ወሲባዊ ይዘት ካላቸው ፎቶዎች ጋር በተያያዘ በታገዱት ጋዜጠኛ ዙሪያ የቢቢሲ ኃላፊ ምላሽ እንደሚሰጡ ተጠቆመ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ወሲባዊ ይዘት ላላቸው ፎቶዎች ለታዳጊ ከፍለዋል በሚል በታገዱት የቢቢሲ ጋዜጠኛ ዙሪያ የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ጥያቄ ሊቀርብላቸው እንደሚችል ተጠቆመ።
ዋና ዳይሬክተሩ ቲም ዴቪ ዛሬ ሐምሌ 4፣ 2015 ዓ.ም የቢቢሲ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸምን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ለመስጠት ቀጠሮ ይዘዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ከጋዜጠኞች ጋር በሚኖራቸውም ቆይታ አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች ከሰሞኑ መወዛገቢያ የሆነው የቢቢሲ አቅራቢ ቅሌት ዙሪያ ሊሆን እንደሚችልም ተገምቷል።
ቢቢሲ የግል የመረጃ መብታቸው ጋር ይጣረሳል በሚል የአቅራቢውን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ጉዳዩ እስኪጣራም ድረስ የታገዱት ጋዜጠኛ ማንነት በዚህ መግለጫ ወቅት ዋነኛ ጥያቄም ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
የቢቢሲ የቴሌቪዥን መርሃ ግብር አቅራቢ አንድ ታዳጊ ወሲባዊ ይዘት ያለው ፎቶግራፍ እንዲልኩ መክፈላቸውን በመጀመሪያ የዘገበው ዘ ሰን ጋዜጣ ነው።
ማንነታቸው እንዲሁም ፆታቸው ያልተገለጸው ጋዜጠኛ ማንነታቸው እንዲሁም ፆታቸው ያልተገለጸ ታዳጊን ከ17 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ልቅ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ፎቶዎች እንዲልኩ በአስር ሺህ ፓውንዶች የሚቆጠር ገንዘብ መክፈላቸውን የጋዜጣው ሪፖርት ይጠቁማል።
የታዳጊው እናት ለጋዜጣው እንደተናገሩት፣ ልጃቸው ከ17 እስከ 20 ዓመት በዚህ ሂደት አልፈው፣ ከጋዜጠኛው የተከፈለን ገንዘብ ኮኬይን መግዣ ሆኗል።
ታዳጊውን እወክላለሁ ያሉ ጠበቃ በበኩላቸው ዘ ሰን ላይ የወጣውን ዘገባ በማጣጣል የወላጆቻቸውን ቅሬታ “እርባና ቢስ” ብለውታል።
ዘ ሰን ባለፈው ሳምንት ይህንን ጽሑፍ ከማተሙ በፊት በእናታቸው ስለቀረበው ክስ ታዳጊው ሐሰት ነው በማለት ምላሽ መስጠታቸውንም እኚሁ ጠበቃ ተናግረዋል።
ዘ ሰን በበኩሉ የእናትየውን ቅሬታ የሚደግፉ ማስረጃዎችን አግኝቻለሁ ብሏል።
ጠበቃው በበኩላቸው ታዳጊው ለጋዜጣው ቅሬታው ምንም ዐይነት እውነት እንደሌለው ጠቅሰው መልዕክታቸውን ቢልኩም ጋዜጣው ይህንኑ “ያልተገባ ጽሑፍ” በማተም ገፍተውበታል ብለዋል።
በተጨማሪም እናትየውና ታዳጊው ጸብ ላይ እንደሆኑና ምንም ዓይነት ንግግር የላቸውም ሲሉም ጠቅሰዋል።
“የቢቢሲ ጋዜጠኛ ባህርይና የልጃቸው ደህንነት ጉዳይ ስላሳሰባቸው ሁለት ወላጆች ታሪክ ዘግበናል” በማለት ዘ ሰን ምላሽ ሰጥቷል።
“ቅሬታቸውን ለቢቢሲ ቢያቀርቡም ችላ ተብለዋል። ስጋቶቻቸውን የሚደግፉ ማስረጃዎች አይተናል። ማጣራትና መመርመር የቢቢሲ ሥራ ነው” ሲል ዘ ዘሰን አክሏል።
ዘ ሰን እንደዘገበው የታዳጊ ቤተሰቦች ለቢቢሲ ቅሬታቸውን ግንቦት ላይ አስገብተዋል።
ተቋሙ ጉዳዩ “በፍጥነት እንደሚመረመር” መግለጹም ተዘግቧል።
የቢቢሲ ቃል አቀባይ “ማንኛውንም ክስ በቁም ነገር ነው የምንወስደው። ይህንን የሚመለከት አሠራርም አለን” ሲሉ ተናግረዋል።












