በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ስር ያለው የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አገልግሎት ማቆሙ ተነገረ

ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, Bahir Dar University

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር የሚገኘው የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት ሥራ ማቋረጡን ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።

ቢቢሲ ከሆስፒታሉ ሠራተኞች እና ከዩኒቨርስቲው ኃላፊ ለማረጋገጥ እንደቻለው ሆስፒታሉ በአሁኑ ጊዜ የተለመደ መደበኛ ሥራውን እያከናወነ አይደለም።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በሆስፒታሉ የሚሠሩ አንድ የጤና ባለሙያ ሆስፒታሉ ከረቡዕ መስከረም 30/2016 ዓ.ም. ረፋድ ጀምሮ አገልግሎት ማቋረጡን ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኝ ሆስፒታሉ ከውጭ ታካሚ እየተቀበለ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ነገር ግን በስብሰባ ምክንያት ሥራ ላይ ባለመሆናቸው ዝርዝር መረጃ መስጠት እንዳመይችሉ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ “አሁን ከውጭ ታካሚ መቀበል በምንችልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም። ውስጥ ያሉትን ሠራተኞቻችንን እዚያው ምግብ እያዘጋጀን፣ እዚያው እየተንከባከብን ነው ያለነው። እኔ በርቀት ሆኜ እንደ ኃላፊ የማውቀው ይህንን ነው” የሚል አጭር ምላሽ ለቢቢሲ ሰጥተዋል።

ቢቢሲ ያናገራቸው የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያ በበኩላቸው “የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ ከየት እንደሆነ ባይታወቅም ተኩስ ተከፍቶባቸው፣ ለዚያ ምላሽ ለመስጠት እየተኮሱ ወደ ሆስፒታሉ ገቡ። ተኩስ ከሆስፒታሉ አቅጣጫ አለ ብለው ገምተው ይመስለኛል [የገቡት]። ከዚያ ሕንጻው ላይ መሳሪያ ጠመዱ። የሆስፒታሉ ባለሙያ ይህንን ሁኔታ ሲመለከት ስጋት ስለተፈጠረበት ጥሎ መውጣት ጀመረ” በማለት የሆስፒታሉ ሥራ የተቋረጠበትን ምክንያት አስረድተዋል።

አክለውም የመከላከያ ሠራዊት አባላት “ሆስፒታሉ ውስጥ ቆስለው የገቡ፣ ሕክምና ላይ የነበሩ [ታካሚዎችን] ፋኖ ናቸው በሚል እሳቤ እያወጡ ሲወስዱ ያዩ ባለሙያዎች የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ስላልሆነ እና ሥራ ለመሥራት አመቺ ባለመሆኑ ጥለው ሄዱ። በዚያ ምክንያት ሆስፒታሉ ሥራ አቁሟል” ሲሉ ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሆስፒታሉ አስተዳደር ሕንጻ ላይ መሳሪያዎችን ቢጠምዱም ተኩስ እንዳልከፈቱም ተናግረዋል። በዚህም ሳቢያ ሆስፒታሉ ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።

ሌላ ስማቸው እንዲጠቀስ ያለፈልጉ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ደግሞ ሆስፒታሉ ሥራ ማቆሙን አረጋግጠው “ሆስፒታሉ አካባቢ ውጊያ እየተካሄደ ሃኪሞቹ በተረጋጋ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት አልቻሉም” ብለዋል።

በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ከሆስፒታሉ በቅርብ ርቀት ውጊያ ተካሂዶ እንደነበርም ጠቁመዋል።

“ግጭት ነበረ ነገር ግን ሆስፒታሉ ጋር የደረሰ አልነበረም። ጢስ አባይ ላይ ግጭቶች ነበሩ። ግጭቶቹ እየተጎተቱ ወደ ሰባት አሚት መጡ። ሆስፒታሉ የነበረው በደቡብ አቅጣጫ ሲሆን፣ ግጭቱ የነበረው በሰሜን አቅጣጫ ነው። ከዚያ በተለያየ ምክንያት ሆስፒታል የገቡ ሰዎችን መርጠው መምታት ሲጀምሩ ሐኪሞቹ መውጣት ጀመሩ” ሲሉ ያስረዳሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጤና ባለሙያው በበኩላቸው “ፋኖ ነው ብለው ያሰቧቸውን [የሆስፒታሉ] ባለሙያዎችን ወስደዋል። አንድ የሕክምና ባለሙያ በጥይት ተመትቶ ሕክምና ላይ ነው” ብለዋል።

