ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ እና አፍሪካ በምስል

ንግሥት ኤልዛቤጥ ዳግማዊት 

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ንግሥት ኤልዛቤጥ ዳግማዊት በንግሥና ዘመናቸው ከ20 በላይ የአፍሪካ አገራትን ጎብኝተዋል። ንግሥቲቱ በሥልጣን ዘመናቸው በርካታ የአፍሪካ አገራት ከብሪታኒያ ቅኝ አገዛዝ ነጻ በመውጣት የራሳቸውን አስተዳደር ሲመሰርቱ አይተዋል።

የቀድሞዎቹን በብሪታኒያ ሥር የነበሩ በርካታ አገራትን በአንድ ያስተሳሰረውን የኮመንዌልዝ አገራት ማኅበርንም መርተዋል።

የአፍሪካ አገራት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጡ በኋላ ከብሪታኒያ ንጉሣዊ ሥርዓት ጋር የቀረበ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የተወሳሰበ ግንኙነት ነበራቸው።

ንግሥት ኤልዛቤጥ ዳግማዊት 

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ንግሥት ኤልዛቤጥ ልዕልት በነበሩበት ጊዜ ደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ውስጥ 21ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው ሲከበር የኮመንዌልዝ አገራትን ለማገልገል ቃል ገብተው ነበር።

ንግሥቱቱ ከባለቤታቸው ጋር ኬንያ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ልዕልት ኤልዛቤት እአአ በ1952 ከባለቤታቸው ከኤደንብራው አልጋ ወራሽ ጋር ኬንያ ውስጥ ጉብኝት እያደረጉ። ይህ ፎቶ በተነሳበት ዕለት የአባታቸውን ንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ሞት የሰሙ ሲሆን ወዲያውኑም ንግሥት ሆኑ።

ንግሥቲቱ ከናይጄሪያው ባሕላዊ መሪ ኦባአ ዴንጄ ሁለተኛ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በ1956 ንግሥቲቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ናይጄሪያን ጎብኝተው በዚህ ፎቶ ሌጎስ ውስጥ ከናይጄሪያው ባሕላዊ መሪ ኦባአ ዴንጄ ሁለተኛ ጋር ይታያሉ። ንግሥቲቱ በርካታ የአገሪቱን ግዛቶች ጎብኝተዋል።

ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ ከፕሬዝዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ጋር ሲደንሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ የአፍሪካ ፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ መሪ ከሆኑት እና የጋና የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ከነበሩት ክዋሜ ንክሩማህ ጋር ሲደንሱ። ይህ ፎቶ ጋና ነጻ አገር ከሆነች ከአራት ዓመት በኋላ በ1961 የተነሳ ነው።

ንግሥት ኤልዛቤጥ እና ባለቤታቸው ልዑል ፊሊፕ ኢትዮጵያን እአአ በ1965 በጎበኙበት ጊዜ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ንግሥት ኤልዛቤጥ እና ባለቤታቸው ልዑል ፊሊፕ ኢትዮጵያን እአአ በ1965 በጎበኙበት ጊዜ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ጋር።

የጣሊያን ወረራ አብቅቶ ወደ መንበራቸው እስኪመለሱ ድረስ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ በዩናይትድ ኪንግደም ቆይተው ነበር።

ንግሥቲቱ እአአ በ1965 ሱዳንን በጎበኙበት ጊዜ ከፕሬዝዳንት ኤል ቲጋኒ ኤል ማሂ ጋር በካርቱም አውሮፕላን ማረፊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ንግሥቲቱ እአአ በ1965 ሱዳንን በጎበኙበት ጊዜ ከፕሬዝዳንት ኤል ቲጋኒ ኤል ማሂ ጋር በካርቱም አውሮፕላን ማረፊያ

ንግሥቲቱ እና የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ እአአ በ1979

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ንግሥቲቱ እና የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ እአአ በ1979። ከታንጋኒካ ነጻ መውጣት በኋላ ኔሬሬ ፀረ ብሪታኒያ እና ፀረ አውሮፓ አቋም ያራምዱ ነበር። ነገር ግን የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በግጭት ውስጥ ባለው አካባቢ ኔሬሬ የማረጋጋት ሚና አላቸው ብሎ ያምን ነበር።

የዚምባብዌው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ በአውሮፓውያኑ በ1994 ዘውዳዊ የክብር ማዕረግ በተሰጣቸው ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዚምባብዌው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ በአውሮፓውያኑ በ1994 ዘውዳዊ የክብር ማዕረግ በተሰጣቸው ጊዜ።

ነገር ግን ሙጋቤ በጀመሩት የመሬት ባለቤትነት ፕሮግራማቸውና በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ከዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ከኮመንዌልዝ ማኅበር ወጥተዋል። የተሰጣቸውም የክብር ማዕረግ ተነሳ።

ንግሥት ኤልዛቤጥ እና ፕሬዝዳንት ማንዴላ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ንግሥት ኤልዛቤጥ እና የደቡብ አፍሪካው የመጀመሪያ ጥቁር ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ የቀረበ ወዳጅነት እንዳላቸው ይነገራል።

ንግሥቲቱ ለፕሬዝዳንት ማንዴላ ደብዳቤ ሲጽፉ “የልብ ወዳጅህ፣ ኤልዛቤጥ” በማለት ከቅርበታቸው የተነሳ “ማንዴላ” ሲሉ ይጠሯቸው ነበር።

ማንዴላም የንጉሣውያንን ሥርዓት ባልጠበቀ ሁኔታ ንግሥቱቱን “ኤልዛቤጥ” በሚል ነበር የሚጠሯቸው።

ንግሥት ኤልዛቤጥ እና ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ንግሥቲቱ በ2003 (እአአ) ለሁለተኛ ጊዜ ናይጄሪያን ጎብኝተዋል። ንግሥት ኤልዛቤጥ እና ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ አቡጃ ውስጥ በተካሄደው የኮመንዌልዝ አገራት ስብሰባ መክፈቻ ላይ በተገኙበት ወቅት የተነሳ ፎቶ።

ንግሥት ኤልዛቤጥ እና ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በብሪታኒያ ታሪክ ለረጅም ጊዜ በንግሥና ላይ የቆዩት ንግሥት ኤልዛቤጥ በ2007 (እአአ) ወደ አፍሪካ ባደረጉት የመጨረሻ ጉዟቸው፣ በአፍሪካ በሥልጣን ላይ ለረዥም ጊዜ ከቆዩት መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑትን የኡጋንዳውን ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒን አግኝተዋል።

ንግሥቲቱ በ1954 ወደ አፍሪካ የመጀመሪያቸውን ይፋዊ ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ ኡጋንዳን ጎብኝተው ነበር።