማያውቅ ተናገሩት አቶ ማቲዎስ፤ ፓርኩ ዓለም አቀፍ የደኅንነት መስፈርቶችን እንደሚከተል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሁለቱ ሟቾች የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ረቡዕ፣ ሰኔ 25/2017 ዓ.ም. ሐዋሳ ከተማ ውስጥ መፈፀሙንም ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

አደጋው የደረሰበት ጃስ ሆልዲንግ ኩባንያ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ካሉ ሦስት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ከውጭ ይገቡ የነበሩ የወረቀት ማሸጊያ ምርቶችን የሚተካ አምራች መሆኑን አቶ ማቲዎስ ተናግረዋል።

ከስድስት ዓመት በፊት በፓርኩ ሥራ የጀመረው ይህ ኩባንያ በርካታ ሠራተኞች ያሉት ኩባንያ ነውም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ካሏት 14 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አንዱ የሆነው ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአልባሳት እና የጨርቃ ጨርቅ ምርት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በ300 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ግዙፍ ፓርክ ነው።

በሲዳማ ክልል የሚገኘው ኢንዱስትሪ ፓርኩ በ2008 ዓ.ም. ተከፍቶ ሥራ የጀመረ ሲሆን አሁን ላይ 23 ኩባንያዎች በተለያዩ የምርት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙበት ነው።