እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት መውጣቷን የሚያመለክተው የ 50 ሳንቲም ፓውንድ ይፋ ሆነ

የእንግሊዚ ከአውሮፓ ሕብረት መውጫ መታሰቢያ ሳንቲም

የፎቶው ባለመብት, PA Media

እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት መውጣቷን የሚያመለክተው የ 50 ሳንቲም ፓውንድ መታሰቢያ በቻንስለር ሳጂዲ ጃቪድ አማካኝነት ይፋ ተደርጓል።

ሳንቲሟ "ከሁሉም አገራት ጋር ሰላም፣ ብልጽግና እና ጓደኝነት" የሚል ጽሑፍ እንዲሁም "ጥር 31" የሚል ቀን ተጽፎባታል።

ሚስተር ጃቪድ እንግሊዝ ከአውሮፓ ሕብረት የምትወጣበትን ቀን ታሳቢ በማድረግ ሳንቲሞቹን ማምረት እንዲጀምሩ ጥቅምት 31ን በመምረጥ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር። ይህንን ተከትሎም በርካታ ሳንቲሞች በህትመት ላይ የነበሩ ሲሆን የቀኑ መራዘም ግን በሳንቲሞቹ ላይ ሊታተም የነበረው ቀን ተቀይሮ ሌላ ቀን እስኪወሰን ድረስ እንዲዘገይ ተደርጓል።

አዲስ ምዕራፍ

ከሚቀጥለው አርብ ጀምሮ ቁጥራቸው ሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ ሳንቲሞች በመላው እንግሊዝ ገበያ ላይ ይውላሉ። በዓመቱ መጨረሻ ደግሞ ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ይጨመራሉ ተብሏል።

ሚስተር ጃቪድ ሳንቲሟን በበላይነት ለማሳተም ኃላፊነት የተሰጣቸው ግለሰብ ናቸው። ያሳተሙትን ሳንቲም ምን እንደሚመስልም በዚህ ሳምንት ለጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ለማሳየት ፕሮግራም ተይዞላቸዋል።

እንግሊዝ ከአውሮፓ ሕብረት የምትወጣበትን ዕለት በማስመልከትና የሳንቲሟን ህትመትም የዚሁ አካል በማድረግም ሮያል ሚንት የደቡብ ዌልስ መቀመጫውን ለ24 ሰዓታት ክፍት ያደርጋል። ይህም የሚደረገው ጥር 31 (እ.አ.አ) ሰዎች ወደ ስፍራው በመሄድ የራሳቸውን የብሬግዚት መታሰቢያ ሳንቲም እንዲያሰሩ እድል ለመስጠት በማሰብ ነው።

"ከአውሮፓ ሕብረት መውጣት ለእኛ ትልቅ ታሪካዊ ኹነት ነው፤ በመሆኑም ይህች የመታሰቢያ ሳንቲም የአዲሱ ምዕራፋችን ማስጀመሪያ ነች" ብለዋል ሚስተር ጃቪድ።

እንግሊዝ ከአውሮፓ ሕብረት በፈረንጆቹ ጥር 31 ወይም ሳምንት አርብ የምትወጣበትን ሰነድ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከፈረሙ በኋላ ፓርላማው ደግሞ በቀጣዩ ረቡዕ ያጸድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል።