ኃይማኖት፡ አንጎላ 'ሙሰኛ' ያለቻቸውን የብራዚል ቤተ-እምነቶች በቁጥጥር ሥር አዋለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአንጎላ አቃቤ ሕግ ሙሰኛ ናቸው ያላቸውን ግዙፍ የብራዚል ኢቫንጀሊካል አብያተ ክርስትያናት እንዲዘጉ አዘዘ።
ቤተ-እምነቶቹ እንዲዘጉ የታዘዘው ሙስና ተጠናውቷቸዋል በሚል ነው።
ዋና ከተማዋ ሉዋንዳ የሚገኙ 'ዩኒቨርሳል ቸርች ኦፍ ዘ ኪንግደም ኦፍ ጋድ' የተሰኘው ቤተ-እምነት ንብረት የሆኑ ቢያንስ ሰባት አብያተ ክርስትያናት በመንግሥት እጅ እንዲገቡ ሆነዋል።
ከሳሾቹ የኢቫንጀሊካል ቤተ-ክርስትያን በግብር ማጭበርበርና በሌሎች ገንዘብ ነክ ወንጀሎች ላይ እጇ አለ ሲሉ ይወነጅላሉ።
ዩኒቨርሳል ቸርች ኦፍ ኪንግደም ከሳሾች በሚሉት ጉዳይ ላይ ምንም የማውቀው ነገር የለም ስትል ውንጀላውን ታስተባብላለች።
ባለፈው ዓመት 300 ገደማ አንጎላውያን የዩኒቨርሳል ቸርች ኦፍ ኪንግደም ጳጳሳት ቤተ-ክርስትያኗ የአስተዳደር ችግር አለባት፤ አልፎም አፍሪካዊ ቀለም የላትም ሲሉ ከብራዚል ኢቫንጀሊካል ቤተ-ክርስትያን ራሳቸውን ማግለላቸው አይዘነጋም።
ቤተ-ክርስትያኗ ግን የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል ትላለች።
ዩኒቨርሳል ቸርች ኦፍ ኪንግደም በብራዚልና በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት 8 ሚሊዮን ገደማ አባላት አሉኝ ትላለች። 'የብልፅግና ኃይማኖተ-አስተምህሮ' የምትከተለው ቤተ-ክርስትያን አማኞች ለቤተ-እምነቱ ባበረከቱት መጠን ዓለማዊ ሃብታቸው ይካብታል ስትል ታስተምራለች።
ቤተ-ክርስትያኗ የትኩረት አቅጣጫ መሆን የጀመረችው ባለፈው ዓመት አንጎላውያን ጳጳሳት የብራዚሏ ቤተ-ክርስትያን በገንዘብ ማጭበርበር ተተብትባለች፤ አልፎም አፍሪካዊም ሆነ አንጎላዊ ቀለም የላትም ሲሉ ወቀሳ ማሰማት መጀመራቸውን ተከትሎ ነው።
ይህንን ተከትሎ የአንጎላ ባለሥልጣናት ቤተ-ክርስትያኗ ላይ ምርመራ ከፍተዋል።
ከትናንት በስቲያ [አርብ] ነው የአንጎላ ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ አልቫሮ ዳ ሲልቫ ሰባት የዩኒቨርሳል ቸርች ኦፍ ኪንግደም አብያተ-ክርስትያናት በመንግሥት ቁጥጥር መዋላቸውን ይፋ ያደረጉት።
ጠቅላይ አቃቤ-ሕጉ አብያተ ክርስትያናቱን በቁጥጥር አዋልን ማለት ወንጀል ስለመፈፀሙ በቂ ማስረጃ አለን ማለት ነው ብለዋል።
'ከወንጀለኞች ጋር መተባበር፣ ግብር ማጭበርበር፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ እምነት ማጉደልና ሌሎችም ወንጀሎች ተፈፅመዋል ይላሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ።
'ዩኒቨርሳል ቸርች ኦፍ ዘ ኪንግደም ኦፍ ጋድ' በብራዚሉ ትልቁ ኢቫንጀሊካል ቤተ-ክርስትያን ክንፍ ነው።













