የምክር ቤት አባላቱ ጠበቃ እንዳያገኙ መከልከላቸውን ጠበቃቸው እና የቤተሰብ አባሎቻቸው ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, SM
በአማራ ክልል የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብታቸው ቢነሳም እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ቤተሰቦቻቸው እና ጠበቃቸው ተናገሩ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሳ ተሻገር እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ከስድስት ወራት በላይ በአዋሽ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ ማቆያ ታስረው ቆይተዋል።
ከሁለት ወር ገደማ በፊት ደግሞ ወደ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተዛውረው በዚያ ታስረው እንደሚገኙም የቤተሰብ አባሎቻቸቸው እና ጠበቃቸው ተናግረዋል።
የምክር ቤት አባላቱ ለምን ወደ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንደተዛወሩ ምክንያቱን እንደማያውቁ ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆነት አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ገልጸዋል።
ሆኖም ያለመከሰስ መብታቸው በተነሳበት ወቅት በምክር ቤቶቹ ከተሰጡት ማብራሪያዎች በመነሳት ወደ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያመጧቸው ክስ ለመመሥረት አስበው ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ያለመከሰስ መብታቸው በተነሳበት ወቅት የተሰጠው ማብራሪያ ተጠርጣሪዎቹን በሽብር አዋጅ እና በወንጀል ሕግ ክስ ለመመሥረት የሚያስችል መረጃዎችን ማግኘታቸውን መጠቆሙን ጠበቃው አስታውሰዋል።
እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት ያልቀረቡት የምክር ቤት አባላቱ፣ አዋሽ አርባ በነበሩበት ወቅት በተደጋጋሚ ለሕክምና ይመጡ እንደነበር እና አሁንም በከፋ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ከቤተሰቦቻቸው መረዳታቸውንም ጠበቃ ሰለሞን ተናግረዋል።
“አቶ ዮሐንስ ቧያለው ለሕክምና በመጣበት ወቅት ሌላ እስረኛ ለመጎብኘት ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ስሄድ አይቻቸዋለሁ። አካላቸው ተጎሳቁሏል። የአካባቢው የአየር ሁኔታ ሁለመናቸውን እንደቀየራቸውም ከቤተሰባቸው ሰምቻለሁ” ብለዋል።
ለወራት በእስር ላይ የቆዩት የምክር ቤት አባላቱ ለከባድ የጤና እክል መዳረጋቸውንም ቢቢሲ ከቤተሰቦቻቸው ሰምቷል።
ጠበቃቸውም ደንበኞቻቸውን አግኝተው ለማነጋገር እና ስላሉበት ሁኔታ ለመረዳት ሜክሲኮ ወደሚገኘው የፌደራል ወንጀል ምርመራ ክፍል ሄደው ቢጠይቁም ፈቃድ እንዳላገኙ ተናግረዋል።
“ይሄ የእኛ ሥልጣን አይደለም። ስለዚህ ጠበቃ እንዲያገኙ የሚፈቅደው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድ አሊያም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የሚመለከተው አካል እንጂ እኛን አይመለከተንም። እኛ አቆዩ ነው የተባልነው። የማገናኘት ፈቃድ አልተሰጠንም” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባላቱ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንደሚገኙ እና በቀን አንድ ጊዜ ምግብ እንዲያቀብሏቸው እንደተፈቀደላቸው የሚገልጹት የቤተሰብ አባሎቻቸውም እንግልትና ማዋከብ እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል።
ከአራት ቀናት በፊት አቶ ዮሐንስ ቧያለውን በስልክ እንዳነጋሯቸው የሚገልጹት የቤተሰብ አባል “ስላለባቸው የጤና ችግር እና እንግልት በነጻነት ለመናገር እንኳን ተቸግረዋል” ብለዋል።
የምክር ቤት አባላቱ ከዚህ ቀደም አዋሽ አርባ በነበሩበት ወቅት የሚደርሰባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወም የረሃብ አድማ አድርገው ለጤና ችግር ተዳርገው እንደነበርም ተገልጿል።
“የጨለማ ክፍል ውስጥ ለረዥም ጊዜ ታስረዋል”
ከሦስት ቀናት በፊት እንደተጻፈ በሚገልጽ እና የምክር ቤት አባላቱን ጨምሮ በ14 እስረኞች ፊርማ በወጣ በእጅ የተጻፈ ደብዳቤ ላይ፣ በእስረኞቹ ላይ ከፍተኛ እንግልት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈፀመባቸው ይገልጻል።
ከታሳሪዎቹ የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ የተላከው ይህ ደብዳቤ ማንነትን መሠረት ያደረገ ስድብ፣ ዛቻ፣ ማስፈራራት እና ድብደባ እንደተፈፀመባቸው፤ እንዲሁም ከታሰሩ ከሰባት ወራት በላይ ቢሆናቸውም ከጠበቃ፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከቤተሰብ፣ ከሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጋር እንዳይገናኙ መደረጋቸውን ይገልጻል።
ከዚህም በተጨማሪ ለምግብ እጥረት እና ለተለያዩ በሽታዎች መዳረጋቸው፣ ታስረው በቆዩበት የአዋሽ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በመቃብር ቦታ እና የዱር አውሬዎች በሚገኙበት ስፍራ መታሰራቸው ሞራላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ እንዳደረሰባቸው፣ እንዲሁም በጨለማ ክፍል ውስጥ ተዘግተው እንደሚውሉ ያትታል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ቤተሰቦቻቸውም የጨለማ ክፍል ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።
የአቶ ዮሐንስ ቧያለው የቤተሰብ አባል የሆኑት ግለሰብ “ምግብ ሊቀበለኝ ሲመጣ ለማየት ሲቸገር አየሁት። ምን ሆነህ ነው? ብዬ ስጠይቀው ‘በጨለማ ክፍል ውስጥ እያስገቡን ስለነበር ዐይኔ ችግር አለበት’ አለኝ” ብለዋል።
በአማራ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በክልሉ ውስጥ እና እንዳስፈላጊነቱ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን ለስድስት ወራት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥር 24/2016 ዓ.ም. ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙ ይታወሳል።
ከዚሁ አዋጅ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ከሚገኙት መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ክርስቲያን ታደለ አንዱ ናቸው።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት እንደራሴ የነበሩት ዶ/ር ካሳ ተሻገርም ላለፉት ወራት በተመሳሳይ ሁኔታ በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ የሚሆንበት የስድስት ወራት ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ለተጨማሪ አራት ወራት ከተራዘመ በኋላ የምክር ቤቱ አባላቱ ያለመከሰስ መበት መነሳቱ ይታወሳል።












