የ9/11 ጥቃት ያቀነባበሩ ናቸው ተብለው የተከሰሱ ሦስት ሰዎች የፍርድ ማቅለያ ስምምነት ላይ ደረሱ - ፔንታጎን

የ2001 የኒው ዮርክ ሽብር ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እአአ መስከረም 2001 በአሜሪካ የደረሰውን የሽብር ጥቃት በማቀነባበር ከተከሰሱት ሰዎች መካከል ሦስቱ የቅድመ ችሎት ስምምነት መፈጸማቸውን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ካሊድ ሼክ ሞሐመድ፣ ዋሊድ ሙባረክ ሳሊህ ሙባረክ ቢን አታሽ እና ሙስጠፋ አህመድ አደም አል-ሃውሳዊ ለፍርድ ሳይቀርቡ ለዓመታት በኩባ ጓንታናሞ ቤይ ታስረው ይገኛሉ።

የዩናይትድ ስቴትስ የዜና አውታሮች እንደዘገቡት ከሆነ ግለሰቦቹ ጥፋተና መሆናቸውን በማመን አቃቤ ህግ የሞት ፍርድ እንዳይጠይቅባቸው ተስማምተዋል።

የስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች ገና አልተለቀቁም።

በኒው ዮርክ፣ ቨርጂኒያ እና ፔንስልቬንያ ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በአልቃይዳ ጥቃት የተገደሉ ሲሆን ይህም "የሽብር ጦርነት" እና የአፍጋኒስታን እና የኢራቅ ወረራዎችን አስከትሏል።

ይህም እአአ በ1941 ጃፓኖች 2 ሺህ 400 ሰዎች ከገደሉበት የፐርል ሃርበር ጥቃት በኋላ በአሜሪካ ምድር ላይ የተፈጸመው እጅግ አስከፊው ጥቃት ነው።

ስምምነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የተደረገው አቃቤ ህግ ለተጎጂ ቤተሰቦች በላከው ደብዳቤ ነው ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

"የሞት ቅጣት ሊወገድ በሚችልበት መልኩ እነዚህ ሦስት ተከሳሾች በክሱ ላይ የተዘረዘሩትን 2 ሺህ 976 ሰዎች መግደልን ጨምሮ በተከሰሱባቸው ወንጀሎች በሙሉ ጥፋተኛ መሆናቸውን ለመቀበል ተስማምተዋል" ሲሉ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አድሚራል አሮን ሮግ በደብዳቤው ገልጸዋል።

ካሊድ ሞሐመድ በ2003 በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ግለሰቦቹ በሲቪሎች ላይ ጥቃት መሰንዘር፣ የጦርነትን ህግጋት በጣሰ ግድያ፣ ጠለፋ እና ሽብርተኝነትን ጨምሮ በርካታ ክሶች ተመስርተውባቸዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል ሲል ታይምስ ዘግቧል።

ጠላፊዎች የመንገደኞች አውሮፕላኖችን በማስገደድ በኒውዮርክ የዓለም ንግድ ማዕከል እና ከዋሽንግተን ወጣ ብሎ በሚገኘው የፔንታጎን ህንጻ ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ ካሊድ ሼክ ሞሐመድ ዋና አቀነባባሪ መሆኑ በሰፊው ይነገራል።

የአራተኛው አውሮፕላን ተሳፋሪዎች ባደረጉት ትግል በፔንስልቬንያ ውስጥ ሜዳ ላይ ወድቋል።

በዩናይትድ ስቴትስ ምህንድስና ያጠናው ሞሐመድ ከሃውሳዊ ጋር ፓኪስታን ውስጥ እአአ በ2003 ተይዟል።

አውሮፕላኖችን የመጥለፍ እና ወደ አሜሪካ ህንፃዎች የማብረር ሃሳብን ለአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ያቀረበው እሱ ነው ሲል አቃቤ ህግ ይከራከራል። የተወሰኑ ጠላፊዎችን በመመልመል እና በማሰልጠን ድጋፍ አድርጓልም ተብሏል።

ድርጊቱ በአሜሪካ መንግስት ከመታገዱ በፊት ቢያንስ 183 ጊዜ ያህል "ውሃ ውስጥ መዝፈቅን" ጨምሮ በርካታ "የምርመራ ዘዴዎች" ተፈጽመውበታል።

አድሚራል ራግ በደብዳቤው ላይ እንደገለጹት ከሆነ ስምምነቱን ለመቀበል የተደረገው ውሳኔ "በቀላል ያልተደረሰበት" እና "ለፍትህ. . . ምርጥ መንገድ" ነው።

የባይደን አስተዳደር መስከረም ላይ የመሐመድን ጨምሮ በኩባ በሚገኘው የአሜሪካ የባህር ሃይል የተያዙ አምስት ሰዎች ጋር የተደረሰውን ውሉን ውድቅ አድርጓል።

ግለሰቦቹ ለብቻቸው እንዳማይታሰሩ እና የአእምሮ ህክምና እንደሚያገኙ ከፕሬዝዳንቱ ዋስትና መጠየቃቸው ተዘግቧል።

የዋይት ሃውስ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በበኩሉ የፕሬዚዳንቱ ፅህፈት ቤት ስለአዲሱ ስምምነት ረቡዕ ዕለት ማወቁንና በድርድሩ ላይ ምንም ሚና እንዳልነበረው አስታውቋል።

ተጎጂ ቤተሰቦች "እነዚህ እንስሳት በምንወዳቸው ሰዎች ላይ ያደረጉትን ነገር ፍርድ ቤት ለማቅረብ 23 ዓመታት ጠብቀናል" ሲል በጥቃቱ ባለቤቱ የሞተችበት ጂም ስሚዝ ለኒውዮርክ ፖስት ተናግሯል።

"ይህንን ዕድል ከእኛ ነጥቀዋል" ካለ በኋላ በሚናቸው ልክ "ከፍተኛውን ቅጣት" መቀበል አለባቸው ብሏል።

ሪፐብሊካኖችም ከተከሳሾች ጋር ስምምነት በመደረሱ የባይደን አስተዳደርን በፍጥነት ተችተዋል።