መልካም ጓደኝነት እና ማኅበራዊ ሕይወት ለጤና እና ለረዥም ዕድሜ ያላቸው ጠቀሜታ

ጓደኛሞች ሲሳሳቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ልክ እንደ የሰውነት ማጎልመሻ እንቅስቃሴ ሁሉ ማኅበራዊ ትስስርም ጤናዎ ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል ይላሉ በቅርቡ ይህን የተመለከተ መፅሐፍ ያሳተሙት ዴቪድ ሮብሰን።

በሰው ልጅ ጤና እና ረዥም ሕይወት በመኖር መካከል ያለው ቁርኝንት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረት እያገኘ መጥቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነትም እየተነሳ ይገኛል።

ማኅበራዊ ትስስራቸው ጠንካራ የሆኑ ሰዎች ብቸኝነት ከሚያዘውትሩ ጋር ሲነፃፀሩ ጤናቸው መልካም እንደሆነ እየተነገረን ነው።

ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ረዥም ዕደሜ ከመኖር ጋር ያለውን ቁርኝት የተረዳው የዓለም ጤና ድርጅት የማኅበራዊ ትስስር ኮሚሽን አቋቁሟል፤ “ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ የጤና ጉዳይም ነው” ብሏል።

እንዴት ሆኖ ነው ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ለጤናችን ጠቃሚ የሚሆነው? የሚለው ሐሳብ ግራ አጋቢ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በዘርፉ የሚደረጉ ጥናቶች በተለይ ባለፉት አስርት ዓመታት እየተጠናከሩ መጥተዋል።

የዘርፉ ሰዎች እንደሚሉት ጓደኛ የማፍራት አቅማችን የሰውነታችንን በሽታን የመከላከል አቅም ሊያጠናክረው ከመቻሉም ባለፈ ከልብ ህመም ጋርም ሊቆራኝ ይችላል።

በአጠቃላይ ረዥም ዕድሜ እና ጤናማ ሕይወት እንዲኖረን ከፈለግን በአቅራቢያችን ያሉ ሰዎችን ቅድሚያ ልንሰጣቸው ይገባል።

የዚህ ሳይንስ መሠረት የተጣለው በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ ነው። በወቅቱ የካሊፎርኒያ ግዛት የሕብረተሰብ ጤና ኃላፊ የነበረው ሌስተር ብሬስሎው ረዥም ዕድሜ ለመኖር ምን ያስፈልጋል? የሚለውን ለማወቅ የተለጠጠ ዕቅድ አወጣ።

ይህን ለማጣራት ከአልሜዳ ክፍለ ግዛት 7 ሺህ ተሳታፊዎችን መርጦ ቃለ-መጠይቅ በማደል የሕይወት ዘይቤያቸውን እና ጤናቸውን ለተከታታይ ዓመታት መረመረ።

የሌስተር የጥናት ቡድን ዘንድሮ ለጤናችን ጠቃሚ ናቸው የምንላቸውን ጉዳዮች መርጦ አወጣ። ለምሳሌ ትምባሆ አለመጫስ፣ ብዙ አልኮል አለመጠጣት፣ ከ7 እስከ 8 ሰዓታት እንቅልፍ ማግኘት፣ ስፖርት መሥራት፣ ክብደትን መቆጣጠር፣ ቁርስ መብላት ተካተውበታል።

የጥናት ቡድኑ አባላት እነዚህን የጥናት ውጤቶች ለሌስተር ይፋ ሲያደርጉለት ቀልድ የያዙ መስሎት ነበር። ነገር ነገር ግን ይህ “አልሜዳ 7” ተብለው የሚጠራው ጥናት ባለንበት ዘመንም ጥቅም ላይ ይውላል።

ሶስት ሴቶች በሩጫ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በ1979 የሌስተር ጥናት ቡድን አባላት የነበሩት ሊሳ በርክማን እና ሌዎናርድ ሳይም፤ ረዥም ዕድሜ ለመኖር አስፈላጊ ነው ያሉትን ስምንተኛ ጉዳይ ማግኘታቸውን ገለጹ። ይህ ምንድነው? ሲባሉ ማኅበራዊ ትስስር ነው አሉ።

በአማካይ በርካታ ወዳጅ ዘመድ ያላቸው ሰዎች ብዙም ማኅበራዊ ትስስራቸው ካልጠነሩ ሰዎች ጋር ሲነፃፀሩ ረዥም ዕድሜ ይኖራሉ። ጥናቶች እየሰፉ ሲመጡ ሁሉም ዓይነት ግንኙነቶች ጠቃሚ ቢሆኑም በተለይ አንዳንዶች የበለጠ ጥቅም እንዳላቸው መረዳት ተቻለ።

ከትዳር አጋር ጋር ያለ ግንኙነት እና ከቅርብ ጓደኞች ጋር የሚመሠረት ቅርበት የበለጠ ጥቅም ያለው ሲሆን፣ ቤተ-እምነት አሊያም ትርፍ ጊዜ የምናሳልፋባቸው ልምዶችም ትሩፋታቸው መልካም ነው።

