ታዋቂው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ እና ገጣሚ ነቢይ መኮንን አረፈ

ነቢይ መኮንን

የፎቶው ባለመብት, enedalgeta multimedia/yt

የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ታዋቂው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ነቢይ መኮንን ባደረበት ህመም ምክንያት ማረፉን ጋዜጣዋ እና የቅርብ ወዳጆቹ ተናገሩ።

የቅዳሜ ዕለት ተወዳጅ ጋዜጣ የነበረችውን አዲስ አድማስ ጋዜጣን ከመሠረቷት መካከል አንዱ የነበረው ነቢይ ጋዜጣዋን እስከ ህልፈቱ ድረስ በዋና አዘጋጅነት ሲመራ ቆይቷል።

ነቢይ መኮንን ከጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅነት በሻገር በድንቅ የግጥም ሥራዎቹ፣ ቀልብን በሚይዙ የድርሰት ጽሑፎቹ እና ተወዳጅ በሆኑት የትርጉም ሥራዎቹ አድናቆትን አትርፏል።

ነቢይ መኮንን ህመም አጋጥሞት የህክምና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ጋዜጣው አዲስ አድማስ በፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሮ፣ ረቡዕ ሰኔ 26/2016 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ሕይወቱ ማለፉን ገልጿል።

በአዳማ ተወልዶ ያደገው ገጣሚ፣ ተርጓሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን ትምህርቱን የተከታተለው በዚያው ናዝሬት (አዳማ) አጼ ገላውዲዮስ ትምህርት ቤት ነው።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኬሚስትሪ ትምህርት የተመረቀ ቢሆንም በጋዜጠኝነት፣ በተርጓሚነት እና በደራሲነት በርካታ ሥራዎችን ለአንባቢያን አበርክቷል።

የአዲስ አድማስ ዋና አዘጋጅ የነበረው ነቢይ መኮንን በጋዜጣው ላይ በየሳምንቱ በተረት እና ምሳሌ እያዋዛ በሚጽፋቸው ርዕሰ አንቀጾች ይታወቃል።

የአዲስ አድማስ ዋና አዘጋጅ የነበረው ነቢይ ከዓመታት በፊት “ባለጉዳይ” የተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ለዕይታ ከማብቃቱም በላይ በትወናም ተሳትፏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእዚህ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ጭብጥ ከመሬት ጋር የተያያዘ የሙስና ጉዳይ ሲሆን፣ ታዋቂዎቹ አበበ ባልቻ እና ፈቃዱ ተክለማሪያም እና ፍቅርተ ጌታሁንን ጨምሮ ራሱ ነቢይ መኮንን እና ሌሎችም ታዋቂ ተዋንያን ተሳትፈውበታል።

ይህ ተከታታይ ድራማ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 10 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ሲታይ አድናቆትን አግኝቶ ነበር።

ነቢይ “ናትናኤል ጠቢቡ” እና “ጁሊየስ ቄሳር” የተሰኘ ተውኔቶችንም ተርጉሞ ለመድረክ አቅርቧል።

"ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነኝ" የሚለው ነቢይ ባለካባ እና ባለዳባ በተሰኘው ተውኔት ላይም በትወና ተሳትፏል።

የአዲስ አድማስ ጋዜጣን ለረዥም ጊዜ በዋና አዘጋጅነት የሠራው ነቢይ ገጣሚ እና ተርጓሚም ነበር።

“ስውር ስፌት” የተሰኘ የግጥም መድብል በሁለት ቅጽ ለንባብ አብቅቷል።

በደርግ ዘመን በኢህአፓ አባልነት ለ10 ዓመታት የታሰረው ነቢይ፣ በእስር ቤት እያለ ‘ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ’ የተሰኘውን ታዋቂ ረጅም ልቦለድ መጽሐፍን ‘ነገም ሌላ ቀን ነው’ በሚል ወደ አማርኛ ተርጉሞ ለንባብ አብቅቷል።

ነቢይ ‘ነገም ሌላ ቀን ነው' የተሰኘውን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ እስር ቤት ሳለ ነበር የተረጎመው።

ይህንንም የትርጉም ሥራውን በሲጋራ ወረቀት ላይ እየጻፈ በድብቅ ከእስር ቤት በማስወጣት በመጨረሻ ሲፈታ መታተሙን በሕይወት እያለ ተናግሯል።

ሁለገብ የሥነ ጽሁፍ ሰው የሆነው ነቢይ በ1970ዎቹ መጨረሻ ለህትመት የበቃው ይህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ዕትም በሳንሱር ምክንያት መግቢያው እና አንዳንድ ሃሳቦቹ ተቆራርጠው የታተመ ቢሆንም፤ ዳግም ለህትመት ሲበቃ ግን ያልታተመው መግቢያው ታክሎበት በአዲስ መልክ ታትሟል።

ነቢይ “የኛ ሰው በአሜሪካ” - የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻው በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ሲወጣ ቆይቶ፣ ኋላ ላይ በመጽሐፍ ተዘጋጅቶ ለህትመት የበቃ ሌላኛው ሥራው ነው።

ይህ መጽሐፍ በአሜሪካ በሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ላይ ያተኮረ ነው።

ሌላው ለንባብ የበቃው የነቢይ መጽሐፍ “የመጨረሻው ንግግር” የተሰኘ ሲሆን “ዘ ላስት ሌክቸር” የሚለው መጽሐፍ ትርጉም ነው።