“አንቺሆዬ”፡ የኢትዮጵያዊያት ታሪክን መናገር

የፎቶው ባለመብት, Anchihoye
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውና "አንቺሆዬ" የተሰኘው ፌሚኒስት ፊልም ፌስቲቫል ተካሄዷል።
ፌስቲቫሉ ምሳሌ የሆኑ ኢትዮጵያዊያት ታሪክን የመናገር መንፈስን የተላበሰም ነበር።
ዝግጅቱ ብዙ ጊዜ እንዲሁ በፊልም ስለምትሳለው ሳይሆን የዛሬዋን እናም ብዙዎች ራሳቸውን ሊያዩ ስለሚችሉባት ሴት ለምን አይወራም አይነገርም? የሚል ጥያቄንም ያነገበ ነበር።
የአርበኛዋና የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ስንዱ ገብሩን ህይወት የሚያስቃኘው ፊልም በፌስቲቫሉ ለእይታ ከበቁት ፊልሞች አንዱ ነበር።
ሴቶች ከወንዶች እኩል እንዲቆሙ በማይጠበቅበትና ሴት ልጅ እንደዚህ ወይም እንደዚያ መሆን አለባት የሚለው የማህበረሰቡ ጫና ያይል በነበረበት፤ በእርሷ ዘመን እንደ ፍላጎቷና እንደ እምነቷ በኖረችው አስናቀች ወርቁ ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ፊልምም ታይቷል።
ሴታዊትና የሎው ሙቭመንት "አንቺሆዬን" ያዘጋጁት ሚዲያ ማህበረሰብንና ባህልን በመቅረፅ ረገድ ያለውን ተፅኖ በማጤን ነው።
የየሎው ሙቭመንቷ ረድኤት ከፍአለ "ያሳየነው የፌሚኒስት (የሴቶች እኩልነት) ሃሳቦችን ለማንፀባረቅና ከሥርዓተ-ፆታ ጋር በተያያዘ በማህበረሰቡ ዘንድ ሊቀየሩ ይገባል፣ ለውጥ ያስፈልጋል የምንልባቸውን ጉዳዩች የሚያመላክቱ ፊልሞችን ነው" ትላለች።
በፌስቲቫሉ የውይይት መድረኮችን ተዘጋጅተው ነበር።
በመገናኛ ብዙሃን የሴቶች ውክልና ምን ይመስላል? በፊልሞች ላይ ሴቶች የሚሳሉት እንዴት ነው? የሚሉና መሰል ርዕሰ ጉዳዩች ተነስተው የነበረ ሲሆን፤ በፊልሙ ኢንዱስትሪ ተጠቃሽ የሆኑት አዜብ ወርቁና መአዛ ወርቁም ጽሁፍ አቅራቢዎች ነበሩ።
"ሥራ የላትም" የተሰኘውን ፊልም ያዘጋጀው ሃኒባል አበራም ፅሁፍ አቅርቧል።
"አብዛኛውን ጊዜ ፊልም ላይ የሚሳሉት ሴቶች እኛን ልናይ የማንችልባቸው ናቸው" ትላለች የሴታዊቷ ካምላክነሽ ያሲን።
በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የፊልም ፕሮዲውሰሮችና ዳይሬክተሮች ከተለመደው ሴቶች ከሚሳሉበት መንገድ መውጣት ከባድ እንደሚሆንባቸው መግለፃቸውን ትናገራለች።
በአጠቃላይ ፌስቲቫሉ የፌሚኒስት ሃሳቦችን ማስረፅን ጨምሮ ሴቶች በሚዲያ የሚሳሉበት መንገድ እንዲስተካከል አስተዋፆ እንደሚያደርግ ታምናለች።
ፌስቲቫሉ የተካሄደው በቫንዳስ ሲኒማ ባለፈው ሳምንት ከአርብ እስከ እሁድ ነበር። የመጀመሪያው ፌሚኒስት ፊልም ፌስቲቫል ከመሆኑ አንፃር የታዳሚው ቁጥር ጥሩ የሚባል እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልፀዋል።
የሴቶች ሚና በቴክኖሎጂ ዘርፍም በፌስቲቫሉ አንድ መወያያ ርእሰ ጉዳይ ነበር።












