ዓለምን ጉድ ያሰኘው ውዝግብ - ዜሌንስኪን፣ ትራምፕን እና አውሮፓን ወዴት ይመራቸዋል?

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በዋሽንግተን ከዶናልድ ትራምፕ እና ከምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ጋር የነበራቸውን ኃይለ ቃል የተሞላበት ምልልስን ተከትሎ ከዋይት ሐውስ እንዲወጡ ትዕዛዝ ከተሰጣቸው ከሦስት ቀናት በኋላ ወደ ኪየቭ ተመልሰዋል።

ዜሌንስኪ በሳምንቱ መጨረሻ በለንደን ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር በጽህፈት ቤታቸው ዳውኒንግ ስትሪት ከተቀበሏቸው በኋላ ከንጉሥ ቻርለስ ሦስተኛ ጋር ተገናኝተዋል።

በዶናልድ ትራምፕ ጽህፈት ቤት (ኦቫል ኦፊስ) ውስጥ ከነበረው እሰጣገባ በተቃራኒ እሁድ ዕለት በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከአውሮፓ መሪዎች ጠንካራ ድጋፍን አግኝተዋል።

ከለንደኑ ጉባኤ በኋላ ሰር ኪር ስታርመር የአውሮፓ መሪዎች ለዩክሬን የሰላም ዋስትና ለመስጠት "የፍቃደኞች ጥምረት" እንዲመሠርቱ ሐሳብ አቅርበዋል፤ ነገር ግን ማን ምን ዓይነት አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ የሚገልጽ ዝርዝር የለም።

ዜሌንስኪ ከትራምፕ ጋር ስላላቸው ግንኙነት እና አውሮፓ ለዩክሬን የፀጥታ ዋስትና ለመስጠት ስለያዘው ዕቅድ እስካሁን ምን እናውቃለን?

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቁጭ ብለው

የፎቶው ባለመብት, EPA

የትራምፕ እና ዜሌንስኪ ግንኙነት ምን ላይ ነው?

ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ቅዳሜ ማለዳ ላይ በተከታታይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሯቸው መልዕክቶች ዩክሬን እና አሜሪካ የጋራ ግባቸውን ለመረዳት "ቅን እና ቀጥተኛ መሆን" አለባቸው ብለዋል።

በተጨማሪም አሜሪካ ከጎናቸው "እንድትቆም" እንሚፈልጉም አመለክተዋል።

ከዋይት ሐውስ ከወጡ ከሰዓታት በኋላ ዜሌንስኪ በፎክስ ኒውስ ላይ ቀርበው ውይይቱ "በጣም ከባድ" መሆኑን ተናግረው አሜሪካውያንን እና ዶናልድ ትራምፕን አመስግነዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ሕግ አውጪዎች ዜሌንስኪ ይቅርታ እንዲጠይቁ ጥሪ ቢያቀርቡም በቀጥታ ይህንኑ ሳይፈጽሙ ቀርተዋል።

ትራምፕ በሳምንቱ መጨረሻ በተደረገው የኃይለ ቃል ልውውጥ ላይ በቀጥታ አስተያየት ባይሰጡም፣ አብዛኞቹ የሪፐብሊካን ተወካዮች ለትራምፕ እና ለቫንስ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

በአርብ ዕለቱ ውጥረት የበዛበት ስብሰባ ወቅት በኦቫል ኦፊስ ውስጥ የነበሩት የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክ ዋልትስ የዩክሬኑን መሪን ከ"የቀድሞ የሴት ጓደኛ" ጋር ሲያነጻጽሯቸው፤ አፈ-ጉባዔ ማይክ ጆንሰን ደግሞ ዜሌንስኪ ሥልጣናቸውን እንዲለቅቁ ጠይቀዋል።

ይኹን እንጂ ለዘብተኛው ሪፐብሊካኑ ኮንግረስማን ዶን ባከን "ለአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ መጥፎ ቀን ነው" ሲሉ፣ የአላስካ ሴናተር ሊዛ ሙርኮቭስኪ በበኩላቸው "አስተዳደሩ ከአጋሮቻችን እየራቀ ፑቲንን ሲያቅፍ ማየት ያምማል" ብለዋል።

የአውሮፓ መሪዎች ምን ምላሽ ሰጡ?

አርብ አመሻሽ ላይ ዜሌንስኪ ከዋይት ሐውስ ከወጡ በኋላ የተለያዩ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ ጎርፈዋል።

መልዕክታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ካጋሩ የተለያዩ አገራት መሪዎች መካከል ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ያላቸውን ጥሩ ግንኙነት ለማስቀጠል የሚፈልጉት የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እና ዶናልድ ትራምፕን "ለሰላም በጀግንነት በመቆማቸው" ያወደሱት የሃንጋሪው ቪክቶር ኦርባ ይገኙበታል።

እሁድ የተካሄደው የለንደኑ ስብሰባ ላይ ከቃላት ድጋፉ ባሻገር ተጨባጭ እርምጃ መኖር አለበት የሚል ስሜት ተንጸባርቋል።

አብዛኞቹ መሪዎች አሁንም የአሜሪካን ድጋፍ አስፈላጊ እንደሆነ በአጽንኦት ያስገነዝባሉ።

በጉባዔው መገባደጃ ላይ ስታርመር ለዩክሬን የሚሰጠው ወታደራዊ ዕርዳታ እንዲቀጥል፣ ዩክሬን በሰላም ድርድር ላይ ለመገኘት ቁርጠኛ እንድትሆን፣ የዩክሬን የመከላከያ አቅምን በማጎልበት የወደፊት የሩሲያ ጥቃትን ለመከላከል እና ዩክሬንን ለመከላከል "የፈቃደኞች ጥምረት" ማጠናከርን የያዘ ባለ አራት ነጥብ የሰላም ዕቅድ አውጥተዋል።

የአውሮፓ የደኅንነት ዋስትናዎች?

የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ወታደሮችን ወደ ዩክሬን የመላክ ሃሳብ የበርካታ ወገኖች ድጋፍ ነበረው ቢሉም፤ ጉዳዩን አገራት በየግላቸው እንዲወያዩበት ትተውታል።

የስካንዲኔቪያ አገሮች ሃሳቡን እንደሚቀበሉት አስቀድመው ፍንጭ ሰጥተዋል።

የዴንማርክ ጠቅላይ ሚንስትር፣ ሜቴ ፍሬደሪክሰን አገራቸው የቀረበውን ሃሳብ "በቅን ልቦና" እየተከታተለች ነው ሲሉ፣ የስዊድኑ ኡልፍ ክሪስተርሰን በበኩላቸው አገራቸው የአሜሪካን ድጋፍ ካገኘች ለዩክሬን የደኅንነት ዋስትና ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ምናልባት "ግራ የሚያጋባ" ስላሉት እና በዩክሬን ስላለው የአውሮፓ ድጋፍ ከመወያየት ይልቅ፣ አሜሪካን የሚያካትት ሌላ ስብሰባ እንዲደረግ መገፋፋትን መርጠዋል።

ለረጅም ጊዜ የኪየቭ ከፍተኛ ደጋፊ የነበረችው ፖላንድ ምንም እንኳን ለዩክሬን በሰብዓዊ እና ወታደራዊ እርዳታ ላይ ጥቂት ገደቦችን ብታስቀምጥም ወታደሮቿን ላለመላክ ከወዲሁ ወስናለች።

የአውሮፓ መሪዎች ሐሙስ ብራስልስ ውስጥ ለሚደረገው ልዩ የመከላከያ ስብሰባ ከመገናኘታቸው በፊት አዳዲስ ለውጦችን ለማብላላት ጥቂት ቀናት ይኖራቸዋል።

በዚህም የኮሚሽኑ ኃላፊ ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን "አውሮፓን እንዴት ማስታጠቅ እንደሚቻል አጠቃላይ ዕቅድ" በማለት የገለፁትን ያቀርባሉ።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር እና የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ተቃውሞ የገጠመው የተኩስ አቁም ዕቅድ

እሁድ ምሽት የፈረንሳይ ጋዜጣ 'ለ ፊጋሮ' እንደዘገበው፣ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ስታርመር በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል "በአየር እና በባሕር" ለአንድ ወር የሚቆይ የእርቅ ስምምነት ሃሳብ ማቅረባቸውን ዘግቧል።

በመላምቱ መሠረት ሁለቱም ወገኖች በአየር፣ በባሕር እና በኃይል መሠረተ ልማት ዙሪያ ለአራት ሳምንታት የተኩስ አቁም ለማድረግ ይስማማሉ።

ነገር ግን ማክሮን ለመከታተል በጣም ከባድ ስለሆነ በጦር ግንባር ላይ የሚደረገውን ውጊያ እንደማይሸፍን ጠቁመዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰኞ ማለዳ ላይ የዩኬ የጦር ኃይሎች ሚኒስትር "የተኩስ ማቆም ምን እንደሚመስል ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ አልተደረሰም" በማለት የእርቁን ሃሳብ አጣጥለውታል።

ሉክ ፖላርድ ለታይምስ ሬድዮ "ከፈረንሳይ እና ከአውሮፓ አጋሮቻችን ጋር በመተባበር ሂደቱ ምን እንደሆነ ለማየት. . . በዩክሬን ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ለመፍጠር እየሠራን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ማንኛውም እርቅ በሩሲያ ተቀባይነት ማግኘት ያለበት ቢሆንም፣ ያንን ለማድረግ ሩሲያ ፈቃደኛ ስለመሆኗ እስካሁን ምንም ማስረጃ የለም።

የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ

ሩሲያ ምን አለች?

ምንም እንኳን ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዋሽንግተን ውስጥ ከአሜሪካ መሪዎች ስለገጠማቸው ውዝግብ እስካሁን በይፋ አስተያየት አልሰጡም።

ነገር ግን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ዜሌንስኪ አሜሪካ ውስይ የገጠማቸው "የዩክሬን ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ውድቀት" ነበር ብለዋል።

ሰኞ ጠዋት ፕሬዝዳንት ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው በዩክሬን ጉዳይ ላይ በተደረገው የለንደን ስብሰባ ላይ ያላቸውን ትችት ጨምረዋል።

ፔስኮቭ "ለዩክሬን የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ በአስቸኳይ ማጠናከር አስፈላጊ ስለመሆኑ መግለጫዎች ተሰጥተዋል። ይህ በግልጽ የሰላም ዕቅድ አካል አይደለም፤ ጦርነቱን ለመቀጠል የተደረገ ነው" ብለዋል።

ቃል አቀባዩ "ቀሪው የሚወሰነው ምን ዓይነት የሰላም ዕቅዶች ናቸው ተዘጋጅተው የሚቀርቡት የሚለው ላይ ነው። ለዚህ ሂደት ማንኛውም ገንቢ ድጋፍ ተቀባይነት አላቸው" ሲሉ አክለዋል።