በሞዛምቢክ ወረርሽኝ ለመከላከል ከ45 ሺህ በላይ ዶሮዎች ተቃጠሉ

ዶሮዎች

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የወፍ ጉንፋን (በርድ ፍሉ) በሽታ ስርጭትን ለመከላከል ሲባል በደቡባዊ ሞዛምቢክ ከ45 ሺህ በላይ ዶሮዎች ታርደው ተቃጥለው እንዲቀበሩ ተደረገ።

ከደቡበ አፍሪካ የተነሳው የወፍ ጉንፋን የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ነው ተብሏል። ዶሮዎቹም ወደ ሞዛምቢክ የገቡት ከአጎራባች ደቡብ አፍሪካ ነው።

ወረርሽኙ ሞራሙቤኔ በተባለ የሞዛምቢክ ግዛት መስፋፋቱ ተገልጿል።

ወደሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት ስላለ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

የወፍ ጉንፋን ወይም በርድ ፍሉ በተለይም የዱር አእዋፍ የሚያጠቃ ሕመም ነው።

በንክኪ፣ በተበከለ ምግብና ውሃም ዶሮዎች በማቆያ ሳሉ በቀላሉ ሊሰራጭ ይችላል።

ይህ ወረርሽኝ መነሳቱ የእንቁላልና ዶሮ እጥረት አስከትሏል። ዋጋውም በሞዛምቢክ ንሯል።

ከ350 የሞዛምቢክ ሜቲካል ወደ 600 ነው በአንድ ጊዜ የዶሮ ዋጋ የጨመረው። እንቁላል ደግሞ ከ100 ሜቲካል 150 ገብቷል።

45ሺው ዶሮዎች እንዲወገዱ የተወሰነው በበሽታው ከተያዙ ዶሮዎች ጋር ንክኪ ስለነበራቸው እንደሆነ የሞዛምቢክ የእንስሳት ጥበቃ አስታውቋል።

ደቡብ አፍሪካ ገጥመዋት ከሚያውቁ ወረርሽኞች ከፋ የሆነውን ይህንን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየሞከረች ነው።

በአጠቃላይ ሰባት ሚሊዮን እንቁላል የሚጥሉ ዶሮዎች እንዲገደሉ ዶሮ አርቢዎችን አስገድዳለች። ይህም ከአገሪቱ ዶሮዎች መካከል ከ20-30% ነው።

የሞዛምቢክ ብሔራዊ እንስሳት ጥበቃ ባለሙያው አሜሪኮ ዳ ኮንሴችዮ እንዳሉት ዶሮና የዶሮ ተዋጽኦ ከደቡብ አፍሪካ እንዳይገባ አግደዋል።

ወረርሽኙ በተነሳበት የሞዛምቢክ ግዛት ዶሮና እንቁላል ስርጭትም ቆሟል።