እሾህን በእሾህ፡ የመጠጥ ሱስን መከላከያው አደንዛዥ መድኃኒት
![ሰዎች መጠጥ [ቢራ] ይዘው](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/6088/production/_109921742_731636ed-e0fc-4cf1-ae79-b80dc672ea1e.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኬታሚን የተሰኘውን ክኒና አንድ ጊዜ ከዋጡ አልኮል የሚባል ነገር ያስጠላዎታል ሲል የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ይፋ አድርጓል።
ለዘጠኝ ወራት ጥናቱን ሲከናውኑ የነበሩት ባለሙያዎች እንደሚሉት ኬታሚን የወሰዱ ሰዎች የመጠጥ ፍላጎታቸው እጅጉን ቀንሷል።
ኬታሚን የማደንዘዣ መድኃኒቶች ወስጥ የሚገኝ ንጥረ-ነገር ነው።
ይህንን መድኃኒት ነው አጥኚዎቹ የመጠጥ ሱስን መከላከያው ምርጥ መላ ሲሉ ያጩት።
ቢሆንም ባለሙያዎቹ ይህ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ስለሆነ ተጨማሪ ምርመራዎች ያሻሉ ባይ ናቸው።
ኬታሚን
ኬታሚን በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው በአደንዛዥ፣ አረጋጊ እና ስቃይ ማስታገሻ መድኃኒቶች ውስጥ ነው። ኬታሚን ለሰዎች ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም የሚሰጥ መድኃኒት ነው።
ንጥረ-ነገሩ ሰመመናዊ ባሕርይ ስላለው ከብዙ መድኃኒቶች ጋር እየተደባለቀ ጥቅም ላይ ይውላል፤ 'የፓርቲ መድኃኒት' የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል።
ኬታሚን ያለበት መድኃኒት ከሃኪም ትዕዛዝ ውጭ መውሰድ ሰውነት ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።
የእንግሊዝ መንግሥት ኬታሚንን 'መደብ ቢ' ከሚባሉት መካከል ያስቀምጠዋል። ይህ ማለት መድኃኒቱን ይዞ መገኘት፣ መጠቀም፣ ማምረትም ሆነ መሸጥ በሕግ ያስቀጣል።
የኬታሚን ጎንዮሽ ጉዳቶች
- የሽንት ከረጢት ላይ የሚደርስ ጉዳት
- የጤና መታወክ ስሜት
- ግራ መጋባት
- የመርሳት ችግር
- የጡንቻ አለመታዘዝ
- ጡዘት/ሰመመን
- ጭንቀት
- ያለፈን እያሰቡ መጨነቅ

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library
ታድያ ለምን ጥቅም ላይ ይውላል?
ጥናቱ 55 ወንድና 35 ሴት ጠጪዎች ተሳትፈውበታል። ተሳታፊዎቹ በሳምንት ቢያንስ 30 'ጃምቦ' [15 ሊትር ገደማ] ቢራ እንዲጠጡ ተደረገ። ይህ መጠን የሰው ልጅ በሳምንት መጠጣት አለበት ተብሎ ከሚመከረው በአምስት እጥፍ የላቀ ነው።
ሰዎቹ ከዚያ በፊት የመጠጥ ሱስ የሌለባቸውና ምንም ዓይነት ከመጠጥ ጋር የተያያዘ ሕክምና ያላገኙ ናቸው።
መጀመሪያ ከቢራ ውጪ ያለ የአልኮል መጠጥ ፎቶ እንዲያዩ ተደረገና ምን ያህል ጉጉ እንደሆኑ ተጠና፤ ከዚያ ቢራ እንዲጠጡ ተደረገ።
ከዚያም በሦስት ቡድን እንዲከፈሉ ተደርጎ እንደ መጀመሪያ የአልኮል መጠጥ ፎቶ ከተመለከቱ በኋላ በቢራ ፋንታ በጣም ትንሽ የኬታሚን ጠብታ ተሰጣቸው። በሁለተኛው የጥናት ደረጃ በኬታሚን ፈንታ ምንም ጉዳት የሌለው ጠብታ ተሰጣቸው። ከዚያ ደግሞ የኬታሚን ጠብታ።
ይህ ሂደት ለዘጠኝ ወራት እንዲቀጥል ተደረገ። በስተመጨረሻም ሦስቱም ቡድን ውስጥ ያሉ ሰዎች ለአልኮል መጠጥ ያላቸው ፍላጎት ሲለካ ከበፊቱ እጅጉን የቀነሰ ሆኖ ሊገኝ ችሏል።
በተለይ የመጀመሪያ ቡድን ውስጥ ያሉ ሰዎች የመጠጥ ፍላጎታቸውን በግማሽ ከመቀነሳቸው በላይ ቀስ ብለው መጠጣት ጀመሩ።
አጥኚዎቹ ምን ይላሉ?
የጥናቱ ቡድን ኃላፊ ዶክተር ራቪ ዳስ «ሰዎች ከአልኮል ሱስ ችግር እንዲለቀቁ እንፈልጋለን፤ ነገር ግን ይህ የመጀመሪያው ደረጃ ጥናት ነው» ይላሉ።
ሌሎች የጥናት ቡድኑ ኃላፊዎችም ሙከራው ገና ብዙ እንደሚቀረው ይስማማሉ።
«በርካታ ሰዎች የሚሳተፉበት ተለቅ ያለ ጥናት ይጠይቃል። ኬታሚን ለአልኮል ሱስ ዘላቂ መፍትሄ መሆኑን አፋችንን ሞልተን መናገር የምንችለው የዚያን ጊዜ ነው።»
ሌላኛው አጥኚ ፕሮፌሰር ሴሊያ ሞርጋን፤ «ኬታሚን ሱስ የሚያስይዝ ንጥረ-ነገር በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል። በተለይ በሽንት ከረጢት ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ለዚህ ነው ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ልናደርግ የሚገባው» ይላሉ።