በወቅቱ ይህ የጥናት ውጤት ይፋ ሲሆን በፐብሊክ ሄልዝ መመሪያዎች ላይ ለመካተት ጊዜ ወስዶበት ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት ሳይንቲስቶች ሰውነታችንን ልክ እንደ ማሽን ይመለከቱት ስለነበር እና ከአእምሮ ጤናችን እና ከአካባቢያችን ጋር ያለውን ግንኙነት መመርመር ያልጀመሩበት ወቅት ስለነበር ነው።

ከዚያ በኋላ የተሠሩ በርካታ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ማኅበራዊ ትስስር እና ብቸኝነት ለተለያዩ በሽታዎች ያለንን ተጋላጭነት ሊወስኑት ይችላሉ።

ዋና ዋና ጥቅሞች

ከማኅበራዊ ትስስር የምናገኘው ጥቅም ለሰውነታችን ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል አቅም አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው።

በ1990ዎቹ በዩኤስ የካርኒጌ ሜለን ዩኒቨርሲቲው ሼልደን ኮኽን 276 ተሳታፊዎችን መርጦ ስለማኅበራዊ ትስስራቸው ሙሉ መረጃ እንዲሰጡት ጠየቀ።

ተሳታፊዎች ጤናቸው ከተመረመረ በኋላ ሪኖቫይረስ የተባለው ሳል እና ማስነጠስ የሚያመጣው ቫይረስ ተሰጥቷቸው ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደረገ። በሚቀጥሉ አምስት ቀናት ተሳታፊዎቹ የህመም ምልክት ማሳየት ቢጀምሩም የተሻለ ማኅበራዊ ትስስር ያላቸው ግን የተሻለ መቋቋም ቻሉ።

ብዙ ወዳጅ ዘመድ የሌላቸው ሰዎች ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ የሥራ አጋር እና የፍቅር ጓደኛ ካላቸው ሰዎች ጋር ሲነፃፀሩ በጉንፋን የመያዛቸው ዕድል ከሦስት እስከ አራት እጥፍ ከፍ ያለ ነው።

ውፍረት ለስኳር በሽታ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው። ማኅበራዊ ትስስር እንደ ዓይነት 2 የስኳር በሽታ ያሉ ከማይድኑ በሽታዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ጥናቶች ይጠቁማሉ።

አራት ሺህ ሰዎች የተሳተፉበት የዩሲኤልኤ ጥናት፤ ማኅበራዊ ትስስራቸው ጠንካራ የሆኑ ሰዎች እንደ አልዛይመር ካሉ ከእርጅና ጋር ተያይዘው በሚመጡ በሽታዎች የመያዝ ዕድላቸው ዝቅ ያለ ነው ይላል።

ብቸኝነት ከላይ ከተጠቀሱት ጉዳቶች በተጨማሪ ለከፍተኛ የደም ግፊት፣ ለልብ ህመም እና ለስትሮክ የመጋለጥ ዕድልን 30 በመቶ ሊጨምር ይችላል።

ብቻዋን የተቀመጠች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአውሮፓውያኑ 2010 የወጣ ጥናት ደግሞ የማኅበራዊ ትስስራችን ጥራት እና መጠንን ይመለከታል። ሰዎች በአቅራቢያቸው ካሉ ሰዎች ድጋፍ የሚያገኙ ከሆነ ጤናቸው መልካም የመሆኑ እና ረዥም ዕድሜ የመኖራቸው ዕድል ከፍ ያለ ነው።

በአጠቃላይ ማኅበራዊ ትስስር አሊያም ብቸኝነት፤ አልኮል ከመጠጣት፣ ከስፖርት፣ ከሰውነት ክብደት እና ከአየር ጥራት የበለጠ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል።

የማኅበራዊ ትስስራችን ጥንካሬ እንዲሁም በጤናችን ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለመረዳት ወደ ዝግመተ ለውጥ ፅንሰ-ሐሳብ መጓዝ አለብን። ጥንታዊው የሰው ልጅ አብሮ መኖር የለመደው ምግብ ለመጋራት እና ከአደጋ ራሱን ለመጠበቅ ነው። ብቸኝነት ለረሃብ፣ ለበሽታ እና ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል ማለት ነው።

በዚህ ምክንያት አእምሯችን እና ሰውነታችን ብቸኝነትን እንደ ትልቅ አደጋ አድርጎ ወስዶት ሊሆን ይችላል። ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ብቻችንን ስንሆን ሐዘን የሚሰማን።

ልክ የሰውነት አካላችን ላይ ጉዳት ሲደርስ ለቁስላችን እንክብካቤ እንደምናደርገው ሁሉ ከብቸኝነት ለመሸሽ ማኅበራዊ ትስስር እንመሠርታለን።

ሰውነታችንን ለማበልፀግ ስፖርት እንደምናዘወትረው ሁሉ በሕይወታችን ትርጉም ያላቸው ግንኙነቶች መመሥረት ሊጠቅመን ይችላል። ያሉንን ግንኙነቶች ማጠናከር እና አዳዲስ መመሥረት ይመከራል።