በየሦስት ደቂቃው አንድ ሰው በመኪና አደጋ የሚሞትባት የዓለማችን አደገኛ አገር

ሙምባይ ውስጥ የሚገኝ ማሳለጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሕንድ ከአሜሪካ በመቀጠል በዓለም ሁለተኛ የመንገድ መሠረተ ልማት ያላት አገር ናት

በየሦስት ደቂቃው አንድ ሰው በተሽከርካሪ አደጋ ሕይወቱን በማጣት ሕንድ በዓለም ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ የሚከሰትባት አገር መሆኗን አንድ ሪፖርት አመለከተ።

በአንድ ዓመት (2023) ብቻ በመንገድ ላይ በተሽከርካሪዎች አማካኝነት ባጋጠሙ አደጋዎች ከ172 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ ይህም በየቀኑ በአማካኝ 474 ሰዎች እንዲሁም በየሦስት ደቂቃው ደግሞ አንድ ሰው በአደጋ ለሞት መዳረጉ ተገልጿል።

በአገሪቱ በተጠቀሰው ጊዜ ከ480 ሺህ በላይ የተሽከርካሪ አደጋዎች የተመዘገቡ ሲሆን በእነዚህ ሳቢያም ከ170 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ፣ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በዓመቱ በአደጋ ከሞቱት ሰዎች መካከል 10 ሺህ የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው። በትምህርት ቤቶች እና በኮሌጆች አካባቢ የደረሱ አደጋዎች ደግሞ ሌሎች 10 ሺህ ሰዎች ላይ ጉዳት ሲያደርሱ፣ 35,000 እግረኞች ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል።

ሪፖርቱ እንዳለው ከልክ በላይ መፍጠን በሕንድ ውስጥ ለተከሰቱት የትራፊክ አደጋዎች ዋነኛው ምክንያት ሲሆን፣ ብስክሌት እና ሞተር ላይ በሚደርሱ አደጋዎች የራስ ቅል መከላከያ ቆብ (ሄልሜት) ባለማድረግ 54,000 ሰዎች እንዲሁም 16,000 የሚሆኑት ደግሞ የመቀመጫ ቀበቶ ባለማሰር ለሞት ተዳርገዋል።

ሌሎቹ ለሰው ሞት ምክንያት የሆኑት ደግሞ ከልክ በላይ መጫን 12,000 ሞት፣ ካለ መንጃ ፈቃድ ማሽከርከር ደግሞ ለ34,000 አደጋዎች ምክንያት ሆኗል። የመንገድ ላይ ደንብን ጠብቆ አለማሽከርከርም ከፍተኛ ጉዳትን ማስከተሉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

አደጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሕንድ የመንገድ መሠረተ ልማቷን ለማስፋፋት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ብትመድብም የአገሪቱ መንገዶች ለእግረኞች እና ለአሽከርካሪዎች አደገኛ በመሆን በዓለም ከሚጠቀሱት መካከል ሆነዋል።

በዚህም ምክንያት የትራፊክ አደጋ ከአገሪቱ ከአገሪቱ ዓመታዊ አጠቃላይ ምርት (ጂዲፒ) ላይ 3 በመቶ የሚሆነውን ለውድመት ይዳርጋል።

ይህም ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ሕንድ በመንገድ አቅርቦት ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛ ከፍተኛው የመንገድ መሠረተ ልማት ያላት ስትሆን፣ በአገሪቱ ውስጥ 350 ሚሊዮን የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ።

የሕንድ ትራንስፖርት ጥናት እና የአደጋ መከላከል ማዕከል የአገሪቱን መንገዶች ሁኔታን በተመለከተ ለዓመታት ባደረገው ጥናት በሕንድ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ አሳሳቢ የሆኑ እንከኖች እንዳሉ አመልክቷል።

የሕንድ የመንገድ ዲዛይን ደረጃዎች በወረቀት ላይ እጅግ ጥብቅ ሲሆኑ ችግር የሚከሰተው መሬት ላይ ተግባራዊ ሲደረጉ መሆኑ ይነገራል።

በመካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት የመንገድ ደኅንነት ዙሪያ የሰሩት በአሜሪካ ችካጎ ዩኒቨርስቲ የመንገድ መሠረተ ልማት ባለሙያ የሆኑት ካቪ ብሃላ እንደሚሉት የሕንድ መንገዶች ዲዛይን የአገሪቱን ልዩ የትራፊክ እና የመሠረተ ልማት ፍልጎትን ችላ በማለት የምዕራባውያን ግልባጭ ናቸው ሲሉ ይተቻሉ።

"ሕንድ እየሞከረች ያለችው የአሜሪካንን የመሰሉ የአውራ ጎዳናዎች ሠረተ ልማትን መገንባት ሲሆን፣ ነገር ግን የአሜሪካ አይነት የአውራ ጎዳና ደኅንነት ምህንድስና እና የአደጋ መረጃ አያያዝ ሥርዓት ግን የላትም" ብለዋል ብሃላ።

ሕንድ እየገጠማት ያለውን የትራፊክ አደጋ ጉዳት ለመከላከል መንግሥት በመንገዶች ዲዛይን፣ በተሽከርካሪዎች፣ በመንገድ ደኅንነት ትምህርት፣ ደንቦችን በማስፈጸም እና በአደጋ ጊዜ የሚሰጥ ድጋፍ ላይ ትኩተረት አድርጎ እየሠራ ነው።