ግዙፉ የነዳጅ ኩባንያ ሼል ምርት መቀነስ ‘አደገኛ’ ነው ሲል አስጠነቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የነዳጅ እና የጋዝ ምርቶችን መቀነስ ‘አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው ነው” ሲሉ የግዙፉ የኢነርጂ ኩባንያ ሼል ኃላፊ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ኃላፊው ዋኤል ሳዋን አማራጭ በሆኑ ታዳሽ ኃይሎች ለመተካት የሚደረገው እንቅስቃሴ በፍጥነት የሚሳካ እንዳልሆነ ጠቅሰው አለማችን አሁንም “ነዳጅ እና ጋዝ በከፍተኛ ሁኔታ ትፈልጋለች” ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል።
የቻይና በነዳጅ ላይ ያላት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር እና የአውሮፓ ቅዝቃዜ የነዳጅ ዋጋን ሊያንር እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።
ኃላፊው የሼል ኩባንያ እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ድረስ የነዳጅ ምርቱን ለማስቀጠል እቅድ መያዙን መናገራቸውን ተከትሎ የአካባቢ ተሟጋቾችን አስቆጥቷል።
በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የአየር ንብረት ሳይንቲስት የሆኑት ፕሮፌሰር ኤሚሊ ሹክበርግ እንዳሉት እንደ ሼል ያሉ የነዳጅ ኩባንያዎች አለም ወደምታደርገው የአረንጓዴ ኃይል ሽግግርን በማፋጠን ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
“በህብረተሰቡ ውስጥ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦች የነዳጅ እና ጋዝን ከመጠቀም ውጭ አማራጭ የላቸውም የሚለውን እሳቤ ኩባንያዎቹ ሊተውት ይገባል” ብለዋል።
ኃላፊው በበኩላቸው በዚህ አስተያየት እንደማይስማሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ የነዳጅ እና የጋዝ ምርቶችን መቀነስ አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው ነገር ነው። ባለፈው ዓመት እንዳየነው ይህ ሁኔታ ዋጋውን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሻቅብ ምክንያት ይሆናል” ሲሉም ተናግረዋል።
የዓለም መሪዎች ዓለማችን በ1.5 ሴንቲግሬድ ከመሞቅ ለመከላከል ቃል በገቡት መሰረት ነዳጆችንና ጋዞችን በታዳሽ ኃይልና በአረንጓዴ አማራጮች ለመተካት ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
ባለፈው ዓመት የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ነዳጅ እና ጋዝ ላይ ያለውን ጥገኝነት አክትሞ ወደ አረንጓዴ ኢነርጂ የሚያደርገውን ሽግግርም ለማፋጠን እንደሚሰራ ገልጿል።
ሆኖም በርካታ አገራት ታዳሽ ወደሆኑ ዘላቂ የኃይል አማራጮች ለመሸጋገር መሰረተ ልማት የላቸውም።
ኃላፊው እንዳሉት ባለፈው ዓመት በነበረው የዓለም አቀፍ የጋዝ ፉክክር እንደ ፓኪስታን እና ባንግላዴሽ ያሉ ታዳጊ ሃገራት የኃይል እጥረት እንዲያጋጥማቸው ምክንያት ሆኗል። እነዚህ ሃገራት ፈሳሹን የተፈጥሮ ጋዝ (ኤልኤንጂ)ን መግዛት ስላልቻሉም ለሰሜን አውሮፓም መዘዋወሩም ጠቁመዋል።
እነዚህ ሃገራት የተፈጥሮ ጋዝ በውስን መልኩ ከበለጸጉ ሃገራት ማምጣት ቢችሉም ባጋጠማቸው ኃይል መቆራረጥ “ተማሪዎች በሻማ እንዲያጠኑ ተገደዋል” ብለዋል።
አክለውም “ሽግግር የምናካሂድ ከሆነ ለአንድ የዓለም ክፍል ብቻ የማይሰራ ፍትሃዊ ሽግግር መሆን አለበት” ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች የሆነው ኮሚቴ በበኩሉ የቤት ውስጥ የጋዝ መገልገያ መሳሪያዎች ከመተንፈሻ አካላት ችግር እና የልብና የደም ስር በሽታዎች ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን አረጋግጧል።












