በዕዳ የተዘፈቀው ሕንዳዊ የጉልበት ሠራተኛ 95 ሺህ ዶላር የሚያወጣ አልማዝ አገኘ

በማዕከላዊ ማድያ ፕራዴሽ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ማዕድን ማውጫ ውስጥ የሚሠራ ሕንዳዊ የጉልበት ሠራተኛ ሕይወቱን እስከወዲያኛው የሚቀየር አልማዝ አገኘ።
ባለ 19.22 ካራቱ አልማዝ በመንግሥት ጨረታ 8 ሚሊዮን ሩፒ (95 ሺህ 570 ዶላር) ያወጣል ተብሏል።
ራጁ ጉንድ አልማዝ ለማግኘት በሚል በፓና ከተማ ከ10 ዓመታት በላይ በማዕድን ቁፋሮ ተሰማርቶ ሲሠራ እንደነበር ተናግሯል።
ፓና በአልማዝ ክምችቷ ትታወቃለች። አልማዝ ለማግኘት በሚል መሬት ከመንግሥት በመከራየት ቁፋሮ የሚያካሂዱ ብዙ ናቸው።
የሕንድ ብሔራዊ ማዕድን ልማት ኮርፖሬሽን በፓና የሚካሄደውን ሜካናይዝድ የአልማዝ ማውጣት ፕሮጀክት ይመራል።
አልማዝ ለሚፈልጉ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች እና ቡድኖች መሠረታዊ መሳሪያዎች በማቅረብ ጭምር የሊዝ ፈቃድ ይሰጣል።
በቁፋሮ የሚገኙት አልማዞች በሙሉ ለመንግሥት ገቢ ተደርገው ምርመራ ይካሄድባቸዋል።
"እነዚህ ማዕድን ማውጫዎች ከ200-250 ሩፒ ሊከራዩ ይችላሉ" ሲሉ የግዛቱ የአልማዝ ጽህፈት ቤት ባለስልጣን አኑፓም ሲንግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጉንድ ለቢቢሲ እንደተናገረው ከሆነ አባቱ ከሁለት ወራት በፊት በፓና አቅራቢያ በሚገኘው ክሪሽና ካሊያንፑር ፓቲ መንደር ማዕድኑን ስፍራ በሊዝ ተከራይተዋል።
ቤተሰቡ ማዕድን ስፍራዎችን በሊዝ የሚከራየው የእርሻና የግንባታ ሥራ በሚቀንስበት የበጋ ወቅት ነው።
"እኛ በጣም ድሆች ነን ስንሆን ሌላም የገቢ ምንጭ የለንም። ይህንን የምንሠራው የተወሰነ ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ ነው" ብሏል።

ሰዎች አልማዝ እንደሚያገኙ ሰምቶ ነበር እና እሱም አንድ ቀን ዕድለኛ እንደሚሆን ተስፋ አድርጎ ነበር።
እንደተለመደው ረቡዕ ጠዋትም የከበረ ድንጋዩን ለመፈለግ ወደ ስፍራው አቀና።
"አሰልቺ ሥራ ነው። ጉድጓድ ቆፍረን አፈርና የድንጋይ አውጥተን በወንፊት እናጥባለን። ከዚያም በሺህዎች ከሚቆጠሩ ጥቃቅን ድንጋዮች ውስጥ አልማዝ ለመፈለግ በጥንቃቄ እናጣራለን" ብሏል።
ረቡዕ ዕለት ከሰዓት በኋላ ግን ያ ሁሉ ልፋቱ ፍሬ አፍርቶ ዕድሉ ቀና።
"ድንጋዮቹን እያጣራሁ ሳለ አንድ መስታወት የሚመስል ነገር አየሁ። አንስቼ የሚያብለጨልጨውን ነገር አየሁ። አልማዝ ማግኘቴን ያወቅኩት ያኔ ነበር" ብሏል።

ጉንድ በመቀጠልም የከበረውን ድንጋይ ወደ መንግሥት የአልማዝ ቢሮ ወሰዶ አስመርምሮ አስመዘነ።
አልማዙ በሚቀጥለው የመንግሥት ጨረታ እንደሚሸጥ እና የመንግሥት ሮያሊቲ እና ታክስ ከተቀነሰ በኋላ ጉንድ ገንዘቡ እንደሚሰጠው ተገልጿል።
ጉንድ በገንዘቡ የተሻለ ቤት ለቤተሰቦቹ እንደሚገነባ እና የልጆቹን የትምህርት ክፍያ ለመፈጸም አቅዷል። በመጀመሪያ ያለበትን 500 ሺህ ሩፒ ዕዳ ከፍሎ ለመገላገል ይፈልጋል።
ገንዘቡን ከእሱ ጋር ለሚኖሩ 19 ዘመዶቹ ለመከፋፈል በማቀዱ ስለአልማዙ ሰዎች በማወቃቸው አልፈራም ብሏል።
ለዛሬ ገንዘቡ እንደሚመጣለት ማወቁ ይበቃዋል።
"ነገ ደግሞ አልማዝ ፍለጋ ወደ ማዕድን ማውጫው በድጋሚ እሄዳለሁ" ብሏል።












