መካከለኛው ምስራቅ የለየለት የጦርነት ቀጣና ይሆናል? የኃያላን ሀገራት አጀንዳስ ምንድነው?

የእስራኤል አየር ኃይል በደቡባዊ ሊባኖስ ያደረሰው የቦንብ ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል አየር ኃይል በደቡባዊ ሊባኖስ ያደረሰው የቦንብ ጥቃት

እስራኤል እግረኛ ጦሯን ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ አዝምታለች። ኢራን ደግሞ 200 ገደማ ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል ተኩሳለች። እስራኤል ደግሞ የመን የሚገኙ ሁቲዎችን በቦምብ ደብድባለች።

ይህ በጦር መሣሪያ የታገዘ እሰጥ አገባ መካከለኛው ምስራቅ እልም ወዳለ ጦርነት እንዳይገባ ስጋት ጭሯል።

ለመሆኑ መካከለኛው ምስራቅ ወደለየት ጦርነት የመግባቱ አዝማሚያ እንዴት ነው? የቢቢሲ ተንታኞች ምን ይላሉ?

በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ሁኔታ ለመግለፅ “ከጫፍ ደርሷል” የሚል ቃል ብዙውን ጊዜ እንጠቀማለን ትላለች የቢቢሲዋ ተንታኝ ናዋል አክ-ማጋፊ።

በጋዛ ባለው ጦርነት ምክንያት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ40 ሺህ በላይ ሆኗል። በሊባኖስ ደግሞ በአንድ ሳምንት ብቻ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። አንዳንድ ሥፍራዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።

ናዋል እንደምትለው መካከለኛው ምስራቅ ለዓመታት ደርሶበት የማያውቀው ቀውስ ውስጥ ነው ያለው።

ባፈለው ሳምንት የሔዝቦላሕ መሪ የነበሩት ሐሰን ናስራላሕ ሲገደሉ በእስራኤል ጎዳናዎች ላይ ፌሽታ ሆኖ ነበር።

የኢራን የፍልሚያ ግንባር ከሚባሉት መካከል ሔዝቦላሕ እና ሐማስ መሪዎቻቸውን በጥቂት ሳምንታት ልዩነት አጥተዋል። ምንም እንኳ እስራኤል የሔዝቦላሑን ናስራላሕ እና የሐማስን ሀኒዬ ብትገድልም በቴል-አቪቭ ጎዳናዎች ላይ የነበረው ጭፈራ የልጅ ጨዋታ ነው ትላለች ናዋል።

እርግጥ ነው እስራኤል በጠላቶቿ ላይ ትልቅ ድል ተቀዳጅታለች። ቤይሩት ላይ ባደረሰቻቸው የአየር ድብደባዎች የሔዝቦላሕ ከፍተኛ አመራሮችን ገድላለች።

እስራኤል ከሐማስ ጋር እያደረገች ያለችው አንድ ዓመት የፈጀ ጦርነት በጋዛ ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን ብዙ ሰቆቃ ይዞ መጥቷል።

ምንም እንኳ የፍልስጤሙ ሚሊሻ በጦርነቱ እጅጉን ቢጎዳም የሐማስ መጨረሻ ተቃርቧል ብሎ ማውራት ግን ከባድ ነው።

አንድ ታዳጊ በሊባኖስ ከተማ ፍርስራሽ መካከል

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሐማስ ጠፍቷል ብለው የሚያምኑ ሰዎች መሰል ቡድኖች እንዴት እንዲመሠርቱ እና እንደሚፀኑ ብዙ ግንዛቤ አይኖራቸው ይሆናል።

እንደ ሐማስ ያሉ ቡድኖች ሥር መሠረት አላቸው፤ በማኅበረሰቡ እና በፖለቲካዊ መዋቅር ውስጥ ዘልቀው የገቡ ናቸው።

የናስራላሕ መገደል እና ኢራን እስራኤል ላይ ያደረገችው የሚሳዔል ጥቃት ቀጣናውን ወደለየለት የጦርነት አውራጃ ሊያደርገው ተቃርቧል።

የኢራን ጥቃትን ተከትሎ የእስራኤል ባለሥልጣናት ያሰሙት ንግግር ተጨማሪ ግጭት መሰማቱ አይቀሬ መሆኑን አሳይቷል። በተለይ ደግሞ እስራኤል እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ የሚያስብል ሆኖ ታይቷል። በኢራን የሚደገፉ ሊባኖስ፣ ሶሪያ፣ የመን እና ኢራቅ ያሉ ቡድኖች እና የእስራኤል አጋሮች የሆኑት ዩኬ እና ዩኤስን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራትም ሊሳተፉ ይችላሉ።

