እስራኤል “ትክክለኛው ሰዓት ላይ” ለኢራን ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እሰጣለሁ አለች

የእስራኤል ጦር ካቢኔ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Defense, Israel

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጦር ካቢኔ

እስራኤል ልክ እንደ ኢራን ሁሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎችን በመተኮስ ‘ትክክለኛው ሰዓት ላይ’ የበቀል እርምጃ እውስዳለሁ አለች።

ዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ውጥረት ከሚያባብስ እርምጃ እንዲቆጠቡ አገራት ቢያሳስቡም እስራኤል ግን ትክክል ሆኖ ሳገኘው የአጸፋ እርምጃ እውስዳለሁ ብላለች።

ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤል ላይ በፈጸመችው ቀጥተኛ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከ300 በላይ ሚሳኤል እና ድሮኖች ወደ እስራኤል ማስወንጨፏ ይታወሳል።

ከ300 በላይ የሚሆኑት ሚሳኤሎች እና ድሮኖች ከኢራን፣ ኢራቅ እና ከየመን ወደ እስራኤል የተተኮሱ ቢሆንም አብዛኞቹ ጉዳት ሳያደርሱ በእስራኤል፣ በአሜሪካ እና በወዳጆቿ አማካይነት እንዲከሽፉ ተደርገዋል።

ከኢራን የተወነጨፉ ሚሳኤሎችን በማምከን ድጋፍ ስታደርግ የነበረችው አሜሪካ እስራኤል የበቀል እርምጃ ብትወስድ ተሳታፊ አልሆንም ስትል አስታውቃለች።

አምስት አባላት ያሉት የእስራኤል የጦር ካቢኔ እና የአገሪቱ ፓርላማ አባል ቤኒ ጋንትዝ ትክክለኛው ሰዓት ላይ ኢራን ለፈጸመችው ተግባር እስራኤል ዋጋ ታስከፍላታለች ብለዋል።

ኢራን ከቀናት በፊት በሶሪያ ዋና ከተማ በሚገኘው ቆንስላ ጽህፈት ቤቷ ላይ በተፈጸመው ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ስትዝት ቆይታለች።

የእስራኤል ጦር እና አሜሪካ ኢራን ካስወነጨፈቻቸው ከ300 በላይ ድሮኖች እና ባሊስቲክ ሚሳኤሎች 99 በመቶ የሚሆኑት ዒላማቸውን ከመምታታቸው በፊት መትተው ጥለዋል።

ከአሜሪካ በተጨማሪ ይህን የኢራን ጥቃትን በመከላከል ለእስራኤል ድጋፋቸውን ከሰጡ አገራት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም እና ጆርዳን ይገኙበታል።

እስራኤል የተቃጣባትን ጥቃት አስተማማኝ በሆነ መልኩ መመከቷ በኢራን ላይ ድል እንደተጎናጸፈች ተደርጎ ይቆጠራል ሲሉ አንድ ስማቸው ያልተገጸ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል።

የኢራን ጥቃት ለአሰርት ዓመታት እንደ ጠላት ሲተያዩ በቆዩት አገራት መካከል የለየለት ጦርነት ይቀሰቅሳል የሚል ስጋት አለ። የኢራን እና እስራኤል ግጭት መረጋጋት የራቀውን የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ሰላም እንዲርቀው ያደርጋል የሚሉም በርካቶች ናቸው።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ትናንት እሁድ ሚያዚያ 6/2016 ዓ.ም. የእስራኤል ምላሽ ምን መሆን አለበት በሚል አምስት አባላት ያሉት የጦር ካቢኔ ተሰብስቦ እንደነበር ዘግቧል።

ይሁን እንጂ ኮሚቴው እስራኤል መስጠት ስላላበት የአጸፋ ምላሽ ስፋት እና ጊዜ መስማማት ሳይችል ተበትኗል ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል የአጸፋ ምላሽ ከማድረግ እንድትቆጠብ ኢራን አሳስባለች።

የኢራን ጦር ጠቅላይ አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሞሐመድ ባግሄሪ እስራኤል የአጸፋ ምላሽ ብትሰጥ ኢራን እሁድ ንጋት ላይ ከወሰደችው ጥቃት እጅግ የሰፋ ጥቃት ይጠብቃታል ሲሉ አሳስበዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረቱ እንዳለ ቢሆንም በእስራኤል ሕይወት ወደ ቀደመ ሁኔታ እየተመለሰ ይገኛል። ከእሁድ ረፋድ ጀምሮ ተዘግተው የነበሩ አየር ማረፊያዎች ስራ የጀመሩ ሲሆን የእስራኤል የአየር ክልልም ተከፍቷል።