በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች ለቀድሞ የኮንጎ መሪ ጆሴፍ ካቢላ ጓደኞችና ቤተሰቦች መተላለፉ ተጋለጠ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በቀድሞው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ ቤተሰቦች እና ወዳጆች ንብረት የሆኑ ኩባንያዎች የህዝብ ገንዘብ የሆነ
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች በባንክ ሂሳባቸው እንዲገባ መደረጉን በአፍሪካ ትልቅ የተባለ አፈትልኮ የወጣ መረጃ አመልክቷል።
ይህ ገንዘብ ቢጂአይኤፍ በተባለ ባንክ አማካኝነት ወደ ኩባንያዎቹ ሂሳብ መተላለፉን መረጃው ጨምሮ ጠቁሟል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችም በጥሬ ገንዘብ ከአካውንቶቹ ወጥተዋል።
ይህ ዝውውር በሚደረግበት ወቅት ጆሴፍ ካቢላ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ሲሆን ዝውውሮቹንም አስመልክቶ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
አፈትልኮ የወጣው መረጃ በበርካታ የአፍሪካ ሃገራት እና በፈረንሳይ ከሚሰራው በምሕጻረ ቃል ቢጂአይኤፍ (ባንኬ ጋቦናይዜ ኤት ፍራንሴይዝ ኢንተርናሽናል" ባንክ የተገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግብይቶችን የሚያሳዩ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ሰነዶች እና መረጃዎችን አካቷል።
መረጃው የተገኘው ሚዲያፓርት በተባለ የፈረንሳይ የምርመራ ድረገፅ እና ፒፒኤልኤኤፍ በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅቶች ናቸው።
ምርመራዎች ላይ የሚያተኩረው ቢቢሲ አፍሪካ ማስረጃውን ያገኘው ኮንጎ ሆልድ አፕ በተባለው የሚዲያ አውታር የአውሮፓ የምርመራ ትብብር (ኢአይሲ) አስተባባሪነት ነው።
ምርመራው ከገንዘብ ዝውውሩ ማን ተጠቀመ እንዲሁም የጥቅም ግጭቶችስ ነበሩበት ወይ የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሳል።
የተጋነነ ገንዘብ ዝውውር
የቢጄኤፍ ኩባንያ የኮንጎ ቅርንጫፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፍራንሲስ ሰለማኒ ይባላሉ።
ይህ ድርጅት የቢጂኤፍአይ ባንክ እህት ኩባንያ ነው። ፍራንሲስ ሰለማኒ ናቸው የሚመሩት። ሰለማኒ ደግሞ የቀድሞ የኮንጎ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ የማደጎ ወንድም ናቸው።
የጆሴፍ ካቢላ እህት ገሎሪያ ሚቴዩ ይባላሉ። የዚህን ባንክ የኮንጎ ቅርንጫፍ 40 ከመቶ ድርሻ የያዙት እሳቸው ነበሩ።
አንድ 'ሱድ ነዳጅ' የሚባል ኩባንያ ከዚህ ባንክ 86 ሚሊዮን ዶላር እንደተከፈለው ሰነዱ ያትታል። ይህ ገንዘብ ለሱድ ነዳጅ የከፈሉት የተለያዩ ድርጅቶች እንደሆኑ የተገለጠ ሲሆን አንዱ የኮንጎ ምርጫ ቦርድ ሆኖ ቀርቧል።
ይህም ገንዘብ ከቢጂአይኤኤፍ ዲአር ኮንጎ ተቆጣጣሪ፣ ቢሲሲ፣ ቢያንስ 46 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ጌካሚንስ ተብሎ ከሚጠራው የአገሪቱ ማዕድን ኩባንያ 15 ሚሊዮን ዶላርና 1.3 ሚሊዮን ዶላር ከአገሪቱ የምርጫ ድርጅት የተገኘ ነው።
እነዚህን ክፍያዎች በተመለከተ ቢቢሲ አፈትልኮ በወጣው ያገኘው ብቸው መረጃ ከሴኒ ለ ለሱድ ኦይልና ፔትሮሊየም ምርቶች የተከፈለ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ደረሰኝ ብቻ ነው።
ቢቢሲ በወቅቱ ሱድ ኦይል በፔትሮሊየም ምርቶች ይገበያይ እንደነበር ምንም አይነት ማስረጃ አላገኘም።
የጆሴፍ ካቢላ የማደጎ ወንድም የሆኑት የፍራንሲስ ሰለማኒ እህት አኔት ሉታሌ የዚህ ሐሳዊ የነዳጅ ኩባንያ (ሱድ ነዳጅ) 80 ከመቶ ድርሻ እንዳላቸው ታውቋል፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን ከዚህ የነዳጅ ኩባንያው የባንክ ሒሳብ በሚሊዮን ዶላሮች ወደ ካቢላ ቤተሰብና የቅርብ ጓደኞች የባንክ ሒሳብ ዝውውር ተደርጓል።
ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ ይህ ‹ሱድ ኦይል› የተባለው ድርጅት ያለው የሠራተኛ ብዛት አንድ ብቻ መሆኑ አስገራሚ ሆኗል። ይህም ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ዳቪድ ኢዝቃኤል ነው። ይህ ከፍተኛ የባንክ ዝውውር የሚደረግበት ሐሳዊ ኩባንያው በኪንሻሳ አንዲት ትንሽ ቢሮ አለችው።
በ2013 ደግሞ ሱድ ነዳጅ በ12 ሚሊዮን ዶላር ሪልስቴት መግዛቱ ተደርሶበታል።
ለከፍተኛ የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ቅንጡ መኪና ያስፈልጋቸዋል በሚልም በአንድ ወቅት ከቢጂኤፍአይ ባንክ 70ሺህ ዶላር ተቀብሏል።
ከዚህ ውጭ ኩባንያው ምንም አይነት የቢዝነስ ሥራ የሰራበትን ሰነድ አለማግኘቱን ‹‹ቢቢሲ አፍሪካ አይ›› የጋዜጠኞች ምርመራ ቡድን አረጋግጧል።
ቢቢሲ በዚህ ማጭበርበር እና የኩባንያ ባለቤትነት ላይ ስማቸው የተጠቀሱ ኩባንያዎችን፣ ግለሰቦችን፣ ሥራ አስፈጻሚዎችን በሾለከው ሰነድ ዙርያ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቆ አንዳቸውም ፈቃደኛ አልሆኑም።