አሁን ትልቁ ጥያቄ እስራአል ምን ዓይነት ምላሽ ትሰጣለች የሚለው ሆኗል።

የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት “በ50 ዓመታት ውስጥ ይህን የመሰለ የመካከለኛው ምስራቅን መቀየር የሚችል አጋጣሚ የለም” ሲሉ በኤክስ ገፃቸው ፅፈዋል።

ይህን ያሉት እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር ክምችት ዒላማ እንድታደርግ ሐሳብ በሚሰጠው መልዕክታቸው ነው።

የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ግጭቱን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም። ምዕራባዊያን ኃያላን ሀገራትም ግጭቱን የማስቆም ጉልበት እንደሌላቸው ታይቷል።

የኃያላን ሀገራት ግጭትን ለማስቆም ያላቸው አቅም መዳከሙ ዓለማችን ወዴት እያመራች ነው የሚል ጥያቄ ጭሯል። የመካከለኛው ምስራቅ ዕጣ ፈንታም አደጋ ውስጥ ነው።

በሊባኖስ እስራኤል ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ የታየው ፍርስራሽ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሊባኖሳዊያን ጦርነት ሰልችቷቸዋል። አሁን ያለው ጦርነት አይመለከትንም የሚል አስተሳሰብ አላቸው

የመካከለኛው ምስራቅ ተንታኟ የቢቢሲ አራቢክ ባልደረባ ናስሪን ሀቱም ከላይ በተጠቀሱት ሐሳቦች ትስማማለች። ሊባኖስ የለየለት ጦርነት ውስጥ የመግባት አቅም ላይ አይደለችም ትላለች።

ሶሪያ፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ የመን እንዲሁም ዮርዳኖስ በዚህ ጦርነት ላይ ሊሳተፉ ይችላሉ። ከዚህ ቀደም የለየለት ጦርነት ይነሳል የሚል ፍራቻ ነበር። ማክሰኞ ምሽት ኢራን እስራኤል ላይ ካደረገችው የሚሳዔል ጥቃት በኋላ ግን ይህ ፍራቻ ወደ እውነትነት እየተቀየረ ነው። ኢራን ተጨማሪ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች የሚል ስጋትም ተጭሯል።

ኢራን ዳግመኛ ጥቃት እስራኤል ላይ የምትሰነዝር ከሆነ የቴል አቪቭ ወዳጅ የሆኑት አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ጣልቃ ሊገቡ ይችላሉ።

እስራኤል ጥቃት እየሰነዘረች ያለችው ሔዝቦላሕ ላይ ነው እንጂ የሊባኖስ ጦር ላይ አይደለም። የሊባኖስ መከላከያ ሠራዊት ጦርነት እንዲቀሰቀስ አይፈልግም።

ፈረንሳይ የምትመራው የሀገራት ቡድን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ደፋ ቀና እያለ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ዓላማ የሊባኖስ ጦርን አጠናክሮ ወደ ደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍል መላክ ነው።

ሊባኖሳዊያን ለጦርነት ምንም ፍላጎት የላቸውም ትላለች ናስሪን። በተለይ ደግሞ 2019 ላይ በሀገሪቱ ከተከሰተው የምጣኔ ሀብት ቀውስ ወዲህ ነዋሪዎች ሌላ ቀውስ ውስጥ መግባት አይፈልጉም።

አንዳንድ ሊባኖሳዊያን ይህ ጦርነት አይመለከተንም፤ ተጎትተን ነው የገባነው ብለው ያስባሉ።

ኢራን ላይ የደረሰው የሚሳዔል ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

የምስሉ መግለጫ, ኢራን ባለፈው ሚያዚያ እስራኤል ላይ የሚሳዔል ጥቃት ማድረሷ ይታወሳል

በርካቶች የኢራን የሚሳዔል ጥቃት የእስራኤልን ሐሳብ ሊያስቀይረው ይችላል የሚል እምነት አላቸው። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ፖለቲካዊ ቅርፅ መቀየር ይፈልጋሉ።

ይህን ለማድረግ ደግሞ ኢራን አሊያም በእሳቸው አነጋገር “የእባብ ጭንቅላትን” ዒላማ ሳያደርጉ የሚሆን ነገር አይደለም።

ኢራን ጥቃት ከተሰነዘረባት ሌሎች አጋር ሀገራትን ወደ ጦርነቱ ልታስገባ ትችላለች። ይህ ደግሞ ጦርነት ከቀጣናው አልፎ ዓለም አቀፋዊ ሊሆን ነው ማለት ነው።

እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር ማብላያ መምታት ትሻለች። ጥያቄ አሜሪካ ለእእራኤል ይሁንታ ትሰጣለች ወይ? ነው።