በስህተት የገባላቸውን አንድ ሚሊየን የመለሱት የመቀለ ነዋሪ

የፎቶው ባለመብት, ደሳለኝ ብስራትና አንበሳ ባንክ
ከሰሞኑ በስህተት የተላከላቸው 1 ሚልዯን ብር ለባንኩ ወስደው ያስረከቡት የመቀለ ከተማ ነዋሪው ድርጊት ብዙዎችን አጀብ አሰኝቷል። የገንዘቡ ባለቤትም ገንዘቡን ተቀብሏል።
ነገሩ ወዲህ ነው። ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ደሳለኝ ብስራት ዕለተ ቅዳሜ ታኃሣሥ 18 አመሻሽ ላይ ቁጭ ባሉበት በተንቀሳቃሽ ስልካቸው አንድ መልዕክት ይደርሳቸዋል። ይህም 'አንበሳ ኢንተርናሸናል' ከተባለ የተላከ መልዕክት '1 ሚልዮን ብር ገብቶልሃል' ሲል ይነበባል።
«ስህተት መሆኑ ገባኝ የአንበሳ ባንክ አካውንቴ አዲስ መሆኑን ሳስብ ነው። ሌላ አካውንት ቢሆን ሰው አድርጎልኛል ብዬ አስብ ነበር። አካውንቱ አዲስ ስለሆነ ግን ብዙ ሰው አያቀውም ተሳስተው ነው ብዬ ሰኞ ጥዋት ወደ ባንክ ቤት ሄድኩኝ።»
ስህተቱ እንዴት ሊፈጠር ቻለ?
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የመርካቶ ነጋዴ ከአንድ ሌላ ቻይናዊ ጋር ባላቸው ውል መሠረት 1 ሚሊዮን ብር ለሌላ ግለሰብ መላክ ነበረባቸው። ቻይናዊው ብር የሚላክለትን ግለሰብ የሂሳብ ደብተር ቁጥርም ይሰጣቸዋል፤ እኝህ ግለሰብም እነደተባሉት ገንዘቡን ለመላክ ወደ አንበሳ ባንክ ያመራሉ። ባንክ ሲደርሱ ግን የተሰጣቸው የሂሳብ ደብተር ቁጥር እና የባለቤቱ ስም እሚመሳሰል አልነበረም።
በግዜውም ጉዳዩን ለማጣራት የሞከሩት የገንዘቡ ላኪ ወደ ቻይናዊው አጋራቸው ደውለው ሁኔታውን ያስረዱታል። ነገር ግን ወከባ ውስጥ የነበረው ቻይናዊ አጋራቸው «እንግዲህ እኔ ስም ተሳስቼ ይሆናል እንጂ ቁጥሩስ ትክልል ነው ግድየለህም አስገባው» ይላቸዋል። አንድ ሚሊዮን ብሩም ዘሎ የአቶ ደሣለኝ አካውንት ወስጥ ዘው ማለት።
የአንበሳ ባንክ የራጉኤል ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ መድሃንዬ ኪዳነ ከመቐለ ወደ ቅርንጫፋቸው ሲደወል «በወቅቱ እኛ የተሳሳትን መስሎን ነበር» ይላሉ። ሆኖም ብሩ የተላከበት ማስረጃ ሲታይ ምንም ስህተት የለም። ይሄኔ ለገንዘቡ ላኪ ደውለው ሁኔታውን እነደነገሯቸው ያስረዳሉ። ላኪው የመርካቶ ነጋዴ ሁኔታውን ሲሰሙ እግጅ እንደተደናገጡ ያወሳሉ።
«ተጠቀምበትና ጠያቂ ከመጣ በኋላ ትመልሰዋለህ»
ክስተቱን የሰሙ የአቶ ደሣለኝ ወዳጆች በሁኔታው አፋቸውን ሸፍነው ተገረሙ። ግማሹ መልካም ነገር ነው ያደረግከው ይለኛል፤ ግማሹ ደግሞ ምነው ደሣለኝ? የሚል አስተያየት ይሰጣቸዋል። «አውጥተህ አሰቀምጠው»፤ «ዝም ብለህ ተጠቀምበትና ጠያቂ ከመጣ በኋላ ትመልሰዋለህ» ያሏቸውም እነደነበሩ አልደበቁም። እሳቸው ግን «መመለስ ካለብኝ በጊዜ ነው መመለስ ያለብኝ ብዬ መልሽላሁ» ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, ደሳለኝ ብስራት
አቶ ደሳለኝ በምላሹ ምን አገኙ?
አንበሳ ባንክ ለአቶ ደሣለኝ የምስጋና ደብዳቤ በመስጠት ለቅን ተግባራቸው እውቅና እንደሰጣቸው አቶ መድሃዬ ይናገራሉ። «የአቶ ደሳለኝ ተግባር ከአእምሮ በላይ ነው ብዙ ነገር በሚበላሽበት ዘበን» ሲሉ ክስተቱን ይገልፁታል።
ተገልጋዮችም የሚልኩበትን የሂሳብ ደብተር ቁጥር በትክክል ከቻሉም የሂሳብ ደብተሩ ባለቤት ስም ከአባት እና አያት ጭምር ቢያውቁ መልካም ነው ሲል ምክር የጣል ያደርጋሉ።













