የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል መውሰድ የሚችሏቸው 10 እርምጃዎች

የአየር ንብረት ለውጥ መላው ዓለምን ከሚያሳስቡ ሁነቶች አንዱ ነው። የአገራት መሪዎች በተለያየ ጉባኤ ይመክሩበታል። የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾችም ግንዛቤ ለመፍጠር ይጥራሉ።
አገራት እንዲሁም ተቋሞች ካለባቸው ኃላፊነት ጎን ለጎን ግለሰቦችም የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ።
እርስዎም ቀጣዮቹን አስር እርምጃዎች ቢወስዱ ዓለምን ከአየር ንብረት ለውጥ ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት ያግዛሉ።
1.ተረፈ ምርትን በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል
የተረፈ ምርቶች መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። እንዲያውም በቀጣይ 20 ዓመታት የተረፈ ምርት መጠን 2 ቢሊዮን ቶን ይሆናል ተብሎ ይገመታል።
ስለዚህም ተረፈ ምርቶችን በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል አንዱ አማራጭ ነው።
2. የውሀ አካልን መጠበቅ
በተለያዩ የምድር ክፍሎች የውሀ አካላት እየደረቁ መጥተዋል። ውሀ ውስጥ የሚኖሩ እንስሳት ላይ ጉዳት እየደረሰም ይገኛል።
ይህም እጅግ አስጊ ነው። ስለዚህም ማንኛውም አይነት የውሀ አካል ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል።
ከውሀ አካል ባሻገር የምድራችን የደን ሀብትም እየተመናመነ መጥቷል። እአአ ከ1960ዎቹ ወዲህ ግማሽ ያህሉ የዓለም የደን ሀብት ወድሟል። ብዝሀ ሕይወትም እየተቃወሰ ነው።
ደን የካርቦን ልቀትን በማመቅ ምድር ከመጠን በላይ እንዳትሞቅ ያደርጋል። ስለዚህም ዛፍ መትከል እንዲሁም ደን አለመጨፍጨፍ የእያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት ነው።

3. 'ሰልባጅ' መግዛት
ልብስ ለመሥራት የሚውለውን ተፈጥሯዊ ግብአት ለመቆጠብ ሲባል የሚወሰዱ እርምጃዎችን ደግሞ እንመልከት።
አንደኛው አማራጭ ልብስ ጥቅም ላይ የሚውልበትን እድሜ ማርዘም ነው። አንድ ሰው አልባሳቱን ለተወሰነ ጊዜ ከተጠቀመ በኋላ ለተራድኦ ድርጅቶች መስጠት ይችላል።
በዚህ መንገድ ሚሊዮን ቶን የሚመዝኑ ጥቅም አልባ ተብለው የተጣሉ ልብሶችን ማዳንና አካባቢን መጠበቅ ይቻላል።
ከዚህ በተጨማሪ ጥቅም ላይ የዋሉ ወይም ሰልባጅ ልብሶችን መግዛት ሌላው መፍትሔ ነው።
4. የሕንጻ ካርበን ልቀትን መግታት
40 በመቶ የሚሆነው የምድር የካርቦን ልቀት የሚመነጨው ከግንባታ፣ ጥገና እና ሕንጻዎች ነው።
በተለይም ቢሮ የሚበዛባቸው ሕንጻዎች ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ።
ይህንን ችግር መቅረፍ ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ ጥብቅ ሕግ ማውጣትና ሕጉን የሚተላለፉን መቅጣት ነው።
5. ከመደብር ስለሚገዙት ቁሳቁስ ማወቅ
ብዙ መደብሮች ስለሚሸጧቸው ቁሳቁሶች ግልጽ መረጃ አይሰጡም።
ከቁሳቁሶች በተጨማሪ የምንገዛው ምግብ የትና በምን ሁኔታ እንደተመረተ ሊገለጽልን ይገባል።
አንድ ምርት ሲዘጋጅና ሲጓጓዝ ምን ያህል ካርቦን እንደተለቀቀ በግልጽ ቢቀመጥ፤ ሁላችንም በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ ላይ መድረስ እንችላለን።
6. ሴቶችን ትምህርት ቤት መላክ
በየትኛውም የዓለም ጥግ ሴቶች መማር አለባቸው።
የዓለም እኩሌታውን የያዙት ሴቶች እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ድረስ እንዲማሩ ምቹ ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል።
ማኅበረሰቡ በተማረ ቁጥር ለአካባቢ ጥበቃ የሚሰጠው ትኩረት ያድጋል።
7. ምግብ አለማባከን
ምግብ አስተርፎ መጣል የካርበን ልቀትን ከሚጨምሩ መካከል ይጠቀሳል።
ዌስት ኤንድ ሪሶርስስ አክሽትን ፕሮግራም የተባለው የእርዳታ ድርጅት እንደሚለው በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ 6.6 ሚሊዮን ቶን ምግብ ይጣላል።
ምግብ ተርፎ እንዳይጣል፤ ምን ምግብ መግዛት እንደሚፈልጉ፣ ምን ያህል እንደሚመገቡ አስቀድሞ ማወቅ ይገባል።

8. ማኅበራዊ ሀይል ማመንጨት
በእንግሊዘኛ ኮምዩኒቲ ኢነርጂ ይባላል። አንድ ማኅበረሰብ ተሰባስቦ ኃይል የሚያመነጭበት መንገድ ነው።
የጋራ ሀይል ማመንጨት ከሚሠራበት አንዱ የኤሌክትሪክ ሀይል ዘርፍ ነው።
ለምሳሌ ዴንማርክ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት የንፋስ ሀይል ማመንጫዎች የማኅበረሰቡ የጋራ ንብረት ናቸው።
9. አትክልት ነክ ምግብ ማዘውተር
አትክልት ነክ ምግብ ማዘውተር ምድርን ከአየር ንብረት ለውጥ ከሚታደጉ መፍትሔዎች አንዱ ነው።
አትክልት፣ ፍራፍሬና ጥራጥሬ ማዘውተርና ስጋ መቀነስ ለግል ጤና ከመጥቀሙ ባሻገር አካባቢንም ከጉዳት ያድናል።
10. የካርቦን መጠንን መቀነስ
በዚህ ትውልድ የሚከወኑ ነገሮች መጪው ትውልድ ላይ ጫና ማሳደራቸው አይቀርም።
ታዲያ መጪውን ትውልድ ለመታደግ የካርቦን ልቀትን መቆጣጠር የግድ ነው።
ስለዚህም የካርቦን ልቀታቸው አነስተኛ የሆኑ ምርቶችን መሸመት በማዘውተር የድርሻዎን መወጣት ይችላሉ።












