በሶማሊያ ችግር የገጠመውን አውሮፕላን በባሕር ዳርቻ በማሳረፍ ሕይወት ያተረፈው አብራሪ ተወደሰ

አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Aussom

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሶማሊያ የሚገኘው አየር መንገድ የቴክኒክ ችግር የገጠመውን የመንገደኞች አውሮፕላን በሞቃዲሹ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አጠገብ በሚገኝ የባሕር ዳርቻ ላይ በማሳረፍ ሕይወት ያተረፈውን አብራሪ አወደሰ።

አብራሪው ይህንን እርምጃ በመውሰዱ በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩ 55 ሰዎች በሕይወት መትረፍ ችለዋል።

ስታርስካይ አቪየሽን እንዳለው አብራሪው በፍጥነት በማሰብ እርምጃውን መውሰዱ ለ50 መንገደኞች እና አምስት የበረራ ቡድን አባላት መትረፍ ወሳኝ ነበር።

ፎከር 50 የተባለው አውሮፕላን አውሮፕላኑ ማክሰኞ ዕለት ጠዋት ከሞቃዲሹ የተነሳው እዚያው አገር ውስጥ ወደሚገኘው ሙዱግ ክልል መዲና ጋልካዮ ለመብረር ነበር።

ሆኖም የበረራ ቡድኑ አባላት አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ ወዲያውኑ ችግር እንደገጠመው ሪፖርት ማድረጋቸውን እና እንዲመለስ መጠየቃቸውን የሶማሊያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ገልጿል።

ከዚያ ግን መሬት ላይ ለማረፍ ቢሞክርም በማኮብኮቢያው ላይ መቆም ባለመቻሉ ማኮብኮቢያውን ስቶ ብዙም ጥልቀት በሌለው የውሃ ክፍል ሊያርፍ መቻሉን የአቪየሽኑ ዳይሬክተር አህመድ ማካሊን ሃሰን ተናግረዋል።

አውሮፕላኑ ያጋጠመው ችግር በትክክል ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።

በኤክስ ላይ የተጋራ ምስል መንገደኞች ከአውሮፕላኑ ሲወጡ እና በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ከወደቀው አውሮፕላን ስብርባሪ ውስጥ ወጥተው ሲሄዱ አሳይቷል። እስካሁን የደረሰ ከባድ ጉዳት እንደሌለም ተገልጿል።

በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና አውሮፓ ኅብረት ወታደሮች የነፍስ አድን ጥረቶችን ለማገዝ በፍጥነት በአካባቢው መሰማራታቸውን ገልጿል። የሶማሊያ የትራንስፖርት ሚኒስትርም አደጋው ባጋጠመበት ቦታ እንደነበሩ በኤክስ ገጹ ባጋራው ጽሑፍ ጨምሮ ገልጿል።

" ሁሉም መንገደኞች እና የበረራ ቡድን አባላት ደኅና መሆናቸውን ስናረጋገጥ እፎይታ ይሰማናል። አውሮፕላኑ በድንገት ለማረፍ ያስገደደው የቴክኒክ ችግርን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ ነው" ብለዋል የስታርስካይ ቃል አቀባይ ሃሰን መሐመድ አደን።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም " የአብራሪው ፈጣን እና የተረጋጋ ውሳኔ ለሁሉም ተሳፋሪዎች ደኅንነት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ። በመሆኑም አብራሪው ሁኔታውን በተቆጣጠረበትን መንገድ በይፋ እናወድሰዋለን" ብለዋል።