የዓለም ባንክ በጦርነቱ የተከሰተው የምግብ ቀውስ 'ሰብአዊ ጥፋት' ያስከትላል ሲል አስጠነቀቀ

የስንዴ እርሻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ በተከሰተው የምግብ ቀውስ ዓለም "የሰብዓዊ ጥፋት" እያጋጠማት ነው ሲሉ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ ገለጹ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ድህነትን ለማቃለል የተቋቋመውን ተቋም የሚመሩት ማልፓስ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቀውሱ ከቀጠለ የምግብ ዋጋ ንረት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ድህነት እንደሚገፋና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል።

"ይህ የሰብዓዊ ጥፋት ነው። የተመጣጠነ ምግብ እየቀነሰ ይሄዳል። ምንም ማድረግ ለማይችሉ መንግስታት የፖለቲካ ፈተና ይሆናል። መንስኤ ባይሆንም የዋጋ መናር ያጋጥማቸዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

የዓለም ባንክ የምግብ ዋጋ በ37 በመቶ ሊጨምር እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል።፣ ይህም "ለድሆች ከፍተኛ የሚባል" ሲሆን "ትንሽ እንዲመገቡ እና እንደ ትምህርት ቤት ላሉት የሚኖራቸውን ወጪ ያሳንሳል። በእውነቱ ይህ ፍትሃዊ ያልሆነ ቀውስ ነው። በጣም ድሃ የሆኑት ላይ የበለጠ ጫናው ያርፋል። ይህ በኮቪድ ወቅት ተመሳሳይ ነበር ።

የዋጋ ንረቱ ሰፊና ጥልቅ ነው ያሉ ሲሆን "በተለያዩ ዓይነት ዘይቶችና እህሎች ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ነው። የስንዴ ዋጋ መናር ደግሞ እንደበቆሎ ያሉ ሰብሎች ዋጋ እንዲንር ያደርጋል" ብለዋል።

ዓለም ላይ ሁሉንም ሰው ለመመገብ የሚያስችል በቂ ምግብ ነበረ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበሩ የምግብ ክምችቶች በታሪክ ደረጃ ከፍተኛውን ደረጃ ይዞ ነበር።

ነገር ግን ምግቡን ወደሚፈለገው ቦታ ለማድረስ የመጋራት ወይም የሽያጭ ሂደት ሊኖር ይገባል ብለዋል።

ማልፓስ ሃገራት የምርት ድጎማ እንዳይሰጡ ወይም የዋጋ ቅነሳ እንዳያደርጉ አበረታተዋል።

ይልቁንም ትኩረቱ እጅግ በጣም ድሃ ለሆኑ ሰዎች ከሚደረገው እርዳታ ጎን ለጎን የማዳበሪያ እና የምግብ አቅርቦትን በዓለም ዙሪያ ማሳደግ ላይ መሆን አለበት ብለዋል።

የዓለም ባንክ ኃላፊ በማደግ ላይ ላሉ ሃገራት የምግብ እና የሃይል ዋጋ እየጨመረ ባለበት ወቅት የወረርሽኙን ዕዳ ለመክፈል ባለመቻላቸው "ችግር ውስጥ ያለ ቀውስ" ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል ።

"ይህ የእውነት ነው። ለአንዳንድ ሃገራትም እየተፈጠረ ነው። ምን ያህል ርቀት እንደሚሄድ አናውቅም። በአሁኑ ጊዜ 60% የሚሆኑት በጣም ድሃ ሀገራት በእዳ ጫና ውስጥ ናቸው ወይም ለከፍተኛ ዕዳ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

"ስለ ዕዳ ቀውስ መጨነቅ አለብን። በጣም ጥሩው መንገድ ቀደም ብሎ መጀመር ነው። ዘላቂ ያልሆነ ዕዳ ያለባቸውን ሃገሮች የዕዳ ጫና ለመቀነስ መንገዶችን ያስፈልጋል። ረዘም ላለ ጊዜ ከተቀመጠ የከፋ ይሆናል" ሲሉም አክለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳለው የዩክሬን ጦርነት በምግብ ዋጋ ላይ "ከፍተኛ የዋጋ ንረት" እንዲፈጠር አድርጓል ብሏል። በመጋቢት ወርም ክብረ ወሰን የሆነ ጭማሪ መከሰቱን አስታውቋል።

ጦርነቱ የዓለማችን ትልልቅ የሱፍ ዘይት አቅርቦትን ሲያቋርጥ እና የአማራጭ የሚባሉትም ዋጋቸው እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ዩክሬን እንደ በቆሎ እና ስንዴ ያሉ እህሎችም ዋነኛ አምራች ነች። የእነዚህም ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቧል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት "በጥቁር ባህር ክልል ያለው ጦርነት በእህል እና በአትክልት ዘይት ገበያዎች ከፍተኛ አለመረጋጋት ፈጥሯል" ብሏል።

የተባበሩት መንግስታት የምግብ ዋጋ መረጃ ጠቋሚ በዓለም ላይ በብዛት የሚሸጡ የምግብ ሸቀጦችን ይከታተላል። በዚህም የእህል፣ የአትክልት ዘይት፣ የወተት፣ የስጋ እና የስኳር ዋጋን ይለካል።

መረጃው መያዝ ከጀመረበት ከ60 ዓመታት በላይ ሲሆነው የአሁኑ የዋጋ ንረት ከፍተኛው ነው።