ጉዳት እያስከተሉ ነው የሚባሉትን ‘የሰማይ ላይ ወንዞች’ የሚፈልጉት ሳይንቲስቶች

የፎቶው ባለመብት, US Air Force
ከወራት በፊት አና ዊልሰን ጄት ውስጥ ተቀምጣ ሰማዩን እየቃኘች ነበር። ከፓስፊክ ውቅያኖስ በላይ ነጫ ደመና ተመለከተች።
የከባቢ አየር ሳይንቲስት ናት፤ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ላይ ምርምር ታደርጋለች።
በዚያው ጄት ውስጥ የሥራ ባልደረባዋ የደመናውን ጥንካሬ ለመለካት እየሞከረ ነበር። እየተከታተሉ ያሉት የከባቢ አየር ወንዝ (ወይም በእንግሊዘኛው atmospheric river) ነው።
ይህ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት እያገኘ ያለ ርዕሰ ጉዳይ ነው።
የከባቢ አየር ወንዝ ማለት ሰማይ ላይ በደመና ውስጥ የታቆረ ውሃ ወይም የፈሳሽ ብናኝ ነው።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ይህ የታቆረ ፈሳሽ ከሚጠበቀው ጊዜ ውጪ የሆነ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ በመፍጠር ይታወቃል። ከፍተኛ ጉዳትም እያደረሰ ነው።
በኪሎ ሜትሮች በሚቆጠር ርቀት በመቶዎች የሚቆጠሩ የከባቢ አየር ወንዞች ሊኖሩ ይችላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Anna Wilson
መነሻው ሞቃት ውቅያኖሶች ነው። ውሃው ይተንና ወደ ሰማይ ወጥቶ ይቀዘቅዛል። አንድ ቦታ ላይም ይሰበሰባል።
ደመና ሆኖ ይቆያል ወይም ዝናብ ሆኖ ይወርዳል። ከፍተኛ መጠን ያለው ስለሆነ አውሎ ነፋስ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የመሬት መንሸራተት ሊያስከትል ይችላል።
ለምሳሌ በአሜሪካ ምዕራባዊ ክፍል ከፍተኛ ዝናብ የሚከሰተው በከባቢ አየር ወንዝ ሳቢያ ነው።
አና እና የሥራ ባልደረቦቿ አራት የከባቢ አየር ወንዞችን ሲያስሱ ነበር። ኋላ ላይ እነዚህ የከባቢ አየር ወንዞች በካሊፎርኒያ የበረዶ ማዕበል እና በኦሪገን ጎርፍ አስከትለዋል።
አና እንደምትለው፣ የከባቢ አየር ወንዝ የት አካባቢ ሊወርድ ይችላል? የሚለው ቀዳሚ ጥያቄ ነው። ምን ያህል ጠንካራ ይሆናል? ምን ያህል ቀናት ይቆያል? የሚሉ ጥያቄዎችም ያነሳሉ።
የአሜሪካ አየር ኃይል እና የውቅያኖስ ጥናት ማዕከልን ጨምሮ ሌሎችም በዚህ አሰሳ ተሳትፈዋል።
“የከባቢ አየር ወንዝ አስደናቂ ነው። ግን የውሃ ብናኝ ስለሆነ አይታይም” ትላለች አና።
ከደመና ጀርባ ስለሚደበቁ ከሳተላይት ዕይታ ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ። ሳተላይትን በመጠቀም የሚደረግ የአየር ሁኔታ ትንበያ ውስጥ ለማካተት የሚያስቸግሩትም ለዚህ ነው።
አና እና የሥራ ባልደረቦቿ እያሰሱ የነበሩት የከባቢ አየር ወንዝ ከሌሎች 51 የከባቢ አየር ወንዞች መካከል የተመዘገበ ነው።
በዋሽንግተን፣ ኦሪገን እና ካሊፎርኒያ ነበር የተመዘገቡት።
አውሎ ነፋስ መቼ ሊመጣ እንደሚችል እና ምን ያህል ጠንካራ ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አስቀድሞ ለመዘጋጀት ያግዛል። የከባቢ አየር ወንዞችን ቀድሞ ለማወቅ የሚደረገው ጥረትም የዚህ አካል ነው።
የከባቢ አየር ወንዝ አጥፊ ሳይሆን ጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ የሚቻልበት መንገድ እንዳለም ሳይንቲስቶች ይናገራሉ።
“የከባቢ አየር ወንዝ ከሌለ ድርቅ ይከሰታል” የሚለው በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የከባቢ አየር ሳይንቲስት ቢን ጉዋን ነው።

የፎቶው ባለመብት, Rich Henning/Noaa
የከባቢ አየር ወንዝ ‘ድርቅ አምካኝ’ የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ይናገራል።
ለምሳሌ እንደ ካሊፎርኒያ ላሉ ደረቅ አካባቢዎች ጠቀሜታው እንደሚያመዝን ያስረዳል።
“አደጋው ላይ እናተኩራለን እንጂ ተፈላጊውን ውሃ የሚያስገኙ ናቸው” ይላል።
በ2017 ከቀደሙት ጊዜያት የተለየ የከባቢ አየር ወንዝ ከጃፓን እስከ ዋሽንግተን ተዘርግቶ ነበር። የከባቢ አየር ወንዙ ወደ 8000 ኪሎ ሜትሮች ተዘርግቶ ነበር።
የከባቢ አየር ወንዝ ባለው አቅም ከቀላል እስከ ከባድ ደረጃ ድረስ ሳይንቲስቶች ይለኩታል።
“ቀላል የሚባለው ለውሃ አቅርቦት ጠቃሚ ነው። ካባዱ ግን ጉዳት ያስከትላል” የምትለው ውቂያኖሶችን በሚያጠናው ተቋም [ኢንስቲትዩት ኦፍ ኦሽኖግራፊ] የምትሠራው ኩዊን ሻዎ ናት።
ከውቅያኖስ በላይ ስለሚገኙ መቼ ሊፈጠሩ እንደሚችሉ መገመት ከባድ እንደሆነ ታስረዳለች።
“እነዚህ የከባቢ አየር ወንዞችን መተንበይ ከተቻለ ቀድሞ ተጠንቅቆ እርምጃ ለመውሰድ ይቀላል። ውሃውን ለማጠራቀም ወይም ለመልቀቅ መወሰንም ይቻላል” ትላለች ባለሙያዋ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የከባቢ አየር ወንዝን ከሁለት ሳምንት አስቀድሞ ወይም ቢያንስ ከወር በፊት መተንበይ የሚቻልበትን መንገድ ለማግኘት ሳይንቲስቶች እየሞከሩ ነው።
ቦታውን መለየት ከተቻለ ሳይንቲስቶች ናሙና ለመውሰድም ይችላሉ።
በመላው ዓለም የአየር ፀባይን በተመለከተ መረጃ የሚሰጠው ተቋም ስለ ከባቢ አየር ወንዝ መረጃ እንዲያገኝ ሲደረግ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠት እንደሚቻል ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
የከባቢ አየር ወንዝ እያስከተለ ካለው ጉዳት አንጻር ቀድሞ የመተንበይ እንቅስቃሴው እየተፋጠነ ይገኛል።
በሆንግ ኮንግ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ አጥኚ የሆነችው ፕሮፌሰር ሜንኩዊን ሉ፣ ከዝናብ እና ከበረዶ መጠን ጋር በተያያዘ ትንበያ የሚሰጥ ጥናት አድርጋለች።
በምዕተ ዓመቱ መጨረሻ ለዝናብ እና ለበረዶ መንስዔ የሆነ የአካቢ አየር ወንዝ በእጥፍ እንደሚጨምር ጥናቱ ያሳያል።
“የከባቢ አየር ወንዝ የሚፈጠርበት ፍጥነት እና የእንቅስቃሴው ኃያልነት ከጨመረ ከፍተኛ ዝናብ ያስከትላል” ትላለች ፕሮፌሰሯ።
ከባቢ አየር እየሞቀ ከመሄዱ ጋር በተያያዘ ስለ ከባቢ አየር ወንዞች ማወቅ ግዴታ ይሆናል።
ምን ያህል ሙቀት እና ፈሳሽ እንደያዙ ማወቅም ያሻል።
በምዕራብ አንታርክቲካ የበረዶ መቅለጥ እያስከተለ ካለው ጉዳት አንጻር የከባቢ አየር ወንዞችን የሙቀት መጠን ማወቅ አስፈላጊ እንደሆነ ሳይንቲስቶች ያስረዳሉ።
በምሥራቅ እስያ የከባቢ አየር ወንዝ ለከፍተኛ ዝናብ መከሰት 90 በመቶ አስተዋጽኦ አለው።
በአንድ ጊዜ በተለያየ አካባቢ ጎርፍ የሚያስከትል ወይም ከአንድ ቦታ ወደሌላው የሚሻገር ጎርፍ የሚፈጥርም ነው።
ይህም ለአፈር መሸርሸር ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር ሰደድ እሳት እንዲነሳም ሰበብ ይሆናል።
አና እንደምትለው፣ በሰማይ ላይ የከባቢ አየር ወንዝ ለማግኘት የሚደረገው አሰሳ ሚናው ቀላል አይደለም።
“በፍጥነት ሊተገበር የሚችል ወይም በፍጥነት ለሰዎች ጥቅም ሊሰጥ የሚችል ነገር ላይ ጊዜን ማዋል ለአንድ ሳይንቲስት ትልቅ ደስታ ይሰጣል” ስትል ትገልጻለች።












