በጣልያን ተራራ በሺዎች የሚቆጠሩ የዳያኖሰር የእግር ዱካዎች ተገኙ

ዳያኖሰሮች በቡድን ሆነው ሲራመዱ የሚያሳይ ሥዕል

የፎቶው ባለመብት, Illustrazione di Fabio Manucci, Arch. PaleoStelvio

በሰሜን ጣልያን በሚገኝ ብሔራዊ ፓርክ ከ210 ሚሊዮን ዓመታት በፊት የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የዳያኖሰር የእግር ዱካዎች ተገኙ።

የእግር ዱካዎቹ የአንዳንዶቹ 40 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያላቸው ሲሆን ፊት ለፊት በተርታ ሆነው ታይተዋል። አብዛኞቹ የእግር ዱካዎችም በግልጽ የጣታቸውን እና የጥፍራቸውን ቅርጽ ያሳያሉ።

ዳያኖሰሮቹ ረዥም አንገት፣ ትንሽ ጭንቅላት እና የሾሉ ጥፍሮች ያላቸው ከጁሪያሲክ ዘመን ቀደም ብለው የነበሩት ሳር በል ዝርያዎች እንደሆኑ ይታሰባል።

በሚላን ተቀማጭነታቸውን ያደረጉት እና ስለ እንስሳት እና እፅዋት ቅሪተ አካል የሚያጠኑት ክርስቲያኖ ዳል ሳሶ " በምኖርበት አካባቢ እንዲህ ዓይነት አስደናቂ ግኝት አገኛለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም" ብለዋል።

ባለፈው መስከረም ወር አንድ ፎቶ አንሺ በሰሜን ምሥራቅ ሚላን በሚገኘው ስትልቪዮ ብሔራዊ ፓርክ ተራራ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሜትሮች የሸፈኑ ዱካዎችን በፎቶዎቹ አሳይቶ ነበር።

ተራራው በ250 እና በ201 ሚሊዮን ዓመታት መካከል ባለው ትሪያሲክ ዘመን ሜዳማ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ የአልፕስ ተራራዎች ሰንሰለት አካል ሆኗል።

ዳል ሳሶ "ይህ ቦታ በዳያኖሰሮች የተሞላ ነበር።ይህ በጣም ብዙ ሳይንሳዊ ሃብት ነው" ብለዋል።

ጨምረውም ዳያኖሰሮቹ በመንጋ ይጓዙ እንደነበር ጠቅሰው፣ ልክ ራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ በቡድን እንደሚሰባሰቡ እንስሳት ዓይነት ባሕርይ እንዳላቸውም ዱካዎቹ እንዳመለከቱ ገልጸዋል።

አስር ሜትር የሚደርስ ርዝመት ሊኖራቸው የሚችል ከጁራሲክ ዘመን ቀደም ብሎ የነበሩ እነዚህ ዳያኖሰሮች በሁለት እግራቸው ሲራመዱ የነበረ ሲሆን በአንዳንድ ሁኔታዎች ከእግር ዱካቸው ፊት ለፊት የእጅ መዳፋቸው ምልክትም ተገኝቷል። ይህም ጉዟቸውን ገትተው መሬት ላይ ማረፋቸውን ያሳያል።

ተራራዎች ላይ የሚታይ የዳያኖሰሮች የእግር ዱካዎች

የፎቶው ባለመብት, Elio Della Ferrera, Arch. PaleoStelvio

አካባቢውን ያገኘው ፎቶ አንሽ ኢሊዮ ዲላ ፍሬራ፣ "ግኝቱ ስለ ምንኖርበት አካባቢ፣ አገራችን እና ዓለማችን የምናውቀው ጥቂት መሆኑን እንደሚያሳይ ነው" ሲል ለውይይት እና ምርምሮች መነሻ እንደሚሆን ተስፋ አድርጓል።

የጣልያን ባህል ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ አካባቢው ወጣ ያለ በመሆኑ ወደ ሥፍራው ለመሄድ የሚያስችል መንገድ ባለመኖሩ በሥፍራው ድሮኖች እና ከርቀት ሆነው መረጃዎችን የሚሰበስቡ ቴክኖሎጂዎች እንደሚሰማሩ ገልጿል።

ስትልቪዮ ብሔራዊ ፓርክ ጣልያን እና ስዊዘርላንድ በሚዋሰኑበት ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ፍራኤላ ሸለቆ ውስጥ ሲሆን በመጭው አውሮፓውያኑ ዓመት የክረምት ኦሊምፒክ የሚካሄድበት አካባቢ ነው።

" ታሪክ ራሱ ለታላቁ ዓለም አቀፍ የስፖርት ዝግጅት ክብር ለመስጠት የፈለገ ያህል ነው። ያለፈውን እና የአሁኑን በማጣመር በተፈጥሮ እና በስፖርት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሳይ ነው" ሲል የባህል ሚኒስቴሩ የክስተቱን ግጥምጥሞሽ ገልጾታል።