ምንጫችን አሁን ላይ አካባቢው በመከላከያ ሠራዊት እንደተከበበ የገለጹ ሲሆን፣ ሰዎች “ለሕይወታቸው በመስጋት” አካባቢውን ለቀው ሄደዋል ብለዋል።

በሆስፒታሉ የሚሠሩት የጤና ባለሙያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከመግባቱ አስቀድሞ ንጹሃን ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

“ከመግደል እና ከማቁሰል በተጨማሪ ታፍነው የተወሰዱ አሉ። የተደፈሩ ሰዎችም ነበሩ። ወደ ስድስት ያህሉ ሆስፒታል ገብተው ሕክምና እየተደረገላቸው ነው” ብለዋል።

ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ ከክልሉ ጤና ቢሮ እና ከአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከባሕር ዳር ከተማ ወደ አዲስ አበባ አቅጣጫ ከክልሉ መዲና 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለችው ሰባት አሚት በተሰኘችው አነስተኛ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ነው።

አካባቢው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አካልም ነው።

ሰባት አሚት ላይ እስከ ትላንት ሐሙስ ጥቅምት 01/2016 ዓ.ም. ድረስ ውጊያ ቀጥሎ የተኩስ ልውውጥ እንደነበረ ምንጮቻችን የጠቀሱ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ እስከ ዛሬ አርብ ረፋድ አካባቢው እንደተረጋጋ ተናግረዋል።

ከትላንት በስትያ ረቡዕ መስከረም 30/2016 ዓ.ም. በነበረው ክስተት አንዳንድ ታካሚዎች በፍራቻ ሆስፒታሉን ለቀው እንደሄዱም ጠቅሰዋል። ሌሎች ደግሞ ሆስፒታል ውስጥ ቀርተዋል።

ሆስፒታል ውስጥ የሚኖሩ የሕክምና ባለሙያዎች “ወጣ ገባ እያሉ ሕክምና እየሰጧቸው ነው። ሌላው ከባህሕር ዳር እየሄደ አገልግሎት የሚሰጠው [የሕክምና ባለሙያ] መንገዱ ስለተዘጋ መምጣት አልቻለም። አዳዲስ ታካሚዎችም መግባት አይችሉም” ብለዋል የሆስፒታሉ የሕክምና ባለሙያ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕክምና ባለሙያው እና መምህሩ የሆስፒታሉ አገልግሎት መቋረጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የሕክምና አገልግሎት ፈላጊዎች ላይ ከፍተኛ መስተጓጓል ይፈጥራል ይላሉ።

ይህ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሰሜን ኢትዮጵያ የሕክምና አገልግሎት በተሻለ ጥራት ለማዳረስ መገንባቱን የሚናገሩት የጤና ባለሙያው፣ አሁን አገልግሎቱ ሲቋረጥ በተለይ ከአምስት ዞኖች ‘በሪፈር’ የሚመጡ ታካሚዎች ለችግር እንደሚዳረጉ ተነግረዋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህሩ በበኩላቸው ሆስፒታሉ አግልግሎት በማቆሙ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ የሕክምና ተማሪዎች ትምህርት ለማቆም ሊገደዱ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የራሱ የኦክስጂን ማምረቻ ያለው ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አገልግሎቱ ሲቋረጥ ኦክስጂን ሲቀርብላቸው የነበሩ የፍኖተ ሰላም፣ የአንጅባራ እና የደብረ ማርቆስ ሆስፒታሎች የአቅርቦት ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል አንስተዋል።

ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት በክልሉ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ መታወጁ ይታወቃል።

እስካሁንም ድረስ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸው እየተዘገበ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ መደበኛ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸው አጋጥሞ በጤና እና በአግልግሎት አቅራቢ ተቋማት ላይ ጫና መፈጠሩን ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው።