እነ አፕል ጉግልና ማይክሮሶፍት በ14 የኮንጎ ቤተሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

የማዕድን ቆፋሪ በኮንጎ

የፎቶው ባለመብት, AFP

አፕል፣ ጎግል፣ ቴስላ፣ ማይክሮሶፍት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሕጻናት የማዕድን አውጪዎች መሞታቸውን ተከትሎ በተከፈተው ክስ ላይ ስማቸው ተጠቅሷል።

ክሱ የተከፈተው 14 ኮንጓዊ ቤተሰቦችን በመወከል በዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች በኩል ነው። ክሱ እንደሚያሳየው ድርጅቶቹ ለምርታቸው የሚጠቀሙበት ኮባልት ከህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ጋር እንደሚያያዝ ያውቃሉ ሲል ያትታል።

ዲሞክራቲክ ኮንጎ ዓለማችን ከሚያስፈልጋት የኮባልት ምርት 60 በመቶውን ታመርታለች።

ማዕድኑ የኤሌትሪክ መኪናዎችን፣ ላፕቶፖችንና ስማርት ስልኮችን ለማንቀሳቀስ የሚያገለግለውን ሊቲየም አየን ባትሪ ለማምረት ይውላል። ይኹን እንጂ ምርቱ ከሕገ ወጥ የማዕድን ማውጣት ጋር እንዲሁም ከሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከሙስና ጋር ስሙ ተደጋግሞ ይነሳል።

በአሜሪካ የተከፈተው ክስ እንደሚያስረዳው እነዚህ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቹ የሚጠቀሙት የኮባልት ማዕድን ከሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ጋር ተያያዞ የተገኘ እንደሆነ "ተገቢ እውቀት" አላቸው ሲል ያትታል።

አክሎም የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱን በመቆጣጠር ረገድ ቸልተኝነት ታይቶባቸዋል፤ ይልቁንም ከዚህ የጉልበት ብዝበዛ ትርፍን አጋብሰዋል ሲል አስፍሯል።

በክሱ ላይ ከተጠቀሱት ድርጅቶች መካከል የኮምፒውተር አምራቹ ዴልና 14ቱ ቤተሰቦች ልጆቻችን ሰርተውበታል ያሉትን የማዕድን ማውጫ በበላይነት የሚያስተዳድሩት የማዕድን አምራች ድርጅቶቹ ዚህጃንግ ሁአዮና ግሌንኮር ይገኙበታል።

ግሌንኮር በዩናይትድ ኪንግደም ለሚታተመው ቴሌግራፍ ጋዜጣ በሰጠው ምላሽ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን ተግባር እንዳልፈፀመ ገልጿል።

ማዕድኑ የኤሌትሪክ መኪናዎችን፣ ላፕ ቶፖችንና ስማርት ስልኮችን ለማንቀሳቀስ የሚያገለግለውን ሊቲየም አየን ባትሪ ለማምረት ይውላል

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty

የምስሉ መግለጫ, ዲሞክራቲክ ኮንጎ ዓለማችን ከሚያስፈልጋት የኮባልት ምርት 60 በመቶውን ታመርታለች

ቢቢሲ ከዚህጃንግ ሁአዮ ምላሽ ለማግኘት ጠይቋል።

በዩኬ የሚታተመው ጋርዲያን ጋዜጣ ባስነበበው የክስ ዘገባው ላይ፣ ሕጻናት ማዕድን ቆፋሪዎች የሚሰሩበት ጉድጓድ ተደርምሶ ከነሕይወታቸው ተቀብረዋል፣ በመደርመሱ በደረሰባቸው ጉዳትም ዘላቂ የጤና ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል።

14ቱ ቤተሰቦች ኩባንያዎቹ ላደረሱባቸው የስነልቦናና የአካል ጉዳት ካሳ እንዲከፈሏቸው ይፈልጋሉ። ማይክሮሶፍት ለቴሌግራፍ በሰጠው ምላሽ ከማዕድን ማውጣት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ሕገወጥነትን እንደሚያጣራ አስታውቋል።

ቢቢሲ ከጎግል፣ አፕል፣ ዴልና ቴስላ ምላሽ ለማግኘት ጠይቋል።